ኢትዮጵያ፣ የግጭትና ዉዝግብ ምድር | ኢትዮጵያ | DW | 25.03.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ፣ የግጭትና ዉዝግብ ምድር

የጎሳ ግጭቱ አጎዞ አጎዞ ርዕሠ-ከተማ አዲስ አበባ «የኔነች-አይደለችም» እሰጥ አገባ ቀስቅሷል።በአዉሮፕላን አደጋ ምክንያት ላጭር ጊዜ ተዳፎኖ የነበረዉ የአዲስ አበባ ጉዳይ ከከተማይቱ-ባለስልጣናት እስከ ጋዜጠኞች፣ ከጠቅላይ ሚንስትሩ፣ እስከ ፖለቲካ አቀንቃኞች ያሉትን ተራበተራ ከዉዝግብ ሞጅሯል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 13:45

የተካረረዉ ዉዝግብ ያስፈራል፣ ግጭት፣ግድያዉ ተበራክቷል።እስከ መቼ

የምዕራብ ኦሮሚያና የበኒ ሻንጉል ጉሙዝ ድንበሮች ነዋሪዎችን ያጋደለ፣ያፈናቀለዉን ጠብ-ግጭት የሚያስወግድ ጉባኤ የመደረጉን በጎነት አስተንተነን ሳናበቃ፣ ነጆ አጠገብ መንገደኞች በጥይት ተደብድበዉ፣ በእሳት ጋይተዉ መገደላቸዉን ተረዳን።ብስራትና መርዶ።አርባ ሺሕ የባቢሌ አካባቢ ተፈናቃዮች ወደየቀያቸዉ መመለሳቸዉን ሰምንተን ሳንጨርስ ተመላሾቹ ቤት ንብረት እንደሌላቸዉ ተነገረን።ደስታና ሐዘን።ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ የመንግሥታቸዉን ጥሩ ሥራ ሲያብራሩ  ቅዳሜ-ከምንጃር ሸንኮራ፤ከዉሊንጪቲና መተሐራ የግጭት፤ግድያ መፈናቀል ዜና ይንቆረቆር ገባ።ተስፋና ትፅቢት።ሳምንቱ በሌላ ሳምንት ተተካ።ግጭት-ግድያ፣ ዉዝግብ፣ትንኮሳዉም እንዲሁ።እስከመቼ? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

የሶማሌና የኦሮሞ፣የአፋርና የኢሳ (ሶማሌ)፣የገሬ (ሶማሌ)ና የቦረና (ኦሮሞ)፣የጉጂ (ኦሮሞ)ና የቡርጂ፣ የግድኦና የጉጂ (ኦሮሞ)፣የቅማንትና የአማራ፣የትግራዊና የአማራ፣ የአማራና የአፋር፣ የኦሮሞና የበኒ ሻንጉል፣ የጋሞና የኦሮሞ፣የአማራ፣አርጎባና የከረዩ (ኦሮሞ)---- ጎሳ እንደረድራለን፣ ግጭት እናሰላለን፣ሟች ቁስለኛ እንቆጥራለን። አንዱን ጠርተን-አስልተን-ቆጥረን ሳናበቃ ሌላ መተካቱ ነዉ-ድቀቱ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ባለፈዉ ቅዳሜ «ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ» ሲሉ  የመርዶ-ብስራት፣ የተስፋ-ሥጋት፣ የትርምስ-ስክነት ቅይጥ ጉዞዋን ማለታቸዉ ከሆነ ቢያንስ ለአስር ወር ይቀጥላል ብለዋል።

ከአስር ወር በኋላ ምናልባት ምርጫ ይደረግ ይሆናል።ምንልባት እንደ ሽግግር የሚታየዉ ወቅት ያበቃ ይሆናል።ምናልባት-----

አሁን የማናዉቀዉ ይሆን ይሆናል።ብቻ፣ የኢኮኖሚ አዋቂና የፖለቲካ ተንታኝ ፕሮፌሰር መሐመድ አባጀበል ጣሒሮ ያሁኑን የጎሳ ግጭቱ በሽግግር ወቅት የሚያጋጥም ተፈጥሯዊ ይሉታል።

በመቀለ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ ክፍል የገብረሕይወት ባይከዳኝ የስትራቴጂ ጥናት ኃላፊ አቶ መረሳ ፀሐይ ግን የግጭት፣ ዉዝግቡ መሠረታዊ ምክንያት ካልተወገደ መቀጠሉ አይቀርም ባይ ናቸዉ።መሠረታዊ ምክንያቱ ይጠቅሳሉ።

ፕሮፌሰር መሐመድ እንደሚሉት ሠላምን ማስፈን፣ ነፃነትን ማስከበር፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታም ዋጋ ያስከፍላል።በተለይ ብዙ ጎሳ የሚኖርባት ኢትዮጵያ አሁን የሚታየዉ አይነት የጥቅም ግጭት ቢቀሰቀስባት አይገርመም።ይሁንና የሚከፈለዉ ዋጋ የከፋ ኪሳራ እንዳያመጣ መትሄ መፈለግ ግዴታ ነዉ-እንደ ፕሮፌሰሩ።

አቶ መረሳ የዘመናይ ኢትዮጵያ መሪዎችን ይወቅሳሉ።ለሐገሪቱ መሠረታዊ ችግር ሁነኛ መፍትሔ አልፈለጉም እያሉ። ከእንግዲሕም ችግሩን ለማስቀረት አብነቱ፣ የፖለቲካ አዋቂዉ እንደሚሉት ድርድር ነዉ።ድርሩ ግን ቀላል አይሆንም።

የጎሳ ግጭቱ አጎዞ አጎዞ ርዕሠ-ከተማ አዲስ አበባ «የኔነች-አይደለችም» እሰጥ አገባ ቀስቅሷል።በአዉሮፕላን አደጋ ምክንያት ላጭር ጊዜ ተዳፎኖ የነበረዉ የአዲስ አበባ ጉዳይ ከከተማይቱ-ባለስልጣናት እስከ ጋዜጠኞች፣ ከጠቅላይ ሚንስትሩ፣ እስከ ፖለቲካ አቀንቃኞች ያሉትን ተራበተራ ከዉዝግብ ሞጅሯል።

አቶ መረሳ የአዲስ አበባ ጉዳይ ሌላዉ አካባቢ

ግጭትና ግድያ ካስከተለዉ የመሬት ወይም የሐብት ባለቤትነት ፖለቲካ የተለየ አይደለም ባይ ናቸዉ።ፕሮፌሰር መሐመድ አባጀበል ግን የኦሮሞ ፖለቲከኞች በአዲስ አበባ ላይ ያነሱት ጥያቄ፣ ጥያቄዉን በሚቃወሙት ዘንድ «መደናገር» ሳይፈጥር አልቀረም።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ባለፈዉ ቅዳሜ እንዳሉት እሳቸዉ ወይም መንግስታቸዉ ያሉ-የሠሩትን ጥሩ እንጂ ሥሕተቱን ወይም መስራት የሚገባቸዉን ጥሩ ጠቋሚዎችን ወይም ተቺዎችን አይወዱም።የወል ስም ሰጧቸዉ፣ «አቅላይ» ብለዉ።

 የአዲስ አበባ ሕዝብ ምናልባት በኢትዮጵያ ዘመናይ ታሪክ በገዛ-ፍቃድና ፍላጎቱ በነቂስ አደባባይ የወጣዉ የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድን የለዉጥ እርምጃ በመደገፍ ነዉ።በማቅለል አልነበረም።ኢትዮጵያ የሚኖረዉ አይደለም አሜሪካና አዉሮጳ የተሰደደዉ ኢትዮጵያዊ ከዋሽግተን ዲሲ-እስከ ፍራንክፈርት የሚገኙ አደባባዮችን ያጥለቀለቀዉ ጠቅላይ ሚንስትሩን አወድሶ፣ ጅምር ሥራቸዉን አሞግሶ ነዉ።

የኤርትራ ሕዝብ ሳይቀር የአስመራ አዉራጎዳናዎችን በሰልፍ የሞላዉ ለአዲሱ የኢትዮጵያ መሪን ሥራና እርምጃን በማድነቅ፣ማወደስ ነዉ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ የመንግስታቸዉን ሥራ፣አሰራርና ዓለማን የሚጠቁም ዕቅድ ወይም ፍኖተ ካርታ  አሳዉቀዉ

አያዉቁም።ቅዳሜ እንዳሉት ግን የኢትዮጵያ ሁኔታ አሁን ባለበት ከቀጠለ፣የሚቀጥለዉ ለአስር ወር ነዉ።በአስር ወር የሚነሳዉን ግጭት-ወይም የሚሠፍነዉ ሠላም፣ የሚጦዘዉን ዉዝግብ ወይም የሚወርደዉን እርቅ አሁን ማወቅ በርግጥ ነብይነትን ይጠይቃል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዳሉት ግን ከአዲስ አበባ ዉዝግብ እስከ ምዕራብ ጎንደር ግጭት፣ ከምዕራብ ወለጋ እስከ ድሬዳዋ፣ ከመተሐራ እስከ ጌዲኦ የየዋሕ ኢትዮጵያዉያን ሞት፣መፈናቀል፣ ሥጋት እንዲወገድ የማይመኝ፣የማይጥር ጤነኛ ኢትዮጵያዊ ግን የለም።ሁሉም የሚመኘዉና የሚጥርለት  እዉን የሚሆነዉ ደግሞ፣ አዋቂዎቹ እንደሚመክሩት ሁሉም የሚሳተፍበት አግባቢ  ድርድር ሲደረግ፣ ሕግና ሥርዓት ሲከበርም ነዉ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic