ኢትዮጵያ «ግራ አጋቢ» ምድር | ኢትዮጵያ | DW | 13.07.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ «ግራ አጋቢ» ምድር

የድንቅነሿ-ድንቅ ሐገር-ኢትዮጵያ ግን ከጋዜጠኛዉ እስከ ጠበቃዉ፤ ከፖለቲከኛዉ እስከ መብት ተሟጋቹ እንዳሉት ከግራ-አጋቢ፤ ዘፈቀዳዊ እርምጃ፤ ካሻቸዉን አድራጊ ሾሞችዋ ጋር በመቶ-ከመቶ የምርጫ ዉጤት ታጅባ ትቀበላቸዋለች።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:05

ኢትዮጵያ «ግራ አጋቢ» ምድር

1972 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የያኔዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደነት ሪቻርድ ኒክሰን ሕዝባዊት ሪፐብሊክ ቻይናን ሲጎበኙ አስተናጋጃቸዉ የቻይና መሪ ሊቀመንበር ማኦ ዜዱንግ «መቼም ይሕን ጉብኝት የድሮ ወዳጃችን ጂያንግ ካይ-ሼክ እንደማድግፉት አምናለሁ» አሏቸዉ አሉ-በቱርጁማን።

ጂያንግ ካይ-ሼክ ወይም ጂያንግ ዦንግ ዤንግ፤ ማኦ የሚመሯቸዉ የቻይና ኮሚንስቶች ከዋናዋ ቻይና አባርረዋቸዉ ታይፔ-ታይዋን ላይ «የቻይና ሪፐብሊክ» የተሰኘዉን መንግሥት የመሠረቱ ጄኔራል፤ ፖለቲከኛም ነበሩ።ኒክሰን የማኦዋን ቻይና መጎብኘታቸዉን በዩናይትድ ስቴትስ የሚደገፉት የታይፔ፤የቶኪዮና የሶል መሪዎች አጥብቀዉ ተቃዉመዉት ነበር።ጉብኝቱ የዩናይትድ ስቴትስ ፖለቲከኞችን፤ የፖለቲካ አዋቂዎችን፤ ጋዜጠኞችንና ያኔ ብዙም የማይታወቁትን የመብት ተሟጋቾችንም በመደገፍና በመቃወም ለሁለት የገመሠ ነበር።

ደጋፊዎቹ፤ ጉብኝቱ ሩብ ምዕተ-ዓመት ያስቆጠረዉን የዋሽግተንና የቤጂንግ (ወይም ፔኪንግ)ን ጠላትነት ለማስወገድ፤ የሩቅ ምሥራቅን ሠላም ለማስከበር፤ ከሁሉም በላይ የአሜሪካንን የበላይነት ለማሰጠበቅ ይበጃል ባዮች ነበሩ።ተቃዋሚዎቹ ባንፃሩ ዩናይትድ ስቴትስ ለኮሚንስታዊት ቀንደኛ ጠላትዋ እንደተንበከከች የሚቆጠር፤የአካባቢዉን ታማኝ ወዳጆችዋን እንደካደች-የሚታይ፤ ኮሚንስቶቹ በቻይና ሕዝብ ላይ የሚያደርሱትን ጭቆና የሚያበረታታ መልዕክት የሚያስተላልፍ በማለት አጣጥለዉት ነበር።

ኒክሰን ግን ሳምንት የቆየ ጉብኝታቸዉን ሲያጠናቅቁ «ዓለምን የለወጠ ሳምንት------ለሃያ-ሁለት ዓመት የከፋፈለንን ጠላትነት ለማስወገድ በ16 ሺሕ ማይል ርቀት መካከል ለወደፊቱ ድልድይ የምገነባበት---»እያሉ አወዳደሱት።

43ኛ ዓመቱ ዘንድሮ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ በኢትዮጵያ ሊያደርጉት ያቀዱት ጉብኝት በዓላማ-በይዘት፤ በክብደት-ቅለትም፤ ከኒክሰን ጋር በጭራሽ የሚስተካከል አይደለም።ሁለቱ ጉብኝቶች በአላማ፤ ይዘት፤ ክብደት የመለያየታቸዉን ያክል አንድ-የሚሆኑበት አንድ ምክንያት መኖሩ ሐቅ ነዉ።ጥቅም።ዘመን የማይሽረዉ፤ ዓለም የሚያዉቀዉ-እነሱም «የሕዝብና የሐገር ብሔራዊ---ጥቅም» እያሉ የሚያንቆለጳጵሱት-ዕዉነት።

አሜሪካኖች እንደ መሪ፤ እንደ ፖለቲከኛ፤ እንደ ዲፕሎማት ወይም እንደ ኩባንያ ባለቤት ሐገር ጎበኙ-አልጎበኙ፤ ጠላት እና ወዳጅ እያሉ አንዱን አጥፍተዉ ሌላዉን አቅፈዉ ደገፉ፤ ለሰብአዊ መብት፤ለፍትሕ፤ ለዴሞክራሲ መቆማቸዉን እየተናገሩ-ከጨቋኝ አማባገነኖችን መሐል-እየመረጡ አንዱን ሲረዱ-ሌላዉን ሲያስወግዱ የመርሐቸዉ መሠረት ይኸዉ ነዉ።ጥቅምን ማስከበር።

እርግጥ ነዉ ኦባማ በያዝነዉ ወር ያደርጉታል የተባለዉ ጉብኝት አሜሪካኖችን ሊያከራክር ቀርቶ መሪዉ ጥንታዊቱን አፍሪቃዊት ሐገር እንደሚጎበኙ የሚያዉቀዉም ጥቂት ነዉ።የሚያዉቁትም፤ ያላወቁት ቢያዉቁትም የጉብኝቱ ዓላማ በትልቅቱ ሐገር የመርሕ መዘዉር ላይ የሚሾር መሆኑን እንደሚያዉቁት ለማወቅ ተንታኝ አያስፈልግም።

የታቀደዉ ጉብኝት ወትሮም አንድ ያልሆኑትን ኢትዮጵያዉያንን ግን እሁለት ገምሶ ለማነታረክ፤ ለአደባባይ የተቃዉሞ ሰልፍ ለማሳደምም ትልቅ ርዕስ ነዉ።ተወዛጋቢዎች ለየአቋማቸዉ ማስረገጪያ የሚያቀርቧቸዉ ምክንያቶች የመቃረናቸዉን ያክል የጉብኝቱ ዋና መሠረት አንድ መሆኑን እኩል ያዉቁታል።ጥቅም።

ኒክሰን በቻይና ያደረጉትን ጉብኝት የተከታተሉ እንደፃፉት የኒክሰን የፀጥታ አማካሪ (ኋላ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር) ሔኔሪ ኪንስንጀር ጉብኝቱን ለማመቻቸት በድብቅ ወደ ቻይና ከተጓዙበት ከ1971 ጀምሮ የቤጂንግ ኮሚንስቶች የሚወቀሱበትን ጉዳይ ለመሸፋፈን ቻይናን ማፀዳዳት፤ተበዳዮችን መሸነጋገል የእስረኞችን ይዞታ ማሻሻል፤የዚያኑ ያክል ጥንካሬያቸዉን ለማሳየትም ወታደራዊና ምጣኔ ሐብታዊ ክርናቸዉን ለመወጣጠር ሲጣጣሩ ነበር።

ፕሬዝደንት ኦባማ ኢትዮጵያን መጎብኘታቸዉን የሚቃወሙ ወገኖች ጉብኝቱን በመገናኛ ዘዴዎች ከመተቸት አልፈዉ ተቃዉሟቸዉን ኦባማ ቤተ-መንግሥትን ደጃፍ ላይ በሠልፍ በገለፁ ማግስት ከወደ አዲስ አበባ-የሰማነዉ የያኔዋን ቤጂንግን የሚያስታዉስ እርምጃ ነዉ።

የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ሰወስት ዓመት ሲያንከባልለዉ የቆየዉን የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ መሪዎችን ክስ በሰወስት ቀን አጣድፎ አስራ-ስምንቱንም ተከሳሾች በተያዘባቸዉ የአሸባሪነት የወንጀል ጭብጥ የጥፋተኛኝነት ብይን ሰጥቷል።የተጣደፈዉ ብይን «ምናልባት ኢትዮጵያ የፍትሕ ሐገር መሆንዋን-ለማሳየት------ ምናልባት በአሸባሪነት ለሚጠረጠሩ ምሕረት እንደሌላት------ምናልባት-----» እያልን ለታላቅ እንግዳዋ ለማማረብ ብለን መገመት እንችላለን።

ተከሳሾቹ አሉ እንደተባለዉ ፍርድ ቤቱን እንደ ፍትሕ ማዕከል ሳይሆን እንደ የመንግሥት ባለሥልጣናት ትዕዛዝ ፈፃሚ መቁጠራቸዉን አለመሸሻጋቸዉ እንጂ-ክፋቱ።

ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ እንዳሉት ሆነም-አልሆነ ተከሳሾች በአስር ቀን ዉስጥ የቅጣት ማቅለያ እንዲያቀርቡም ወስኗል። በልማዱ የቅጣት ማቅለያዉን የሚያቀርቡት ወይም የሚያዘጋጁት የተከሳሾች ጠበቆች ናቸዉ።ይሁንና ፍርድ ቤቱ በተከሳሾቹ ላይ የጥፋተኝነት ብይን በሠጠበት ዕለት (ባለፈዉ ሳምንት ሰኞ) የፍትሕ ሚንስቴር በፃፈዉ ደብዳቤ የተካሳሾቹ ዋና ጠበቃ አቶ ተማም አባ ቡልጎ ለአመት ከሰባት ወር ጥብቅና እንዳይቆሙ አግዷል።ለምን?

የፍትሕ ሚንስቴር ባለሥልጣናትን መልስ እንዲሰጡ በተደጋጋሚ ሥልክ ብንደዉልም ልናገኛቸዉ አልቻልም።አቶ ተማም ግን የሚገምቱት አለ።

«በእነሱ መልካም ፈቃድ።» በአሸባሪነት ተወንጅላ መጀመሪያ አስራ-አራት ዓመት እስራት ኋላ በይግባኝ አምስት ዓመት ተፈርዶባት የታሰረችዉ ፀሐፊና መምህርት ርዕዮት ዓለሙ የተከሰሰች፤ ተወነጀለችበትን ጭብጥ አልቀበልም እንዳለች-ከአራት ዓመት በላይ አስቆጥራለች።

justitia rechtsprechung Symbolbild

የሙያ ተጋሪዎችዋ፤ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾችም ርዕዮት የታሰረችዉ መንግሥትን የሚተች መጣጥፍ በማሳተሟ እንጂ-መንግሥት እንዳለዉ አሸብራ፤ ለማሸበር ሞክራ ወይም ከአሸባሪዎች ጋር ተባብራ አይደለም።

በዚሕም ምክንያት መታሰር-መከሰሷ እንጂ የታሰረችበት ትክክለኛ ምክንያት አይታወቅም።ኦባማ «መጡ፤ መጡ» ሲባል በቀደም ተለቀቀች።እንደ እስራቱ ሁሉ መለቀቋ እንጂ-የተለቀቀችበት ትክክለኛ ምክንያት አይታወቅም።

የጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ ታሪክም ግራ-አጋቢ ነዉ።ከዓመት ከሰወስት ወር በፊት-ከዘጠኝ ባልረቦቹ ጋር ድንገት ታሰረ።ከአሸባሪዎች ጋር በመተባበር ወንጀል ተከስሶ የፍርድ ቤት ቀጠሮ ሲጠብቅ ድንገት ክሱ ተሰርዟል-አንተም ተለቀሐል አሉት።

አንድ እስር ቤት ከታሰሩት፤ ባንድ የወንጀል ጭብት፤ ባንድ የክስ መዝገብ ከተከሰሱት ዘጠኝ ጋዜጠኞችና የአምደ መረብ ፀሐፍት መካካል አምስቱ፤ ተስፋዓለም «ግራ-አጋቢ» ባለዉ መንገድ ሲለቀቁ አራቱ እዚያዉ እስር ቤት ቀሩ።

ለጋዜጠኛዉ «ግራ አጋቢ» ነዉ።ለጠበቃዉ « እነሱ ከፈቀዱ---»። የፌስ ቡክ ምፀተኞች ደግሞ «ብዙ እስረኞች እንዲፈቱ ምናለ ኦባማ ኢትዮጵያን ደጋግመዉ ቢጎበኙ።» አይነት ይላሉ።ለመብት ተማጋቹ ለያሬድ ሐይለማርም ግን ድንገት የመፍታቱ ዘመቻ ጥቅም የተሰላበት ግን-የዘፈቀደ ፖለቲካዊ ዉሳኔ።

የቀድሞዉ ተቃዋሚ ፓርቲ የኢትዮጵያ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ከፍተኛ ባለሥልጣን አቶ አስራት ጣሴ እንደሚሉት ደግሞ ኢትዮጵያ ዘፈቀዳዊም፤ግራ-አጋቢም፤ሹሞችዋ ያሻቸዉን የሚያደርጉባትም ሐገር ልትሆን-ላትሆንም ትችላለች።የዜጎች ነፃነትና መብት ግን ክፉኛ ይደፈለቅባታል።ታዋቂዉ ጠበቃና የሕግ ባለሙያ አቶ ተማም አባቡልጎ ያክሉበታል።

1965 የታላቅዋ ብሪታንያ ንግሥት ኤልሳቤት ዳግማዊ ኢትዮጵያን ሲጎበኙ፤ አፄ ሐይለ ሥላሴ የተቀበሏቸዉ የአዲስ አበባ «ለማኞችን» ከየሥፍራዉ አስለቅመዉ፤ ቁሻሻ ሥፍራዎችን አስከልለዉ፤ አዉራ ጎዳናዎችና ሕንጻዎችን አስጊጠዉ ነበር።በሐምሳ ዓመቱ ዘንድሮ ጠቅላይ ሚንስትር ሐይለ ማርያም ደሳለኝ ፕሬዝደንት ኦባማን ለመቀበል እንደ አፄ ሐይለ ስላሳሴ ወይም እንደ ማኦ ዜዱንጉ መዘጋጀት አለመዘጋጀታዉን አናዉቅም።

የድንቅነሿ-ድንቅ ሐገር-ኢትዮጵያ ግን ከጋዜጠኛዉ እስከ ጠበቃዉ፤ከፖለቲከኛዉ እስከ መብት ተሟጋቹ እንዳሉት ከግራ-አጋቢ፤ ዘፈቀዳዊ እርምጃ፤ ካሻቸዉን አድራጊ ሾሞችዋ ጋር በመቶ-ከመቶ የምርጫ ዉጤት ታጅባ ትቀበላቸዋለች።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Audios and videos on the topic