ኤች አይቪ ኤድስ በኬንያ | የጋዜጦች አምድ | DW | 14.09.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

ኤች አይቪ ኤድስ በኬንያ

በምስራቅ አፍሪካዊቷ ኬንያ ኤች አይቪ ኤድስ የብዙዎችን ህይወት መቅጠፍ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። በአገሪቱ የበሽታዉን ስርጭት በመቆጣጠር ተግባር ላይ የተሰማሩ ዓለም ዓቀፍና አገር በቀል ድርጅቶችም በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ። ሆኖም እንደ ድርጅቶቹ መብዛትና እንደተመደበላት የገንዘብ ድጋፍ መጠን ሲታይ ይህ ነዉ የሚባል የጎላ ለዉጥ አለመታየቱ ነዉ የሚነገረዉ።

የዛሬ አምስት ዓመት ነበር የኬንያ መንግስት HIV/AIDS በአገሪቱ ህዝብ እየጨረሰ እንደሚገኝ በይፋ የገለፀዉ። ሆኖም ችግሩን ለመቆጣጠር የተወሰደዉ እርምጃ እጅግ የዘገየና ያልተቀናጀ መሆኑ ነዉ የሚተቸዉ።
ከመንግስት የተገኘዉ መረጃ እንደሚያሳየዉ 30ሚሊዮን ይሆናል ተብሎ ከሚገመተዉ የአገሪቱ ዜጋ መካከል 2ሚሊዮን የሚሆነዉ በHIV ቫይረስ የተያዘ ነዉ።
ከ200,000 በላይ የሚሆኑት የበሽታዉ ሰለባዎች የእድሜ ማራዘሚያና የህመም ማስታገሻ የሚያስፈልጋቸዉ ሲሆኑ በየእለቱም በኬንያ ከኤድስ ጋር በተገናኙ በሽታዎች 700 ሰዎች ይሞታሉ።
በኬንያ AIDS Watch የተሰኘዉ ተቋም አስተባባሪ ኢግናቱስ ኪቤ እንደገለፁት እንዲህ ያለ አደጋ በህዝቡ ህይወት ላይ መምጣቱን በይፋ የገለፀ አካል ለመከላከያ የታቀደዉን ገንዘብ ለመልቀቅ ረጅም ጊዜ ሊፈጅበት አይገባም።
በHIV/AIDS የተያዙ ወገኖች የሚያስፈልጓቸዉን መድሃኒቶች የመግዛቱ ሂደትም ሆነ ጨረታዉ ከስድስት እስከ ሰባት ወራት ይፈጃል። በዚህ መሃልም በርካታ በሽተኞች አስፈላጊዉን እርዳታ ሳያገኙ ህይወታቸዉ ያልፋል።
መንግስት ከሁሉም ነገር በቅድሚያ የተቆላለፈ የአሰራር ስልቱን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መለወጥ እንዳለበትም ያስገነዝባሉ።
በአሁኑ ጊዜ የአገሪቱ የገንዘብ ሚኒስቴር ነዉ ለዚሁ ጉዳይ ተብሎ የሚላከዉን የእርዳታ ገንዘብ በመረከብ ከHIV ጋር ለተገናኙ ፕሮጀክቶች እንዲያከፈፍል ለብሄራዊ የኤድስ መቆጣጠሪያ ካዉንስል በጀት የሚለቀዉ።
በርከት ያሉ ድርጅቶች ናቸዉ በኬንያ ኤድስን በመዋጋቱ ረገድ ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ የገንዘብ ድጋፍ ከገንዘብና አስተዳደር ወኪል የሚያገኙት።
በዝቅተኛ ደረጃ በህብረተሰቡ ዉስጥ አገልግሎት ለሚሰጡት ቡድኖች ደግሞ ከበላይ አካል ያገኘዉን ገንዘብ የሚመድብላቸዉ ክፍል ሌላ ነዉ።
በዚህ የዕዝ ተዋረድ የተወሳሰበዉ የአሰራር ሥልትም የታሰበዉ እርዳታና ድጋፍ ለበሽተኞች በወቅቱ እንዳይደርስ ከፍተኛ እንቅፋት መሆኑ ነዉ የሚነገረዉ።
አንዳንድ ለጋሾችም ለየፕሮጀክቱ አስፈላጊዉን ገንዘብ የማከፋፈሉ ሂደት እንደ ቀንድ አዉጣ አካሄድ የተንቀራፈፈ ነዉ በማለት በአሰራሩ የተሰማቸዉን ቅሬታ ይገልፃሉ።
በዩናይትድ ስቴትስ የዓለም ዓቀፍ የልማት ተቋም ዉስጥ የHIV/AIDS ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ዋረን ቡኪንግሃም እንደገለፁት የዓለም ዓቀፍ የገንዘብ ድጋፍን በአግባቡ በመጠቀም ረገድ በኬንያ የተጓተተ አሰራር አለ።
ከዚህ ተነስተዉም ለችግሩ መቆጣጠሪያ በሚል የሚሰጠዉ የገንዘብ ድጋፍ ሁሉ በሚፈለግበት ቦታና ጊዜ ስራ ላይ አልዋለም የሚል ስጋት እንዳላቸዉ አስታዉቀዋል።
«እስከማዉቀዉ ድረስ ለዚህ ጉዳይ ተብሎ ለኬንያ መንግስት የገንዘብ ድጋፍ ከተሰጠዉ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል ሆኖም ገንዘቡ ስራ ላይ አልዋለም። እንደዉም በዚህ ገንዘብ የአገሪቱ መንግስት የእድሜ ማራዘሚያና ህመም ማስታገሻ መድሃኒቶችን አልገዛም» ይላሉ ቡኩንግሃም።
በአዲስ ዘዴ ኤድስን፤ የሳንባ ነቀርሳንና ወባን ለመዋጋት የሚዉል ዓለም ዓቀፍ የንዘብ ድጋፍ ከተቋቋመ ሶስት ዓመት ሆነዉ። ብቸኛና ከፍተኛ ገንዘብ ለዚህ ድጋፍ የምትሰጠዉ አገር ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ ናት።
ለኬንያ ከተወሰነዉ 137ሚሊዮን ዶላር መካከልም እስከዛሬ 36ሚሊዮን የሚሆነዉ ተሰጥቷል።
መንግስት እንደሚለዉ ገንዘቡን በማከፋፈሉ ረገድ የታየዉ መጓተት የተፈጠረዉ ትክክለኛ እሰራር ለመከተል ባደረገዉ ጥረት ነዉ።
የብሄራዊ ኤድስ መቆጣጠሪያ ካዉንስል ዳይሬክተር ፓትሪክ ዖሬጌ እንደሚሉት የሚመጣዉን የገንዘብ ድጋፍ በአግባቡ ለመጠቀም የአሰራር ስልት መቀየስ ይኖርባቸዋል።
ያንን ሳያስተካክሉ ገንዘቡ ወጪ ሆኖ ቢሆን ኖሮ ደግሞ አሁን የሚጠቢቃቸዉ ክስ መልኩ ሌላ ይሆን ነበር።
ይህን ለማቃለል ይረዳል በሚልም በአገሪቱ ባጠቃላይ የኤድስን ጨምሮ የገንዘብ አወጣጥንና የበጀት አመዳደብን በተመለከተ አዲስ መመሪያ የማፅደቅ ሂደት ተጀምሯል።
ለጋሾች ባደረጉት ግፊት ባለፈዉ ወር በአገሪቱ ፓርላማ ተቀባይነት ያገኘዉ ይህ አዲስ መመሪያም የፕሬዝደንቱን ፊርማ እየጠበቀ መሆኑ ታዉቋል።
በሌላ ወገን የገንዘቡ አወጣጥ ላላ ይበል የሚለዉን ግፊት የሚያጠናክሩ ቡድኖችም በኤች አይቪ ፕሮጀክቶች ሰበብ ገንዘብ በቀላሉ ማጋበስ ያለሙ ናቸዉ በሚል ትችት ተሰንዝሯል።
ፖለቲከኞችም ተመሳሳይ ስጋት እንዳላቸዉ በመግለፅ ምርመራ ይካሄድበት ሲሉ አሳስበዋል። ሆኖም ባለስልጣናት እፍኝ የማይሞሉ በማህበረሰብ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ብቻ ናቸዉ በዚህ የሚጠረጠሩት ይላሉ።
በእነሱም ዙሪያ ምርመራዉ እየተካሄደ መሆኑን ገልፀዉ ጥፋተኛ ሆነዉ የሚገኙትን ለመቅጣት መዘጋጀታቸዉን ገልፀዋል።ተዛማጅ ዘገባዎች