ኤርትራና ኢትዮጵያ በሶማሊያ ግጭት | የጋዜጦች አምድ | DW | 03.01.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

ኤርትራና ኢትዮጵያ በሶማሊያ ግጭት

የኤርትራዉ የማስታወቂያ ሚኒስትር አሊ አብዶ በኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች ድጋፍ መቋዲሾ በደረሰዉ የሽግግር መንግስትና በእስላማዊዉ ንቅናቄ መካከል የሚካሄደዉ ግጭት በቀላሉ በድል ተጠናቀቀ ሊባል የማይችል በሚያረገርግ መሬት ላይ የተመሰረት ነገር ነዉ ሲሉ ዛሬ ለአዣንስ ፍራንስ ፕረስ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያዉያን ወታደሮች በሱማሊያ

ኢትዮጵያዉያን ወታደሮች በሱማሊያ

በኢትዮጵያ መንግስት የተወሰደዉ የጦር ጣልቃ ገብነት እርምጃም የዩናይትድ ስቴትስን ይሁንታ ያገኘ መሆኑን በመጥቀስ ቀጣዩ መዘዝ ሳይታይ የተከወነ ነዉ ሲሉ ኮንነዋል። በሌላ ወገን ኤርትራ ወታደሮች ወደሶማሊያ ምድር ማስገባቷ ሲነገር ከርሟል፤ ተንታኞችም በድንበር ዉዝግብ የሚነታረኩት ኤርትራና ኢትዮጵያ ሶማሊያን ሌላ የጦርነት መፋጠጫ መድረክ አድርገዋታል ይላሉ። በአፍሪቃ ቀንድ በሶማሊያ የሚታየዉ ሁኔታ ዉሎ ሲያድር አጎራባቾቹንም ሁሉ የሚያነካካ ችግር ሊያስከት ይችላል የሚለዉስጋት አሁንም አልቀነሰም።
ናይሮቢ የሚገኙት የሶማሊያ ጉዳይ ምሁር ማት ብራይደን ቀደም ሲል አሜሪካኖች ሶማሊያ ዉስጥ ለሚከወን ተግባር ተልዕኮዉ ተሳካ በሚል ባንዲራ ማዉለብለብ እንደማይቻል ተገቢዉን ትምህርት ቀስመዋል ይላሉ። በእርግጥ የቤት ስራዉ በኢትዮጵያ በኩል በመሰራቱና ሰላማዊ ዜጎች እምብዛም ሳይጎዱ ዉጤት በመታየቱ እፎይታ አግኝተዋል አሜሪካኖች፣ ሆኖም ግን ተጠናቋል ብሎ አፍሞልቶ ለመናገር አሁን ይከብዳል ይላሉ። ከዚህም ሌላ እሳቸዉም ሆኑ በርካታ የምስራቅ አፍሪቃ ጉዳይ ተንታኞች ከዚህ በተጨማሪ በሶማሊያ ምድር የሚታየዉ ግጭት ለድንበር ዉዝግባቸዉ እልባት ያላበጁት ኤርትራና ኢትዮጵያ ለራሳችዉ ችግር ተጨማሪ መፋጠጫ አድርገዉታል ይላሉ። የኤርትራዉ የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ አሊ አብዶ ግን ይህን አይቀበሉትም። ይህን በማስመልከት ለተጠየቁት ጥያቄ በሰጡት ምላሽም ችግሩን በቀጥታ ያያያዙት የኢትዮጵያ መንግስት አገር ዉስጥ ከገጠመዉ የፖለቲካ ቀዉስ ጋ ነዉ።
«የአዲስ አበባዉ አስተዳደር የህዝቡን ትኩረት በአገር ዉስጥ ካለዉ ችግር ለማዞር እየሞከረ ነዉ። ሶማሊያ ዉስጥ ያለዉ ጦርነት በአሜሪካና በሶማሊያ ህዝብ መካከል የሚካሄድ ጦርነት ነዉ። በእኛ በኩል ኤርትራ ሶማሊያን ከኢትዮጵያ ጋ የምትፋለምበት የጦር ሜዳ አድርጋ አይታት አታዉቅም። ለም? ለምን? ከኢትዮጵያ የሚያጋጨን የድንበር ችግር የለብንም። ያ ጉዳይ በዓለም ዓቀፉ የግልግል ኮሚሽን ከዥም ጊዜያት በፊት የተፈታ ችግር ነዉ። የቀረን ተግባራዊ ማድረግ ነዉ። እሱም ቢሆን የራሱ መንገድ አለዉ።»

የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ ወታደራዊ ኃይል በሶማሊያ ምድር እንደሌለዉ ቢገልፅም በቀጣይ በይፋ በጦርነቱ መግባቱን ገልጿል። ኤርትራም ወደሶማሊያ 2,000 ወታደሮችን ልካለች በሚል በተደጋጋሚ ተነግሯል። የኤርትራ ጥረትም እስላማዊ ሚሊሺያዎቹን ለመደገፍ ነዉ ይባላል ተባሉ አቶ አሊ። በእሳቸዉ አገላለፅ ኤርትራ እስላማዊ ሸንጎዉን በመደገፍ ወታደሮቿን ወደሶማሊያ እንዲዋጉ አላከችም፤ በቅርቡ በተካሄደዉ ዉጊያም የተገደለም ሆነ የተያዘ ኤርትራዊ ወታደር የለም።
«ኤርትራዉያንን ዳንሱር ላይ አግኝተናል ብለዉ ነበር። ቀጠሉና ደግሞ የለም ስማቸዉ ብቻ ነዉ ከስም ዝርዝር ዉስጥ የተገኘዉ አሉ። እንደገና ፓስፖርታቸዉን አገኘን አሉ፣ ከዚያ ደግሞ የለም ኤርትራዊ የሚባል አላገኘንም ግን ከኬንያ የሰማነዉ ዘገባ አለ አሉ። እና ነገሩ እንደዉ የመኝታ ሰዓት ተረት ዓይነት ነዉ።»

የተንታኞቹ ጨምረዉ እንደሚሉት በኢትዮጵያ ወታደሮች ከሚታገዘዉ የሽግግር መንግስት ጋር በከባድ ዉጊያ መፋጠጥን በመሸሽ የተበተኑት ኃይሎች ተከታታይ አደጋ ለመጣል ራሳቸዉን መልሰዉ ሊያደራጁ የሚችሉበት አጋጣሚ እጅግ የሰፋ ነዉ። አቶ አሊ አብዶም ዘግየት ብሎ ሁኔታዉ መከታተል ይበጃል ባይ ናቸዉ። በመቋዲሾ የጦር አበጋዞቹ ተመልሰዉ የተደራጁበትና ከተማዋም ወደቀዉስ መግባቷ ሁኔታም ሲታይ ሶማሊያ ተመልሳ እንዲህ በአጭር ጊዜ የተረጋጋች ትሆናለች ብሎ መገመት ይከብዳል። ሰላም አስከባሪ ኃይል መግባት የሚለዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኃሳብ እዚህ ጋ ሊታሰብ ይችላል። ዛሬ የተሰማዉ የኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ታጣቂዎች ያደረሱት ዓይነት አደጋ እንዳይቀጥል። ኤርትራ ደግሞ ወደሶማሊያ የኢጋድ ሰላም አስከባሪ ኃይል ይግባ የሚለዉን ከተቃወሙውት መካከል አንዷ ናት። በዳርፉርም እንዲሁ የካርቱሙን መንግስት በመደገፍ ሰላም አስከባሪ ኃይል የመግባቱን ሃሳብ አልደገፈችም። ሰላም አስከባሪን በተመለከተ አቋማቸዉን አቶ አሊ እንዲህ ነዉ የገለፁት

«እነዚህ አሁን የአዞ እንባ የሚያነቡት፣ እነዚህ ስለ ሰላም አስከባሪ መላክ የሚያወሩት ወገኖች በተደጋጋሚ ግጭቱን ለማቀጣጠል ለመቋዲሾ የጦር አበጋዞች መሳሪያም ሆነ ገንዘብ ሲያስገቡና ሲያፈሱ አንድ ቃል ያልወጣቸዉ ናቸዉ። ለምን? አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በሰላም አስከባሪ ስም ነዉ የሚፈፅሙት፥ ምክንያቱም ቀላል ነዉ፣ ያም የባልካን አካባቢ ሀገራት በዘርና በሃይማኖት ተለያይተዉ ሲያቆራቁስ የሚገኘዉን ዓይነት ችግር እዚህም በመፍጠር ሶማሊያ ስትበታተን ብች ጥቅማችን ይከበራል ብለዉ ስለሚያምኑ።»

ተዛማጅ ዘገባዎች