ኤቦላን የመከላከሉ ጥንቃቄ | ጤና እና አካባቢ | DW | 06.08.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

ኤቦላን የመከላከሉ ጥንቃቄ

በተለያዩ አራት የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት የታየዉ የኤቦላ ተሕዋሲ እስካሁን ለ826 ሰዎች ህልፈተ ሕይወት ምክንያት ሆኗል። ባለፈዉ ሳምንት ሴራሊዮን ዉስጥ ተሕዋሲዉ በሽተኞችን ይረዱ የነበሩ አንድ ዶክተርን ህይወት መቅጠፉ አጀብ ተብሎለት ሳያበቃ፤

አሁንም ሌላ ዶክተር በኤቦላ መያዛቸዉን ናይጀሪያ አረጋግጣለች። የሰዎች ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ልማድ ከፍ እያለ በመሄዱ ምክንያት በአንድ አካባቢ የተከሰተ ወረርሽኝ ወደሌላ የሚዛመትበት አጋጣሚ እየፈጠነ መሄዱ በግልፅ እየታየ ነዉ። ለዚህም ነዉ ኤቦላ ዛሬ የጥቂት አፍሪቃ ሃገራት ብቻ ሳይሆን የዓለምን ትኩረት የሳበዉ። ስለሌሎች ሃገራት የጥንቃቄ ርምጃ ስናወሳ ኢትዮጵያስ ማለታችን አይቀርም፤ በአፍሪቃ መዲናነቷ የበርካታ አፍሪቃ ሃገራት ዜጎች መዳረሻ የሆነችዉ አዲስ አበባን ጨምሮ በድንበር አካባቢ ምን እየተደረገ ይሆን?

ከሁለት ሳምንታት በፊት ከላይቤሪያ ወደናይጀሪያ ሄዶ አዉሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ ህመሙ አጣድፎት ሃኪም ቤት የተወሰደዉ የላይቤሪያ ዜጋ የበሽታዉ ምንነት እስኪጣራ ፋታ ሳይሰጥ ህይወቱን የነጠቀዉ ኤቦላ መሆኑ የተሰማዉ ካለፈ በኋላ እንደነበር አይዘነጋም። የሕመሙ ምንነት ከታወቀ በኋላም እሱን ተቀብሎ ያከመዉ ሃኪም ቤትና ያስታተሙ ሃኪሞች ለጊዜዉ ተገልለዉ ክትትል እንዲደረግባቸዉ ተወሰነ በዚህ መሃልም አንደኛዉ ዶክተር በአይምሬዉ የኤቦላ ተሕዋሲ መያዛቸዉ ትናንት ተረጋገጠ። በናይጄሪያዋ ሌጎስ ከተማ የኤቦላ ተሕዋሲ ህይወቱን ያሳጣዉን ላይቤሪያዊ በማከም ሂደት በቅርበት መገኘታቸዉ የተገለጸ በተሕዋሲዉ ሳይያዙ አልቀሩም በሚል የተጠረጠሩ ሰዎች ቁጥር ስምንት መድረሱም ተሰምቷል።

ይህ ተሕዋሲ ቀደም ሲልም ሴራሊዮን ዉስጥ ኤቦላ በተዛመተበት የገጠር አካባቢ ገብተዉ የህክምና ርዳታ ይሰጡ ከነበሩ ዶክተሮች የአንዱን ህይወት ነጥቋል። እንደዉም የእሳቸዉ ሞት ሌሎች የሀገሬዉ ዶክተሮች ላይ ባስከተለዉ ሽብርና ፍርሃት የተነሳ የራሳቸዉን ዜጎች ለመርዳት ችግሩ ወዳለበት አካባቢ እንዳይሄዱ እናደረጋቸዉ ተሰምቷል። በዘር በቀለም የማይመስሏቸዉ ምዕራባዉያን የድንበር የለሽ ሃኪሞች ባልደረቦችና የቀይ መስቀል የበጎ ፈቃድ አገልጋዮች ችግሩን ለመጋፈጥ መገደዳቸዉን መዘገባችን ይታወስ ይሆናል።

ኤቦላ የዝንጀሮ ሥጋን በመብላት የሚመጣ ያልተለመደ ተሕዋሲ ነዉ የሚሉና ችግሩን በርካታ የዝንጀሮ ዓይነቶች የሚገኙባት የአፍሪቃ ጣጣ አድርገዉ ለማየት የሚሞክሩ ቢኖሩም ኤቦላ ግን ሌሎቹንም የሚምር ዓይነት አልሆነም። ላይቤሪያ ዉስጥ የነበሩ ሁለት የአሜሪካን ዜጎች በቫይረሱ ተይዘዋል። ታማሚዎቹ ሳምራዉያን የተሰኘዉ ግብረ ሠናይ ድርጅት ባልደረቦች ሲሆኑ አንደኛዉ ዶክተር፤ ሌላኛዋ ደግሞ ወንጌላዊ ናቸዉ። ሁለቱንም ወደሀገራቸዉ በመዉሰድ በተገለለ ቦታ አቆይቶ የሚቻለዉን ሁሉ የህክምና እርዳታ ለማድረግ ዝግጅቱ መጠናቀቁም ተገልጿል። የጀርመኑ የሃምበርግ ዩኒቨርሲቲ ክሊኒክ በኤቦላ ተሕዋሲ የተያዙ ህመምተኞችን በልዩ ጥንቃቄ ባዘጋጀዉ የህክምና ክፍሉ ተቀብሎ ለማስታመም ዝግጁ መሆኑን ባለፈዉ ሳምንት መጨረሻ ቢያሳዉቅም እስካሁን ያመለከተ እንደሌለ ገልጿል። እንዲያም ቢሆን ዝግጁነቱን እንደተጠበቀ እንደሚሰነብት ነዉ ያመለከተዉ።

ከምስራቅ አፍሪቃ ሃገራት የበርካቶች መመላለሻ የሆኑት ኬንያንያ ኢትዮጵያም የየራሳቸዉን የጥንቃቄ ርምጃዎች ለመዉሰድ መዘጋጀታቸዉን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የአፍሪቃ ኅብረት መቀመጫነቷን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶችን በማስተናገዷ ወደሀገር የሚገቡትም ሆነ የሚወጡት ወገኖች እንቅስቃሴ እያደር እያደገ መምጣቱ የሚታይባት ሀገር ከሆነች ከራረመች። የአየር መጓጓዣዉ ብቻ ሳይሆን የደረቅ ወደብና ድንበር ግንኙነቶቿ ከሰዎች ከቦታ ወደቦታ የመዘዋወር ልማድ ማደግ ጋ ተገናኝቶም በአጎራባች ሃገራት የሚከሰተዉ ብቻ ሳይሆን ከቅርብ ርቀት የሚገኙትን የሚያሳስበዉ ችግር ሊደርስባት አይችልም ከማይባልበት ጊዜ ላይ የተደረሰ ይመስላል። እናም ካለፉት ወራት አንስቶ ምዕራብ አፍሪቃን ማስጨነቅ የጀመረዉ የኤቦላ ተሕዋሲ ባንድም ሆነ በሌላ መንገድ ሀገር ዉስጥ ቢገባ ሊደረጉ ስለሚገባቸዉ ጥንቃቄዎች የተባለ እና የተደረገ ነገር እንዳለ ለማወቅ ወደጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ደወልን። የኢትዮጵያ የማኅበረሰብ ጤና ተቋም ይህን በሚመለከት እየሠራ መሆኑ ተገልጾልን የተቋሙን የሕዝብ ግንኙነት አገኘናቸዉ በስልክ፤ አቶ አቤል የሻነህ፤ እስካሁን ጉዳዩን ይፋ ለማድረግ ጊዜ የወሰደበት ምክንያት በሽታዉን በተመለከተ የተረጋገጠ ምልክት ሀገር ዉስጥ ባለመታየቱ መሆኑንም አቶ አቤል ጨምረዉ ገልጸዋል።

ኤቦላ ከዚህ ቀደም ከተከሰተባቸዉ ሃገራት አንዷ ምሥራቅ አፍሪቃ ዉስጥ የምትገኘዉ ዩጋንዳ ናት። የዛሬ ሁለት ዓመት ሐምሌ ወር ዉስጥ በሽታዉ መቀስቀሱ ይታወሳል፤ በምዕራብ አፍሪቃ አራት ሃገራት ካለፈዉ የካቲት ወር ጀምሮ የኤቦላ ተሕዋሲ መታየትና ጉዳት ማድረስ ከጀመሮ አንስቶም ዩጋንዳ አብራ እየተጠቀሰች ትገኛለች። የጤና ጥበቃ ሚኒስቴሯ ግን ለጊዜዉ በዚህ ወቅት የታየ ነገር አለመኖሩን እየገለጸ ነዉ። ዩጋንዳ ከደቡብ ሱዳን ባላት ቀጥታ የድንበር ጉርብትና እና የሰዎች የመንቀሳቀስ ባህሪ አኳያ ተሕዋሲዉ እዚያ ቢታይ ወደደቡብ ሱዳን ለመሻገር የሚገደዉ አይመስልም። በአሁኑ ወቅት ደግሞ በርካታ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ወደኢትዮጵያ ምዕራባዊ ግዛቶች እየገቡ መሆኑ በተደጋጋሚ ይነገራል። በኢትዮጵያም ሆነ በአብዛኛዉ የአፍሪቃ ባህል የታመመ ወዳጅ ዘመድን በርቀት ሳይሆን በቅርበት እየዳበሱ ማስታመም የኖረ ጉዳይ ነዉ። ኤቦላ ተሕዋሲ ደግሞ የታማሚዉን ሰዉ አካልና ከሰዉነቱ የሚወጣ ማንኛዉንም ፈሳሽ በመንካት እንደሚተላለፍ ነዉ በተደጋጋሚ የሚገለፀዉ፤ ምልክቱ ያለበት ሰዉ ቢያጋጥም ሰዎች ምን ዓይነት ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸዉ ኅብረተሰቡ በሚደርሰዉ መንገድ በራዲዮም ሊሆን ይችላል መመሪያ ተላልፎ ይሆን?

የኤቦላ ተሕዋሲ ወረርሽኝ ስጋት ቀደም ሲል ለመጠቆም እንደተሞከረዉ በምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት ብቻ አልተወሰነም። ስዑድአረቢያ ሰሞን ወደሴራሊዮን ተጉዞ የነበረ አንድ ዜጋዋ ከበሽታዉ ምልክቶች አንዳንዱ ስለታየበት ለብቻ ገለል አድርጋ ህክምናና ምርመራ መጀመሯ ዛሬ ተሰምቷል። የ40 ዓመቱ የሳዉዲ ዜጋ ለንግድ ጉዳይ ነበር ወደምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር የተጓዘዉ ሲመለስ ግን በኤቦላ ተሕዋሲ የተያዘ ሰዉ የሚያሳየዉ ዓይነት ከፍተኛ ትኩሳት እንደገጠመዉ ነዉ የተነገረዉ። ጄዳ በሚገኝ ሃኪም ቤት ዉስጥ አሁን ገለል ተደርጎ የህክምና እርዳታ እየተደረገለት የሚገኘዉ ሰዉ ደም ከዓለም የጤና ድርጅት ጋ በመተባበር ወደሚሠራ ዓለም ዓቀፍ ቤተ ሙከራ ለምርመራ ተልኳል።

ኤቦላ ተሕዋሲ በከፍተኛ ትኩሳት ጀምሮ፣ ማስቀመጥና ማስመለስን ያስከትልና ሲጠናም ከተለያዩ የሰዉነት ክፍሎች መድማትን ያስከትላል። ዓለም ዓቀፍ የልማት ባንክ የዚህን ተሕዋሲ ወረርሽኝ ለመግታት ለሶስት ምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት ማለትም ላይቤሪያ ሴራሊዮንና ጊኒ የ260 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለመስጠት ተዘጋጅቷል። ባለፈዉ ሳምንት ዓርብ ዕለትም እንዲሁ የዓለም የጤና ድርጅት ይህንኑ ተሕዋሲ ለመዋጋት ያዘጋጀዉ እቅድ 100 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ አመልክቷል።

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic