ኤችአይቪና የስደተኞች ሁኔታ በደቡብ አፍሪካ | የጋዜጦች አምድ | DW | 11.02.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

ኤችአይቪና የስደተኞች ሁኔታ በደቡብ አፍሪካ

በየአመቱ በሺ የሚቆጠሩ አፍሪካዉያን በጦርነትና በምጣኔ ሃብት ችግር ሳቢያ በአህጉሩ በምጣኔ ሃብት ረገድ የተሻለ ደረጃ ላይ ወደምትገኘዉ ወደ ደቡብ አፍሪካ በማያቋርጥ ሁኔታ አደገኛ ጉዞ ያደርጋሉ። የደቡብ አፍሪካ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንደሚለዉ የተሻለ ህይወት ፍለጋ ወደ አገሪቱ ከሚመጡት በርካታ ስደተኞች መካከል አብዛኞቹ የኤችአይቪ ቫይረስን ይዘዉ ይመጣሉ።

ደቡብ አፍሪካ ከቫይረሱ ጋር ለሚኖሩት ዜጎቿ የእድሜ ማራዘሚያ መድሃኒት በምህፃረ ቃል /ARV/ ለማዳረስ ብትጥርም በአንፃሩ በርካታ ጥገኞችና ህገወጥ ስደተኞች ባሉበት አካባቢ ለማዳረስ ከባድ ፈተና ገጥሟታል።
ፕሪቶሪያ የሚገኙዉ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን ተመራማሪ እንደሚሉት በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ስደተኞች እንኳን ኤችአይቪ ኤድስን በተመለከተ አገልግሎት ሊሰጣቸዉ ቀርቶ በጥርጣሬ የሚታዩና በዚያም ሳቢያ ከህብረተሰቡ ጋር እንኳን እንዳይገናኙ መድሎ የሚደረግባቸዉ ናቸዉ።
በአገሪቱ ግንባር ቀደም ፀረኤድስ ቡድን ቃል አቀባይም ይህንኑ አባባል በማስተጋባት በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ጥገኞችና ህገወጥ ስደተኞች ምንም የማድረግ አቅም ስለሌላቸዉ ከፍተኛ መድሎ እንደሚደረግባቸዉ ገልፀዋል።
እንደ አገሪቱ ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፃ በደቡብ አፍሪካ ወደ 100,000 የሚጠጉ ሰዎች ጥገኝነት ተሰጥቷቸዋል።
ህገወጥ ስደተኞች ባለመመዝገባቸዉ ቁጥራቸዉን የአገሪቱ የዉስጥ ጉዳይ ሚኒስት ባያዉቀዉም የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሃላፊዎች እንደሚሉት ወደ አንድ ሚሊዮን ይጠጋል።
በደቡብ አፍሪካ ከሚገኙት ስደተኞች አብዛኛዎቹ ከዲሞክራቲክ ኮንጎ፤ ቡሩንዲ፤ ሩዋንዳ፤ አንጎላ፤ ሶማሊያና በርካቶች ደግሞ ከዚምባቡዌ የሄዱ ናቸዉ።
በነዚህ አገራት የሚታየዉ የኤችአይቪ ስርጭት ለምሳሌ በሩዋንዳ 5.1 በመቶ፤ ዚምባቡዌ 24.6 በመቶ ሲሆን በደቡብ አፍሪካ 28 በመቶ ደርሷል።
በደቡብ አፍሪካ በማንኛዉም ህመም ጊዜ የህክምና አገልግሎት ማግኘት የሚቻለዉ የጥገኝነት ፈቃድ ከተሰጠ በኋላ በመሆኑ ህገወጥ ስደተኞች ይህ መብት የላቸዉም።
የጥገኝነት ፈቃድ የተሰጣቸዉም ቢሆኑ ለህክምና በሚሄዱበት ወቅት መታወቂያቸዉን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል በገሃድ እንደሚታየዉ ግን መታወቂያዉን መያዙም የማይጠቅምበት ሁኔታ አለ።
በዋና ከተማዋ አካባቢ በሚገኘዉ ኢኩሩሉኒ ሃኪም ቤት የሚያገለግሉት ዶክተር በርናንድ እንደገለፁት ጥገኝነት ያገኙ በሽተኞች በሚመጡበት ጊዜ ለምዝገባ መረጃ ይጠየቃሉ።
እንግዳ መቀበያዉ ቦታ ላይ በሚገኙት ሰራተኞች በደንብ የተማሩ ባለመሆናቸዉ የመታወቂያዉን ህጋዊነት ማወቅ ስለማይችሉ ተጨማሪ መረጃ እንዲያመጡ ያስጨንቋቸዋል።
በዚህም ሳቢያ ይላሉ ዶክተር በርናንድ በሽተኛዉ በህገወጥ ስደተኝነት ይመዘገብና ህክምና ለማግኘት እንደህመሙ ሁኔታ ከ290 እስከ 2,450 ዶላር እንዲከፍል ይደረጋል።
እንደ ዶክተሩ ገለፃ አብዛኞቹ ስደተኞች ይህን ያህል ገንዘብ የመክፈል አቅም ስለሌላቸዉ ሃኪም ሊያያቸዉ አይችልም።
ያለሃኪም ትዕዛዝ ደግሞ ከኤችአይቪ ቫይረስ ጋር የሚኖሩ በሽተኞች ማንኛዉንም አይነት የህክምና እርዳታ ማግኘት አይችሉም።
ከዛሬ ሶስት አመት በፊት የደቡብ አፍሪካ ፍርድ ቤት መንግስት የእድሜ ማራዘሚያ መድሃኒቶችን ለሚያስፈልጋቸዉ ዜጎቹ እንዲያቀርብ በማዘዙ የጤና ባለሙያዎች መድሃኒቱን በነፃ ማከፋፈል ጀመሩ።
የመታወቂያ ወረቀቶችን በአግባቡ ያለመረዳት ችግር ባስከተለዉ ጦስ ወደ ጤና ጣቢያዎች እንዳይደርሱ በመደረጉ በአገሪቱ የሚገኙ ጥገኞች መድሃኒቶቹን 50 ዶላር እያወጡ ለመግዛት ተገደዋል።
ይህንንም መግዛት የሚችሉትና በህክምናዉ ለመረዳት ያቻሉት በጣም ጥቂትና የመግዛት አቅም ያላቸዉ ብቻ ናቸዉ።
ዶክተሩ እንደሚሉት የቋንቋ ችግርም ሌላዉ ስደተኞች የሚገጥማቸዉ ችግር ነዉ።
አንድ ስደተኛ ስልክ ሲደዉልም ሆነ በግንባር ለህክምና ሲመጣ እንግሊዝኛ የማይናገር ከሆነ ለሰአታት አስተርጓሚ ለመጠበቅ እንደሚገደድ እኔ የአይን ምስክር ነኝ ይላሉ።
ከሁለት አመት በፊት በተደረገ ጥናት በደቡብ አፍሪካ ከሚገኙ 1,500 ጥገኝነት ጠያቂች መካከል እስካሁን መልስ የተሰጠዉ 11 ከመቶ ለሚሆኑት ሲሆን ቀሪዉ 89 በመቶ ገና ሶስት አመት መጠበቅ ይኖርበታል ጥገኝነት ለማግኘት።
ከሌሎች የእሪካ አገራት በተለየ ሁኔታ በደቡብ አፍሪካ የስደተኞች መጠለያ ባለመኖሩ ጥገኝነት ፈላጊዎችም ሆኑ ህገወጥ ስደተኞች በከተማዉጥ ካለምንም እርዳታ ይኖራሉ።
በአሁኑ ሰዓት የሚያየዉ የስደተኞች የህክምና ችግር ምናልባት አገሪቱ ለዜጎቿ የእድሜ ማራዘሚያ መድሃኒት በስፋት ካዳረሰች በኋላ ሊሻሻል የሚል ተስፋ አለ።
ያም ቢሆን እስካለፈዉ አመት መጨረሻ ድረስ ለ53,000 ሰዎች አዳርሳለሁ በማለት መንግስት አቅዶት የነበረዉ የመድሃኒት ስርጭት የተከናወነዉ ለ19,000 ሰዎች ብቻ ነዉ።
ይህምከዛሬ ሶስት ዓመት በፊት መንግስትን ወደ ፍርድ ቤት ያቀረበዉን የተግባራዊ ህክምና ኮሚሽን በምህፃረ ቃል TAC በድጋሚ ለክስ የሚያነሳሳ ነዉ ይላሉ ታዛቢዎች።
በደቡብ አፍሪካ 5.6 ሚሊዮን ሰዎች በኤድስ ተጠቅተዋል ሆኖም እንደ TAC ግምት 300,000 ሰዎች ብቻ ናቸዉ የእድሜ ማራዘሚያ መድሃኒት ማግኘት የቻሉት።


ተዛማጅ ዘገባዎች