ኤልቪስ ፕሬስሊ እና ኢትዮጵያውያን አፍቃሪዎቹ | ባህል | DW | 21.08.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

ኤልቪስ ፕሬስሊ እና ኢትዮጵያውያን አፍቃሪዎቹ

በጎርጎሮሳዊው 1950 መጨረሻ እና በ60ዎቹ እንደ ኤልቪስ የሚለብሱ ፀጉራቸውን የሚፈሽኑ የሚደንሱ እና የሚዘፍኑ፣ኢትዮጵያውያን ወጣት ተማሪዎች ቁጥር ጥቂት የሚባል አልነበረም። ስሙ እንደ ቅጽል ስም ይሰጣቸው ከነበሩት መካከል ያኔ በኤልቪስ እና በሌሎችም እውቅ የውጭ ድምጻውያን ዘፈን ይታወቅ የነበረው ድምጻዊ ዓለማየሁ እሸቴ አንዱ ነበር ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:08
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
11:08 ደቂቃ

ኤልቪስ ሲታወስ

የሮክ ኤንድ ሮል ሙዚቃ ንጉሥ የሙዚቃ አዋቂዎች እና አድናቂዎቹ የሰጡት ማዕረጉ ነው፣ ዝናው ከሀገሩ አልፎ በመላው ዓለም ሲናኝ ጊዜ አልወሰደበትም፤ 40 ኛ ሙት ዓመቱ በዚህ ሳምንት አጋማሽ በሀገሩ እና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተዘክሯል። ከጎርጎሮሳዊው 1950ዎቹ አጋማሽ አንስቶ በሙዚቃው ዓለም ትልቅ ቦታ የሚይዘው አሜሪካዊው ዘፋኝ እና የፊልም ተዋናይ ኤልቪስ ፕሬስሊ።  በ20ኛው ክፍለ ዘመን ጎልተው ከወጡት የሙዚቃ ፈርጦች ዋነኛው ኤልቪስ ፣በዘመኑ፣ የወጣት ኢትዮጵያውያን የሙዚቃ አፍቃሪዎችን ቀልብ ከሳቡት የውጭ ዘፋኞች አንዱ ነበር። የዚያን ዘመን ወጣቶች እንደሚሉት ኤልቪስ ታዋቂ እና ተወዳጅ በነበረበት በ1950ዎቹ መጨረሻ እና በ60ዎቹ እንዲሁም በ70 ዎቹ  እንደ እርሱ የሚለብሱ ፀጉራቸውን የሚፈሽኑ የሚደንሱ እና የሚዘፍኑ በአጠቃላይ ርሱን መስለው ለመታየት የሚሞክሩ ወጣት ተማሪዎች ቁጥር ጥቂት

የሚባል አልነበረም። ስሙ እንደ ቅጽል ስም ይሰጣቸው ከነበሩት መካከል ያኔ በኤልቪስ እና በሌሎችም እውቅ የውጭ ድምጻውያን ዘፈን ይታወቅ የነበረው ድምጻዊ ዓለማየሁ እሸቴ ወይም ያኔ እንደሚጠራው ዓለማየሁ ኤልቪሱ አንዱ ነበር ። የቀዶ ጥገና ሐኪም እና ደራሲ ዶክተር ሰሎሞን ማሞ ከኤልቪስ አድናቂዎች አንዱ ናቸው። ዝክረ አዲስ አበባ የሚል ርዕስ የሰጡትን መፀሐፋቸውን በቅርቡ ለአንባብያን እንደሚያቀርቡ የተናገሩት ዶክተር ሰሎሞን በተማሩበት በአዲስ አበባው  ሽመልስ ሃብቴ በሚባለው ትምህርት ቤት አካባቢ ነው ተወልደው ያደጉት። የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ በነበሩበት ወቅት የኤልቪስን ዘፈኖች ማድመጥ ፊልሞቹንም ማየት ከምንም በላይ ያዝናናቸው ነበር። ያኔ እርሳቸው እና ጓደኞቻቸው ኤልቪስን ለመምሰል የማያደርጉት ጥረት አልነበረም። ከትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው ውስጥ በኤልቪስ የሚጠሩም ነበሩ።ኤልቪስ ፕሬስሊ ቱፔሎ ሚሲሲፒ በጎርጎሮሳዊው 1935 ነው የተወለደው። በ13 ዓመቱ ከቤተሰቡ ጋር በሄደባት በቴነሲዋ ሜምፊስ  በጎርጎሮሳዊው 1954 ወደ ሙዚቃው ዓለም ተቀላቀለ። በዚሁ ዓመት የመጀመሪያውን ነጠላ ዜማውን በ 19 ዓመቱ አወጣ። ከሁለት ዓመት በኋላ

Der äthiopische Sänger und Songwriter Alemayehu Eshete (Pablo Ruiz Holst)

ድምፃዊ አለማየሁ እሸቴ

 ሌላ ዜማ አሳትሞ በዩናይትድ ስቴትስ የሙዚቃ ሰንጠረዥ የመጀመሪያውን ቦታ ያዘለት ።በዚያው ዓመት  ለመጀመሪያ ጊዜ «ላቭ ሚ ቴንደር» በተባለው ፊልም ላይ ተወነ። እንዲህ እንዲህ እያለ ዝናው እያናኘ የሄደው ኤልቪስ በ1960ዎቹም በተዋናይነት ለተካፈለባቸው በርካታ ፊልሞች የተለያዩ ዘፈኖችን ተጫውቷል። ለ7 ዓመታት መድረክ ላይ ሙዚቃዎቹን  ማቅረብ ካቋረጠ በኋላ በ1968 እንደገና ወደ መድረክ የተመለሰው ኤልቪስ በሙዚቃ ቅጂ ሽያጭ ታሪክ ተወዳዳሪ አልነበረውም። ወደ 600 ሚሊዮን የሙዚቃ ቅጅዎቹ ተሽጠውለታል።  ለሙዚቀኞች የሚበረከተው የግራሚ ሽልማት ሦስት ጊዜ ተሰጥቶታል። በ36 ዓመቱ የግራሚ የህይወት ዘመን ሽልማት ለማግኘት የበቃም ድምጻዊ ነበር ።

ዘንድሮ የኤልቪስ 40 ኛ ሙት ዓመት በሙዚቃው ዝናን ባተረፈባት እና በተቀበረባት በቴነሲዋ ግዛት በሜምፊስ በዚህ ሳምንት አጋማሽ ብዙ አድናቂዎቹ በተገኙበት በተለያዩ ዝግጅቶች ተዘክሯል። በሌላው የዓለም ክፍልም በተለያዩ ስነ ስርዓቶች ታስቧል። ኤልቪስ ከሞተ 40 ዓመታት ቢቆጠሩም እስካሁን በአድናቂዎቹ ዘንድ ምትክ የሌለው ዘፋኝ ነው። ኤልቪስ በጎርጎሮሳዊው ነሐሴ 16 1977 ነበር በልብ ህመም ነው ያረፈው። ሙሉውን ዝግጅት የድምጽ ማዕቀፉን በመጫን ማዳመጥ ይችላሉ። 

ኂሩት መለሰ

ልደት አበበ

Audios and videos on the topic