ኤርትራውያን ተገን ጠያቂዎች በጀርመን እና ስሞታቸው | አፍሪቃ | DW | 20.07.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ኤርትራውያን ተገን ጠያቂዎች በጀርመን እና ስሞታቸው

ኤርትራውያን ትርጁማኖች የተገን ጠያቂዎችን ሃሳብ በተሳሳተ መንገድ እየተረጎሙ መሆኑን በጀርመን የስደተኞች ቡድን አስታወቀ። አንዳንዶቹ ፣ስደተኞቹ የደረሰባቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዳይናገሩ እንደሚያስፈራሯቸው የዶቼቬለው የቤንያሚን ናይት ዘገባ ያስረዳል ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:21
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:21 ደቂቃ

ኤርትራውያን ተገን ጠያቂዎች በጀርመን እና ስሞታቸው

«በእስር ቤት የተሰቃየሁበትን የገለጽኩበት የታለ ሲል ጠየቀን። እንደእሱ የሚል የለም አልነው። እጅግ በጣም ደነገጠ።»

በፍራንክፈርት አንድነት ለኤርትራ (United for Eritrea) የተሰኘው የግብረ-ሰናይ ማህበር ተባባሪ መስራች ሩት ባህታ እንዲህ አይነት በርካታ ታሪኮች አሏቸው። ማህበራቸው ለአዳዲስ ስደተኞች እገዛ ከማድረግ ባሻገር የጀርመን ባለስልጣናት በጀርመንኛ ብቻ የሚያቀርቡትን የተገን ጠያቂዎች ቃል ወደ ትግሪኛ መልሶ የመተርጎም ስራ ይሰራል።በዚህ ወቅት መንግስት በትርጁማንነት ባስቀመጣቸው ሰዎች በስህተት የተተረጎሙ አሊያም ሆን ተብለው የተዘለሉ ጉዳዮች እንደሚገኙ ሩት ባህታ ይናገራሉ።

«በመጀመሪያ ፈጽሞ ማመን አልቻለም። እንደገና የሚተረጉም ሶስተኛ ሰው ማግኘት ይኖርብናል። ሱዳንና ሊቢያን በመሳሰሉ ሃገሮች ነበር። በዚያ ምን እንዳጋጠመው ማንም አልጠየቀውም። አውሮጳ ሲገባ የመጀመሪያው በመሆኑ ሁሉም ነገር በትክክል ይሰራል ብሎ ጠብቆ ነበር። በጣም ደንግጧል። በተቋሙም እጅግ ተበሳጭቷል።»

ትንሽ መንግስት-በጀርመን

በሩት ባህታ እምነት በጀርመን እጅግ በርካታ ኤርትራውያን የመኖራቸውን ያህል ለተገን ጠያቂዎቹ ከሚመደቡት መካከል አንዳንዶቹ ትርጁማኖች ለጨቋኙ የኤርትራ መንግስት ታማኝ በመሆናቸው ሆን ብለው በተሳሳተ መንገድ ይተረጉማሉ፤ተገን ጠያቂዎችንም ያሸማቅቃሉ።

ብዙዎቹ ከኤርትራ ኤምባሲ ገንዘብ ይከፈላቸዋል ብለው ይጠረጥራሉ ። ሩት ባህታ በገንዘብ እንኳ ባይሆን አንዳች ጥቅም ሳያገኙ አይቀርም ብለው ያምናሉ። አብዛኞቹ ወደ ጀርመን የሚጓዙ ስደተኞች ከኢሳያስ አፈወርቂ ርቀናል ብለው ቸል ብለዋቸው ነበር። ሩት ባህታ ግን «ኤምባሲው በጀርመን እንደሚገኝ አነስተኛ መንግስት ነው።» ይላሉ።
አንዳንድ ጊዜ «የአፍሪቃ ሰሜን ኮሪያ» የሚል ስም ባተረፈችው ኤርትራ ያለው የሰብዓዊ መብት ይዞታ በዓለም የከፉ ከሚባሉት አንዱ ነው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሰኔ ወር ያወጣው ዘገባ ኤርትራ« የዜጎቿን እንቅስቃሴና ሃሳባቸውን ሳይቀር ትሰልላለች፤ ግለሰቦች በተከታታይ ያለበቂ ምክንያት ይታሰራሉ፤ይሰቃያሉ፤ይጠፋሉ ያለ ፍትሃዊ ዳኝነት ይገደላሉ።» ብሏል።

ድርጅቱ የሩት ባህታን ጥርጣሬም ይደግፋል። «የስለላ መዋቅሩ ከኤርትራ ውጪም በተለያዩ ሃገሮች የሚኖሩ ዜጎችን ለመቆጣጠር የሚሰራበት አደረጃጀት አለው።» ሲል የሰኔው የድርጅቱ ዘገባ ያትታል።

ይህ አስፈሪ ቢመስልም እውነት ነው። የኤርትራ ፖለቲካ ድንበር ተሻግሮ በጀርመን በሚገኙ በስደተኞች ውስጥ ሰርጎ ገብቷል። አንዳንድ ጊዜ ጊዜና ትውልድ ተሻግሮ በፖለቲከኞች የአባትና አያት ስም እየተከተለ ልጆችና ቤተሰቦችን ያድናል። በጎርጎሮሳዊው 1982 ወደ ጀርመን የገቡት የ68 አመቱ ጆብ ማሾ አልፎ አልፎ ስደተኞችን ሲረዱ የትርጆማኖቹን ጉዳይ በተደጋጋሚ ይሰማሉ።

«ለምሳሌ ነገሮችን በተፈጸሙበት ሁኔታ እንዳይናገሩ ይነግሯቸዋል፣የፖለቲካውን ሁኔታም እንዲህ ማለት አትችሉም፣ እንዲህ ነው ማለት ያለባችሁ ይሏቸዋል። በተቻላቸው መጠን አነስተኛ መረጃ እንዲሰጡ፤ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተቆርጠው እንዲቀሩ ለማድረግ ይሞክራሉ። የሚመጡት ስደተኞች በድህነት ምክንያት የተሰደዱ ተደርገው እንዲቆጠሩ ይፈልጋሉ።»

ሩት ባህታ በተገን ጥየቃ ችሎት ታድመው በሚሰሙትና በሚመለከቱት ከበቂ በላይ ተናደዋል።

«ችሎቱ በጣም አስቀያሚ ነው። ትርጁማኑ ተገን ጠያቂዎቹን ይቆጣቸዋል። እጅግ አስቀያሚ ነው። እኔ እዚያ በመገኘቴ ትርጁማኑ የተበሳጨ ይመስላል።» ሲሉ ሁኔታውን ያስረዳሉ።

ተገን ጠያቂ ኤርትራውያን ሸሽተውት ከመጡት መንግስት በሚደርስባቸው ጫና ተገደው ለመንግስቱ ማደር መጀመራቸውን ተመልክተዋል።

«ተረጋጉ የሆነ ነገር ማድረግ እንችላለን ብለን ስንነግራቸው ይገረማሉ። ተገን ጠያቂዎቹ በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ስለሚገኙ ትርጁማኖቹ ግን ብዙም አይቸገሩም።»

ችግሩ የጀርመን የስደተኞች ፌዴራል ቢሮ ፣የኤርትራውያን ማህበረሰብ ምን ያህል ፖለቲካዊ እንደሆነ አይገነዘብም። ለሁለተኛ ዲግሪ ማሟያ ሁኔታውን ሲያጠኑ የከረሙት ኤደን መንግስ ግን ሁኔታው ከሚገመተው በላይ የተቆላለፈ መሆኑን ይናገራሉ።

«የተገን ጠያቂዎቹ ችሎት የሚካሄደው ከፍተኛ ፖለቲካዊ ስሜት ባለው ሁኔታ ውስጥ ነው። አንዳንዶቹ ተገን ጠያቂዎች እዚህ ለመድረስ ከ5,200 ኪ.ሜ. በላይ ተጉዤ መጥቻለሁ። ሁኔታው ግን ተመሳሳይ ነው። ያለምንም ምክንያት ልታሰር አልችልም። ፍርሃቱ ግን አለ።ሲሉ ይናገራሉ።»

ትርጁማኖቹ ከተገን ጠያቂዎቹ ያገኙትን መረጃ ለኤርትራ ኤምባሲ አሳልፈው መስጠትና አለመስጠታቸውን የጀርመን ባለስልጣናት የሚከታተሉበት መንገድ የለም። መረጃውን የኤርትራ መንግስት የተገን ጠያቂዎቹን ቤተሰቦች ለመበቀልና ቅጣት ለማስከፈል ስለሚጠቀምበት ጉዳቱ ከፍተኛ መሆኑን ኤደን መንግስ ይናገራሉ።

«አንድ ሰው ካመለጠና መንግስት ይህንን ካወቀ በአገር ቤት የሚገኙ የስደተኛው ቤተሰቦች ሊታሰሩ ይችላሉ። የሚፈቱት ደግሞ በቅጣት መልክ ከፍተኛ ገንዘብ ከከፈሉ ይሆናል።»

አሁን የጀርመን መንግስት በኤርትራ ያለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ የከፋ በመሆኑ ማንም ተገን ጠያቂ በግዴታ የመመለስ ስጋት እንዳይኖርባቸው አስቧል። ይሁንና በደብሊን ስምምነት መሰረት መጀመሪያ ወደደረሱበት የአውሮጳ ህብረት አባል አገር ሊላኩ ይችላሉ። ለኤርትራውያኑ ደግሞ ጣልያን መሆኗን ሩት ባህታ ይናገራሉ።

«ሰዎች ወደ ኢጣሊያ ተመልሰው እየተላኩ ነው። የጀርመን መንግስት ከፍተኛ ጫና ማሳደር አለበት።»

የጀርመን መንግስት እንዲህ አይነት ችግር የለም ሲል ያስተባብላል። ዶይቼ ቨሌ ያነጋገራቸው የጀርመን የስደተኞች ፌዴራል ቢሮ ቃል አቀባይ ክሪስቶፍ ሳንደር በኢ-ሜይል በላኩት መልዕክት «አሁን እናንተ የገለጻችሁልን ችግር በኤርትራውያን ትርጁማኖች ዘንድ ስለመኖሩ የምናውቀው ነገር የለም። ከሌሎች ቅርንጫፎችም ይሁን የመረጃ ምንጮች ችግሩ አልተገለጠልንም።» ሲሉ መልሰዋል።

ቤንጃሚን ናይት/እሸቴ በቀለ

ሒሩት መለሠ

Audios and videos on the topic