ኢንዶኔዢያ፤ የመንገደኞች አውሮፕላን መሰወር | ዓለም | DW | 28.12.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ኢንዶኔዢያ፤ የመንገደኞች አውሮፕላን መሰወር

ከኢንዶኜዢያ ወደ ሲንጋፑር ሲበር የተሰወረው የኤር ኤዢያ የአየር መንገድ አውሮፕላን አሁንም የደረሰበት አልታወቀም። 155 መንገደኞችን እና 7 የበረራ ሠራተኞችን አሳፍሮ የነበረው አውሮፕላን በገጠመው መጥፎ የአየር ሁኔታ ምናልባትም ሳይከሰከስ እንዳልቀረ ተገምቷል። የአውሮፕላኑ ፍለጋ ለጊዜው ተቋርጧል።

የኤንዶኔዢያ ባለስልጣናት የተሰወረውን አውሮፕላን ፍለጋ ለጊዜው ማቋረጣቸውን እና ሌሊቱ ሲነጋ ሰኞ ጠዋት ፍለጋውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል። አውሮፕላኑ ከራዳር ከመሰወሩ በፊት አብራሪው ስለገጠመው መጥፎ የአየር ሁኔታ በመጥቀስ የበረራ መስመሩ እንዲቀየርለት ለበረራ ተቆጣጣሪ ክፍሉ ፍቃድ ጠይቆ እንደነበር አየር መንገዱ አስታውቋል። በዚህ ወቅት አውሮፕላኑ ቤሊቱንግ የተሰኘችው የኢንዶኔዢያ ደሴት አካባቢ ነበር። ከኤንዶኔዢያ ሱራባያ ወደ ሲንጋፑር ጃቫ በመብረር ላይ የነበረው ይኽ አውሮፕላን ከራዳር የተሰወረው ከመሬት ከተነሳ ከ45 ደቂቃ በኋላ ነበር። አውሮፕላኑ ውስጥ በብዛት ተሳፍረው የነበሩት ኢንዶኔዢያውያን መሆናቸው ተገልጿል። ኤር ኤዢያ የተሰኘው የአየር መንገድ ዋና መቀመጫ ማሌዢያ የሚገኝ ሲሆን፤ ከዓለም በርካሽነቱ ይታወቃል። የዚህ አውሮፕላን የደረሰበት አለመታወቅ ከ10 ወራት ገደማ በፊት 239 መንገደኞችን አሳፍሮ ከኩዋላ ላምፑር ወደ ቤጂንግ በበረራ ላይ የነበረው እና እስካሁን የገባበት ያልታወቀው MH 370 የተሰኘውን የማሌዢያ የአየር መንገድ አውሮፕላን አስታውሷል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ልደት አበበ

ተዛማጅ ዘገባዎች