ኤቦላን ለመከላከል የዘገየዉ ርምጃ ዋጋ ማስከፈሉ | ጤና እና አካባቢ | DW | 19.05.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

ኤቦላን ለመከላከል የዘገየዉ ርምጃ ዋጋ ማስከፈሉ

በአንድ ሀገርም ሆነ ድንበር ተሻግሮ ለሚዳረስ ወረርሽኝ አስፈላጊዉን የህክምና ድጋፍና የባለሙያ ምክር ማቅረብ የሚጠበቅበት የዓለም የጤና ድርጅት፤ የኤቦላ ወረርሽኝ ምዕራብ አፍሪቃ ዉስጥ እንደታየ ርምጃ ለመዉሰድ ዘግይቷል በሚል የሰላ ትችት ቀርቦበታል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:48
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:48 ደቂቃ

ኤቦላን ለመከላከል የዘገየዉ ርምጃ ዋጋ ማስከፈሉ

ድርጅቱ ጉድለቱን ቢቀበልም በበጀት እጥረት የሠራተኞቹ ቁጥር መቀነሱ ለርምጃዉ መዘግየት ከምክንያቶቹ አንዱ መሆኑን እያመለከተ ነዉ።

በምዕራብ አፍሪቃ ዉስጥ ባሉ ሃገራት በጎርጎሪዮሳዊዉ 2013ዓ,ም ታህሳስ ወር ላይ ነበር የመጀመሪያዎቹ የኤቦላ ተሐዋሲ ታማሚዎች የታዩት። ሲጀመር ወረርሽኙ የተቀሰቀሰዉ በጊኒ የገጠር ቀበሌዎችና መንደሮች ነነር። የጊኒዉ የጤና ችግር ብዙም ተነግሮለት ሳይበርድ ወደጎረቤት ላይቤሪያ ብሎም ሴራሊዮን የመዛመቱ ወሬ ተሰማ። የሕክምና አገልግሎት ባልተስፋፋባቸዉ የገጠር መንደሮች የተከሰተዉ ፍቱን መድኃኒት እስካሁን ያልተገኘለት የኤቦላ ወረርሽኝ ወትሮ በማዕከላዊ የአፍሪቃ ሃገራት አካባቢ በተለያዩ ጊዜያት መነሳቱ ነበር የሚታወቀዉ። ኤቦላ ወደምዕራብ አፍሪቃ የተዛመተበት መነሻ ምክንያት በትክክል ባይታወቅም የከፋ ጉዳት ከማድረሱ አስቀድሞ የዓለም የጤና ድርጅት WHO አፋጣኝ ርምጃ ባለመዉሰዱ የሰላ ትችት አስከትሎበታል። አንድ ገለልተኛ የምሁራን ስብስብ ያካሄደዉ ጥናት ድርጅቱ ወረርሽኙን ለመከላከል ዳተኝነት አሳይቷል ሲል ነዉ ከቀናት በፊት የወቀሰዉ። ዘገባዉ ለዓለም ይፋ ይሆናል አይሆንም ሲባል ቆየና ግን ይፋ ሆነ። WHOም ተገቢዉን ርምጃ ለመዉሰድ ረዥም ጊዜ የወሰደበት ምክንያቱን እንዲያብራራም የጥናቱ አቅራቢዎች በይፋ ጠየቁ።

የዓለም የጤና ድርጅት የኤቦላ ወረርሽኝ አፋጣኝ ርምጃና ጥንቃቄ የሚያስፈልገው አደገኛ ወረርሽኝ መሆኑን ለዓለም ይፋ ያደረገዉ በነሐሴ ወር ነዉ። በሽታዉ ጊኒ ዉስጥ ሰዎችን መግደል መጀመሩ በተሰማ ከስድስት ወራት በላይ ጊዜ ወስዶ ማለት ነዉ። ድርጅቶ ቶሎ እርምጃ እንዲወሰድ የኃላፊነት ድርሻዉን ተወጥቶ ቢሆን ኖሮ ወረርሽኙ በአንድ ሀገር ማለትም ጊኒ ዉስጥ በአስርና ሃያ የሚገመቱ ሰዎችን በመግደል ባበቃ፤ ወደሌሎች ጎረቤት ሃገራት ተዛምቶ በጥቅሉ ከ11ሺህ በላይ ሕይወት ባልቀጠፈ ነበር። ከ26 ሺህ የሚልቁትም በኤቦላ ተሐዋሲ ባልተለከፉ ነበር የሚለዉ ቁጭትም ጄኔቫ ላይ ዓመታዊ ጉባዉን በሚያካሂዱዉ የዓለም የጤና ድርጅት ስብሰባ ላይ ከፍተኛ የመነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኗል። ከየአቅጣጫዉ ወቀሳዉ የጠናባቸዉ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ማርጋሬት ቻን፤ ድርጅቱ መዘናጋቱን አልካዱም። ለዚህ ያበቃዉ ግን ከሁለት ዓመታት በፊት በገጠመዉ የበጀት እጥረት ሰበብ የሰዉ ኃይል መቀነሱ መሆኑ ግልፅ እንዲሆን ለማስረዳት ሞክረዋል። ከእንግዲህም በቂ ዝግጅት ሳይደረግ እንዲህ ያለ ወረርሽኝ ተከስቶ የሰዎችን ሕይወት እንዳያጠፋ ድርጅቱን በተገቢዉ መንገድ ከወዲሁ ማደራጀት እንደሚገባ ለአባል ሃገራትና ተሳታፊዎች አመለከቱ።

«ድርጅቱ ከእንግዲህ እንዲህ ያለ ፈታኝ አጋጣሚን መቋቋምና ማስተካከል የሚችልበት፤ በሰዉ ኃይልም ሆነ በበጀት ወይም በአስተዳደራዊ መዋቅር በቂ ዝግጅት ሳያደርግ ከሁኔታዎች ጋ ሲጋፈጥ ለማየት በፍፁም አልሻም። አልፈልግምም።»

የኤቦላ ወረርሽኝ ያስከ ተለዉን ጉዳትና ችግሩ በተከሰተባቸዉ ሃገራት የተፈጠረዉን የጤና፤ የማኅበራዊ ሕይወትና የኤኮኖሚ ምስቅልቅል በመጥቀስ ዘጋቢዎች ለመፍትሄ ፈጥኖ አልተንቀሳቀሰም የሚል ትችል የቀረበበትን ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ከስልጣንዎ በፈቃዳቸዉ ይነሱ ይሆን በማለት ጠየቁ። ቻን ለምላሽ አልዘገዩም« በፍፁም አይደረግም» አሉ። ባይሆን ኃላፊነት እንደሚሰማዉ መሪ ካለፈዉ ስህተት ተምረዉ ለወደፊት ትክክለኛ ስልት መንደፍ አቋማቸዉ መሆኑን ተናገሩ። የእሳቸዉን ምልሽ የተጋሯቸዉ ጥቂት አይደሉም። ዋናዉ ከስህተት መማር ነዉና። በትናንትናዉ ዕለት ለጉባኤዉ ንግግር ያደረጉት የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልም እንዲሁ ያለፈዉ ስህተት መማሪያ እንዲሚሆን ነዉ ያሳሰቡት።

«ምዕራብ አፍሪቃ ዉስጥ የደረሰዉ የኤቦላ ጥፋት እንዲህ ባለዉ የቀዉስ ወቅት አፋጣኝ ዓለም ዓቀፍ ርምጃ የመዉሰድን አስፈላጊነት እያመመንም ቢሆን እንድንረዳዉ አድርጎናል። 26 ሺ ሰዎች በተሐዋሲዉ ተይዘዋል። 11ሺዎች ደግሞ ሞተዋል። በበሽታዉ የተጠቁት ሃገራት ደግሞ በከፍተኛ ምስቅልቅል ዉስጥ መሆናቸዉን ተረድተዋል። ያለን አንድ የስኬት ዜና ላይቤሪያ ከኤቦላ ነፃ መሆኗ ነዉ። በሌሎቹ ችግሩ በጠናባቸዉ ሃገራትም ተመሳሳይ ሁኔታ እንደሚኖር ተስፋ እናደርጋለን። ከበሽታዉ ጋ በምናደርገዉ ዉጊያ የምናሸንፈዉ በተሐዋሲዉ የሚያዝ አዲስ ታማሚ ከሌለ ነዉ። ሆኖም ግን በትክክል አሸናፊዎች የምንሆነዉ ቀጣይ ለሚመጣብን ቀዉስ አስቀድመን ከተዘጋጀን ብቻ ነዉ። ከዚህ ቀዉስ ተምረናል። እናም ሁሉም ሊቀስመዉ የሚገባዉ ትምህርትም አስቀድመን ርምጃ መዉሰድ እንደሚኖርብንና ለዚህም ምን ማድረግ ይገባናል ብለን መጠየቅ ነዉ።»

የዓለም የጤና ድርጅት በተለያዩ የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት የተከሰተዉና በተለይ ግን በሶስቱ ማለትም በጊኒ፣ ሴራሊዮንና ላይቤሪያ ለጠናዉ የኤቦላ ተሐዋሲ መዛመት ምክንያት የሆነዉ የአቅም ማነስ እክሉ እንደሆነ ነዉ ለማሳየት የሞከረዉ። በእርግጥ ድርጅቱ ከ1,000 የሚበልጡ ሠራተኞቹን በተጠቀሱት ሃገራት አሰማርቷል። ፈጥኖ ተገቢዉን ርምጃ በመዉሰዱ ላይ ግን ዘግይቷል አለያም ዳተኝነት አሳይቷል የሚለዉ ትችት የድርጅቱን አስተዳደራዊ መዋቅር በገንዘብም ሆነ በሰዉ ኃይል የማጠናከርን አስፈላጊነት ነዉ ያመላከተዉ።

Deutschland Merkel bei der Weltgesundheitsversammlung

መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል

የዓለም የጤና ድርጅትከ150 ከሚበልጡ ሃገራት የተዉጣጡ ከ7000 በላይ ሠራተኞች እንዳሉት ይገልጻል። እነዚህንም የድርጅቱ ጽሕፈት ቤቶች በሚገኙባቸዉ በ150 ሃገራትና አካባቢዎች አሰማርቷል። ማሌዢያ የሚገኘዉ የድርጅቱ ዓለም አቀፍ ማዕከል እና ስዊዘርላንድ ጄኔቫ የሚገኘዉን ዋና ጽሕፈት ቤቱን ጨምሮ ማለት ነዉ። በዚያም ላይ የሕክምና ዶክተሮች፤ የጤና ጉዳይ ተመራማሪዎች፤ ጠበብትንና የድንገተኛ ወረርሽኝ በሽታ አጥኚዎች፤ እንዲሁም የሠለጠኑ የጤና ጉዳይ መረጃ ሰብሳቢዎች፤ የኤኮኖሚ ባለሙያዎችና የአስቸኳይ ጊዜ የእርዳታ ሠራተኞችንም ያቀፈ ግዙፍ ተቋም ነዉ። ገንዘብን ጨምሮ አስተዳደራዊ ተግባራትን የሚያከናዉኑ አባላትም አሉት። እንዲያም ሆኖ ከአንድ ዓመት በፊት የተከሰተዉ የኤቦላ ወረርሽኝ በሰዉም ሆነ በሃገራት ኤኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከማስከተሉ አስቀድሞ የመቆጣጠሩን ርምጃ ማፋጠን የተሳነዉ ባለዉ የመዋቅር ድክመት መሆኑ ነዉ አፅንኦት የተሰጠዉ። ጄኔቫ ላይ የተሰባሰቡት የድርጅቱ 180 የሚሆኑ አባል ሃገራትና ጉዳዩን በመከታተል ድክመቱን አጉልተዉ ያወጡት ባለሙያዎችም የድርጅቱ አቋምና አቅም የሚስተካከልበትን ስልት መቀየስ እንደሚያስፈልግ ተማምነዋል። ሜርክልም ይህንኑ በንግግራቸዉ ለመጠቆም ሞክረዋል።

«ለዚህም ዓለም አቀፍ ዕቅድ ያስፈልገናል። የዓለም የጤና ድርጅትም በዚህ ረገድ ማዕከላዊ ሚና ይጫወታል። ከዓለም የጤና ድርጅት ምን እንጠብቃለን? ድርጅቱስ ምን ማድረግ ይኖርበታል? በዚህ ድርጅት ዉስጥ የሚሰሩ አባል ሃገራትስ ድርሻቸዉ ምንድነዉ? በእኔ እይታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጤናን ለሚመለከቱ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የሚችል ብቸኛዉ ሕጋዊ ተቋም የዓለም የጤና ድርጅት ነዉ። ለዚህም መዋቅሩን ዉጤታማ በሆነ መንገድ ማስተካከል የሚገባዉ።»

ችግሩን መኖሩን ሳያንገራግሩ የተቀበሉት ዳይሬክተሯ ማርጋሬት ቻን በኃላፊነት የሚመሩት ድርጅት በያዝነዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ለአስቸኳይ ጊዜ የጤና ችግሮች አፋጣኝ ምላሽ መስጠት በሚችል መንገድ የመዋቅር ማስተካከያ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል። በድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ለሁለተኛ ጊዜ እስከጎርጎሪዮሳዊዉ 2017 ሰኔ ወር መጨረሻ ድረስ እንዲያገለግሉ ከሶስት ዓመት በፊት በድጋሚ የተመረት ቻን በቂ የበጀት ድጋፍ ከኖራቸዉ፤ የድርጅቱን የአደጋ ጊዜ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ይበጃሉ ያሏቸዉን መሠረታዊ የሚሏቸዉ ለዉጦችንም እንዲህ ዘረዘሩ፤

WHO Direktorin Margaret Chan zu Ebola Trendwende 25. Jan. 2015

ማርግሬት ቻን

«የሚከተሉትን አምስት ለዉጦች አደርጋለሁ፤ ተጠሪነቱ ለእኔ የሆነ የተቀናጀ የዓለም የጤና ድርጅት ድንገተኛ የጤና መርሃግብር እፈጥራለሁ፤ ከሌሎች ለምላሽ መስጠቱ ተባባሪ ከሆኑ አካላት ጋ የሚተሳሰር በግልፅ የመርሃግብሩን ተግባር የሚመዝን ስርዓትም አበጃለሁ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለድንገተኛ የጤና እክል የሚንቀሳቀስ የሰዉ ኃይልም አደራጃለሁ፤ በተጨማሪም ለድንገተኛ ችግር ምላሽ ለመስጠት እንዲችሉ የማዕከልና ለዘመቻዉ የሚሰማሩ ሠራተኞቻችንን አቅም በስልጠና አጠናክራለሁ። ከዚህም ሌላ አፋጣኝ እና ዉጤታማ ምላሽ የሚሰጥ የአሠራር ሂደትንም እየነደፍኩ ነዉ። እናም በአዲስ መልኩ 100 ሚሊዮን ዶላር የመጠባበቂያ የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግልንም ሃሳብ አቅርቤያለሁ። »

ማርግሬት ቻን ከ8ዓመት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ለድርጅቱ ዳይሬክተርነት ከመመረጣቸዉ አስቀድሞ በWHO ዉስጥ የተላላፊ በሽታዎችና ኢንፍሉዌንዛን የሚከታተለዉ ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተርነት አገልግለዋል። እናም የኤቦላ ወረርሽኝ ሳይታሰብ ባስከተለዉ መዘዝ ድርጅቱ መደናገጡን ግን አልካዱም። እንደእሳቸዉ አገላለፅም በድርጅቱ የ70 ዓመታት ታሪክ ከገጠሙት ፈተናዎች ሁሉ ይህ በአስር እጅ እጥፍ የላቀ ነዉ።

Liberia Ebola Impfung Versuch

የኤቦላ ክትባት ሙከራ

ላለፉት ከ16 ወራት በላይ ዓለም ያሳሰበዉና ያስጨነቀዉ የኤቦላ ተሐዋሲ ወረርሽኝን ስርጭት በተገቢዉ ፍጥነት ለመቆጣጠር ያልተቻለበት ምክንያት ከዓለም የጤና ድርጅት የመዋቅር ዝርዝርክነት በተጨማሪ በሽታዉ የተከሰተባቸዉ ሃገራት ማሕበራዊ የኑሮ ሁኔታም ትልቅ ሚና መጫወቱ አልተካደም።

ቻን አክለዉ ከ180 ሃገራት ለተዉጣጡት ወደ3000 የተገመቱት የጉባኤዉ ተሳታፊዎች በአሁኑ ጊዜ በኤቦላ በተጎዲት ሶስት ሃገራት ዉስጥ አንድ ሺህ የድርጅቱ ሠራተኞች መሰማራታቸዉን ገልጸዋል። ምንም እንኳን ባለፈዉ እሁድ ላይቤሪያ ዉስጥ እስከዛሬ አዲስ በተሐዋሲዉ የተያዘ ሰዉ ባለመኖሩ፤ ከኤቦላ ነፃ የመሆኗ የምስራች ቢነገርም አሁንም ግን ሴራሊዮንና ጊኒ ዉስጥ በኤቦላ የተያዙ አዳዲስ ሰዎች መኖራቸዉ እየተነገረ ነዉ። ካለፈዉ ሳምንት ወዲህ ብቻም በሁለቱ ሃገራት ዘጠኝ ሰዎች በኤቦላ መያዛቸዉ ተረጋግጧል። ላይቤሪያ ግን 42 ቀናት የሚዘልቀዉን ከተሐዋሲዉ ነፃ መሆኗን የማረጋገጫ ቀን አንድም አዲስ ታማሚ ወደሃኪም ቤት ባለመምጣቱ በሰላም አሳልፋለች። ጊኒና ሴራሊዮን ዉስጥ ለአዳዲስ ታማሚዎች መገኘት ምክንያት የሆነዉ ባህላዊዉ የቀብር ስርዓት መሆኑን ዘገባዎች ያመለክታሉ። በዚህ ምክንያትም በቅርቡ እነዚህ ሃገራት ከተሐዋሲዉ ነፃ የመሆናቸዉ ነገር ግን ገና የለየት አይመስልም።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic