ኢንተርኔትና የተሃድሶ ለውጥ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 07.05.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ኢንተርኔትና የተሃድሶ ለውጥ

የመረጃ ፤ የዕውቀት ማካማቻውና ማከፋፈያው ጋን ከተከፈተ ከጥቂት ዐሠርተ ዓመታት ወዲህ፤ የምርምር ውጤቶቻቸውን በኢንተርኔት ይፋ የሚያደርጉ ጠበብት ቁጥር እየጨመረ ሄዷል። ስለሆነም፤ ዕውቀትን ባፋጣኝና በቀላሉ ለመቃኘትም ሆነ ለመቅሰም የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩ የሚያጠራጥር አልሆነም።

በጀርመን መዲና በበርሊን በሩ የተከፈተው ሳይንስ «ሳይንስ ዖፕን» የተሰኘ የኢንተርኔት መድረክ ተከፍቷል። በተለያዩ የሳይንስ ዘርፎች የሚካሄዱ የምርምር ውጤቶችን ይፋ እንዲቀርቡ ድጋፍ የሚያደርጉት እጅግ ታዋቂዎቹ የጀርመን የሳይንስና ቴክኖሎጂ የምርምር ተቋማት ናቸው። እነርሱም፣ የጀርመን የምርምር ማሕበር ዶቸ(ፎርሹንግገማይንሻፍት) DFG ፣ የማክስ ፕላንክ የምርምር ተቋም፣ (ማክስ ፕላንክ የተማራማሪዎች ማሕበር)፣ ሄልምሆልትዝ የምርምር ማኅበረሰብ ፣ የፎልክስቫገን የምርምር ርዳታ ድርጅት፣ በሳይንስ ማሕበር የመገናኛ ብዙኀን መርጃ ማሕበር፤ የላይብኒትዝ የምርምር ማሕበርና የመሳሰሉ ናቸው።

ኢንተርኔት ለምርምር ውጤቶች ማሳወቂያ ክፍት መሆኑ ፤ ውጤቱም በፍጥነት የሚዳረስ መሆኑ ፣ ለሳይንስ ምርምር እገዛ አድርጓል ብለው የሚያምኑ ብዙዎች ናቸው። በሌላ በኩል፤ በኅትመት መልክ ይፋ የሚደረጉ ሥራዎች፤ ተንጓለው ተመርጠው የሚቀርቡ ናቸውና በዚህ ረገድ ጠቀሜታቸው በቀላል የሚገመት አይደደለም የሚሉ አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ስሕተት ቢኖር በኢንተርኔት እንደሚቀርቡ የምርምር ውጤቶች፤ የኅትመት የምርምር ሥራዎችን በቀላሉ ማረም እንደማይቻል ይታመንበታል።

የሳይንስ ምርምር ውጤቶች፤ በመሠረቱ ፣ በአጠቃላይ ፣ መረጃዎች በኢንተርኔት መቅረብ የጀመሩት ዓለም አቀፉ የመረጃ ማሠራጫ የኢንተርኔት አገልግሎት ሥራውን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ነው። ኢንተርኔት፣ ራሱ ዓለም አቀፋዊ በመሆኑ ፤ አብዛኛው የዓለም ሕዝብም ዘመናዊ የትምህርትና የመረጃ አገልግሎት ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማብቃት፤ አንድ ወይም የተወሰኑ ድርጅቶችም ሆኑ ሃገራት ብቻቸውን ሊቆጣጠሩት አይገባም የሚለው መከራከሪያ ሐሳብ ጠንከር ብሎ በመቀጠሉ በዛ ያሉ ዓለም አቀፍ ውክልና ያላቸው ወገኖች የመረጃ ቴክኖሎጂ ድርጅቶች ፣ የንግድ አካላት ፤ መንግሥታት፣ ፣የሲቭሉ ማሕበረሰብ ቡድኖችና የአካዳሚ ባለሙያዎች ፣ ዓለም አቀፍ የኢንተርኔትን አመራር እንዲረከቡ ባለፈው መጋቢት 15-18,2006 ዓ ም ሲንጋፑር ውስጥ በተካሄደው ዐቢይ ጉባዔ፤ ስምምነት ላይ መደረሱ የሚታወስ ነው።

ይህ ሊሆን የቻለው 15 ዓመታት ያህል፤ አያሌ መንግሥታት ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኮሚቴ፤ እንዲሁም ፣ የሲብሉ ማሕበረሰብ ተወካይ ቡድኖች ፣ ዩናይትድ ስቴትስን፤ የኢንተርኔቱን አስተዳደር የበላይ ተቆጣጣሪነት ትተው ዘንድ ሲወተውቱ መቆየታቸው የሚታበል አይደለም።

አሁን ፣ መሪ የኢንተርኔት ቁልፍ ስሞችን በመቆጣጠር ላይ የሚገኘው በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው ለትርፍ እንደማይሠራ የተነገረለት ድርጅት «ኢንተርኔት ኮርፖሬሽን ፎር አሳይንድ ኔምስ ኤንድ ነምበርስ» (ICANN ) በተሰጠው ኮንትራት መሠረት ፣ የውሉ ጊዜ እ ጎ አ በ መስከረም ወር 2015 ዓ ም ከማክተሙ በፊት ፤ አመራሩን አዲሱ ኮሜቴ ሳይረከብ አይቀርም።

የ ICANN ዋና ሥራ አስኪያጅ ፋዲ ቸኻድ፤ የዩናይትድ ስቴትስ ውሳኔ የኢንተርኔት አስተዳደር ከፖለቲካ ነጻ እንዲሆን የሚያበቃ ነው ይላሉ። የወደፊቱን የኢንተርኔት መረብ አመራር በተመለከተ በቅርቡ በሳዖ ፓውሎ ፣ ብራዚል ፣ «Net Mundial» በሚል መሪ ቃል ፣ ሰፋ ያለ የ 2 ቀናት ዓለም አቀፍ ጉባዔ ተዘጋጅቶ እንደተመከረበትም ታውቋል። ብራዚል በዚህ ጉዳይ ላይ እንዴት ግንባር ቀደም ሚና መያዝ ቻለች?

ብራዚል ሲባል በአሁኑ ወቅት፣ ማንም ፣ ምናልባት ትዝ የሚለው፣ እየተቃረበ የመጣው ፤ የዘንድሮው የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ሊሆን ይችላል። ወይም አገሪቱ የታወቀችበት የእግር ኳስ ጨዋታና ፣ ሀድ በሌለው ቦታ ቡና በማምረት የመሪነቱን ቦቦታ መያዟ፣ ወይም ደግሞ በሰፊው ግንባር ቀድም የባዮ ፊውል አምራችና ተጠቃሚ ናት መባሉም ሌላው ዐቢይ ጉዳይ ነው።

ከአዳጊ ሃገራት ላቅ ያለ እመርታ በማሳየት ፣ በታላቅ የዕድገት ጎዳና ላይ ከሚገኙትና በእንግሊዝኛው ምህፃር፤ BRICS በመባል ከታወቁት 5 አገሮች አንዷ የሆነችው ብራዚል፣ በኤኮኖሚም በፖለቲካው መስክም የቆየው የተወሰኑ አገሮች ዓለም አቀፍ ተጽእኖ ማክተም አለበት ብለው ከሚያምኑትና ከሚታገሉትም መካከል አንዷ ናት። «ብሪክስ» የሚባሉት አገሮች ባለው ሁለንታናዊና ወቅታዊ ዓለም አቀፍ ሥርዓት የተንገሸገሹ የሚመስሉ መሆናቸውም ነው የሚገርላቸው። የፖርቱጋል-እስፓኝና አሜሪካ ግንኙነት የምርምር ተቋም ኀላፊ ፒተር ቢርለ እንደሚሉት ከሆነ 5ቱ እመርታ በማሳየት ላይ የሚገኙት ሃገራት ፤ ማለትም ፤ህንድ ፤ ብራዚል ፣ ህንድ ፣ደቡብ አፍሪቃ ፣ ቻይናና ሩሲያ እ ጎ አ ከ 1945 ዓ ም ወዲህ ተንሠራፍቶ የቀጠለው፣ ዩናይትድ ስቴትስ በቁንጮነት የመሪነቱን እርፍ የጨበጠችበት የዓለም ሥርዓት መስተካከል ይኖርበታል። ከዚህም መካከል አንዱ የኢንተርኔት አመራር ነው። ፒተር ቢርለ፣ እንዲያውም «ብሪክስ» የተፈጠረበት ምክንያት የዓለም አቀፉ የአመራር ሥርዓት ያልጣማቸው ወገኖች በመገኘታቸው ነው ባይ ናቸው። እንዲያውም የሩሲያ ከ ቡድን 8 መገለል ለሚዛኑ ይበጃል ያሉበትን ምክንያት እንዲህ ያብራራሉ።

2,«ሩሲያ ከ ቡድን 8 ከአነአካቴው ተገልላ ብትቀር ፣ ሌላ መድረክ በመሻት ፤ ከዚህ ቀደም ከነበረው በላቀ ሁኔታ ከ«ብሪክስ » ጋር ያለውን ግንኑነት ይበልጥ እንዲጠናከር ታደርገዋለች። የዩክሬይንን ጉዳይ በተመለከተ ከአውሮፓው ሕብረት ይልቅ ቆጠብ ያለውን አካሄድ የመረጡ የ«ብሪክስ» አባላት ነበሩ።በአሁኑ ጊዜ ግምት ሊመስል ይችላል፤ ይሁንና ሂደቱ የብሪክስን ደረጃ ይበልጥ ከፍ ወደሚያደርግ ሁኔታ ሊመራ ይችላል።»

ብራዚል ደግሞ ከራሷ አቋም በመነሣት ለ ብሪክስ አባል ሃገራት መድረክ መጠናከር ዐቢይ ግምት ሆኗል የምትሰጠው። በሳዖ ፓውሎ ፌደራል ዩንቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ክሪስቲና ፔቼኪሎ እንዲህ ይላሉ።

« ብሪክስ አባል ሃገራት፣ ለብራዚል ፤ ዓለም አቀፍ ሚናዋን በማጉላት የተሃድሶ ለውጥ እንዲጠናከር ማድረግ የሚያስችላትን መድረክ እንደፈጠሩላት ነው የሚሰማት። ሩሲያ ከ ቡድን 8 መገለሏ አያሳስበንም፤ በአንጻሩ እንዲያውም፣ ከአዳጊ አገሮች በላቀ ሁኔታ እመርታ በማሳየት ላይ የሚገኙ አገሮች ጥቅም የሚጠበቀውና ይበልጥ የሚጠናከረው ከ ቡድን 8 ይልቅ በብሪክስ ውስጥ በመወከል ነው።»

ብራዚል ፤ የደቡብ -ደቡብ ትብብር የሚባለውን ሁለንተናዊ ትብብር በማራመድ ዐቢይ ድርሻ ያበረከተች ሀገር መሆንዋም ነው የሚነገርላት። ይህም ፣ ቀደም ሲል በልዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ አመራር ወቅት ነው ፈር የያዘው። በመሆኑም፤ ለምሳሌ ያህል ፣ ከብራዚል ጋር በሚደረግ የንግድ ልውውጥ ረገድ ፤ ቻይና ዩናይትድ ስቴትስን መቅደሟ ታውቋል።

የብራዚል ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ዲልማ ሩሴፍ ጉባዔውን መርቀው ከመክፈታቸው በፊት ኢንተርኔትንና የዜጎችን መብት የሚመለከት ረቂቅ ህግ በፊርማቸው ማጽደቃቸው የሚታወስ ነው። የዓለም አቀፉ ጉባዔ ተሳታፊዎችም ፤ የብራዚልን የኢንተርኔት አጠቃቀምና የተገልጋዮችን መብት የሚመለከተውን ህግ በጭብጨባ ከማድነቃቸውም ዓለም አቀፍ ሞዴል ሊሆን የሚችል ነው ማለታቸው ነው የተጠቀሰው። የፍርድና ፍትሕ ሚንስትር ሆሴ ኤድዋርዶ ካርዶዞ ፤ ሕጉ ሲረቀቅ ሕብረተሰቡ፤ እንዲሁም የዲጂታል ዐዋቂዎች እንደመከሩበት ነው የገለጡት።

በባራዚል ከ 202 ሚሊዮን ገደማው የአገሪቱ ዜጎች ፤ ገሚሱ መቶ ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑት ኢንተርኔት አገልግሎት የሚያገኙ ናቸው። በጌቱሊዮ ቫርጋስ ድርጅት የህግ ፕሮፌሰር የሆኑት ሮናልዶ ሌሞሽ፤ ውስብስብ በሆነው ኢንተርኔት ነክ ዓለም አቀፍ ውይይት ፤ ብራዚል የመሪነቱን ድርሻ በመያዝ ላይ ናት ማለታቸው ተጠቅሷል። ሌሞሽ እንደሚሉት የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የፀጥታ ድርጅት በፈጸመው ዓለም አቀፍ ስለላ ሳቢያ፤ የዋሽንግተን የኢንተርነት የበላይ አመራር ማክተም ይኖርበታል።

የብራዚል ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ዲልማ ሩሴፍ፣ በጀርመን መራኂተ መንግሥት ወ/ሮ አንጌላ ሜርክል ላይ እንደተፈጸመው ሁሉ፤ በርሳቸውም ላይ በግል ስለላ መካሄዱን ከመቃወማቸውም፤ ባለፈው መስከረም በተባበሩት መንግሥታት አጠቃላይ ጉባዔ፣ የኢንተርኔት አመራርና አገልግሎት፣ በዓለም አቀፍ የሲቭል ቡድን ሥር እንዲሆን ማሳሰባቸው የሚታወስ ነው። በዚያው በብራዚል ከወዲያኛው ሰሞን ዓለም አቀፍ ጉባዔ ለማካሄድ ግፊት የፈጠረውም፤ ከ NET MUNDIAL አስተባባሪዋች መካከል ፤ በብራዚል የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር ፣ የመረጃ ሥነ ቴክኒክ መርሕ ዋና ጸሐፊ ቪርጂሊዮ አልሜይዳ እንዳሉት ፤ በኤድዋርድ ስነውደን በኩል የተጋለጠው ምሥጢር ነው።

ግራም ነፈሰ ቀኝ ፣ የምርምር ውጤቶችን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለሁሉም ማካፈል የሚቻልበት አሠራር በአዲሱ የኢንተርኔት አመራር ይበልጥ ሊስፋፋ እንደሚችል ነው የሚታሰበው።

ተክሌ የኋላ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic