«ኢኬያ» እና የእርዳታ ማሰባሰብ ርምጃው | አፍሪቃ | DW | 14.02.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

«ኢኬያ» እና የእርዳታ ማሰባሰብ ርምጃው

«ኢኬያ» በመባል የሚታወቀው የስዊድናውያኑ የመኖሪያ ቤት እቃዎች መሸጫ መደብር ከጥር 26፣ እስከ መጋቢት 20፣ 2006 ዓም ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ እርዳታ የማሰባሰብ ተግባር በማካሄድ ላይ ይገኛል።

እርዳታው የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎችን ለማሻሻል እና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ጥራት ለማሰደግ ይውላል ተብሎ ይጠበቃል።

«ኢኬያ» ከተባበሩት መግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን«ዩኤን ኤች ሲአር» ጋር በጋራ በጀመረው የእርዳታ ማሰባሰብ ተግባር መሠረት፣ «መብራት ለተሻለ መፃኤ-ዕድል» በሚል አላማ ከሚሸጠው ከያንዳንዱ የኤሌትሪክ ኃይል ቆጣቢ አምፑል አንድ ዩሮ ለእርዳታው ተግባር እንዲውል መድቦዋል። ከዚሁ ሽያጭ የሚሰበሰበው ገቢ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች የመብራት አገልግሎት እንዲያገኙ፣ በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ የመንገድ መብራቶች እዲተከሉላቸው፣ እንዲሁም፣ ታዳሽ የኃይል ምንጮች እንዲስፋፉላቸው ይረዳል። ኢትዮጵያን ጨምሮ ስደተኞችን የሚያሰተናግዱት ቻድ፣ ባንግላዴሽ እና ዮርዳኖስ የዚሁ እርዳታ ተጠቃሚ ይሆናሉ።

«የኢኬያ» የኮምኒኬሽንና የስልታዊ እቅድ አውጪው ክፍል ኃላፊ ጆናተን ሳበራኖት ለዶይቸ ቬለ እንደገለጹት፣ ይህ ርዳታ የብዙ ሕፃናትን ሕይወት ሊለውጥ ይችላል።

« የኢኬያ የርዳታ ድርጅት በድሃ አገሮች ለሚገኙ ሕፃናት የተሻለ የኑሮ ዕድል የመፍጠር አላማ ይዙ የተነሳ ነው። በዚሁ ተግባራችንም ላይ የስደተኞች ጉዳይ ከሚመለከተው የተባበሩት መግስታት ከፍተኛ ኮሚሽን «ዩኤን ኤች ሲ አር» ጋር ተባብረን እንሰራለን። ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ በዓለም ወደ 12 ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞች «ዩኤን ኤች ሲአር» በሚያስተዳድራቸው መጠለያዎች ውስጥ ይኖራሉ፤ ከነዚህም መካከል ስድስት ሚሊዮኑ ሕፃናት በመሆናቸው ነው። ታዲያ ይህ እርዳታ ለነዚህ ስደተኛ ሕፃናት ወደፊት የተሻለ ዕድል ለመፍጠር ያስችላል።»

በመጠሊያ ጣቢያዎች ውስጥ መኖር ቀላል ባይሆንም ፣ ሌላ አማራጭ የሌላቸው ስደተኞች እዚያ ለመኖር ይገደዳሉ። ለምሳሌ በአንዳንድ የስደተኞች መጠለያዎች ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ የመብራት አገልግሎት ማግኘት አይቻልም።

ስለዚህ፣ አሁን «መብራት ለተሻለ መፃኤ-ዕድል» በሚል ስም በመሰብሰብ ላይ ያለው እርዳታ የስደተኞቹን ኑሮ ለማሻሻል ድርሻ ሊያበረክት እንደሚችል የኮምኒኬሽንና የስልታዊ እቅድ አውጪው ክፍል ኃላፊ ጆናተን ሳበራኖት አመልክተዋል። ምን ያህል ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችልም ሲያስረዱ፣

«በመጀመሪያ ከማንኛውም ድርጅት ጋር በጋር በምንሰራበት ጊዜ የረጅም ጊዜ እቅድ ይዘን ነው፣ ለዚህም አብረናቸው ስለምንሰራቸው ሸሪኮቻችን የሚያሰፈልገውን ምርመራ አስቀድመን እናካሂዳለን። ታማኝ መሆናቸውን፣ ጥሩ ስራ መስራታቸውን እናጣራለን። ከዚያ በያዓመቱ አብረውን ለሚሰሩት ድርጅቶች የእርዳታውን ገንዘብ በመስጠት፣ ከኛ ጋር ባንድነት አንድ መርሐ-ግብር እንዲቀርፁ እንጠይቃለን፥ በዓመቱ መጨረሻም ስለተገኙ ውጤቶች እንወያያለን፣ ባለፉት 12 ወራት ያስመዘገቡትን ውጤትም እንዲያሳዩን እንጠይቃለን። ባጠቃላይ ሽርክና ከመጀመራችን በፊት ብዙ ጥናት እናደርጋለን፤ ከዛም ስራውን ቀስ በቀስ እንጀምራለን።» 

እንደ ጆናተን ሳበራኖት እንደገለጹት፣ እርዳታው በየትኞቹ መጠለያ ጣቢያዎች ስራ ላይ እንደሚውል «ዩኤን ኤች ሲአር» ይወስናል።

«መብራት ለትሻለ መፃኤ-ዕድል በሚል አላማ የሚሰበሰበው እርዳታ በአምስት አገሮች ውስጥ መብራት አገልግሎት እንደሚያስገኝ ተስፋ አለን፣ ኢትዮጵያም ከአምስቱ መካከል አንድዋ ነች። ርዳታው ለየትኛው አካባቢ ይበልጥ አስፈላጊ ነው የሚለውን ጉዳይ የሚወስነው የተባበሩት መግስታት የስደተኞት ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን «ዩ ኤን ኤች ሲአር» ይሆናል።»

ሙና ማሞ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic