ኢትዮጵያ የግብፅን ማስጠንቀቂያ ማጣጣሏ | ኢትዮጵያ | DW | 12.06.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ የግብፅን ማስጠንቀቂያ ማጣጣሏ

ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የጀመረችው ግዙፍ የህዳሴ ግድብ ለግብፅ የሚደርሰውን የውኃ ፍሰት የሚቀንስ ከሆነ ግብፅ በሁሉም አማራጮች እንደምትጠቀም ያሰማቸውን ማስጠንቀቂያ ኢትዮጵያ « የሥነ አዕምሮአዊ ጦርነት » ስትል በማጣጣል፣ በሚሰነዘርባት ማንኛውም ርምጃ አንፃር ራስዋን እንደምትከላከል አስታውቃለች።

የግድቡን ግንባታም እንደምትቀጥልበት አክላ ገልጻለች። በአፍሪቃ ብዙ ሕዝብ የሚኖርባቸው እና ፈጣን ዕድገት የሚታይባቸው ኢትዮጵያ እና ግብፅ በአፍሪቃ ትልቁ በሚባለው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ ላይ ዲፕሎማሲያዊ ድርድር በማካሄድ ላይ ቢሆኑም፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል ባለፉት ቀናት በወንዙ ውኃ ሰበብ የተሰማው ፀብ ፍለጋ አነጋገር ሁለቱን ሀገራት ወዝግብ ውስጥ እንዳያስገባ አስግቶዋል።

የግብፅ ፕሬዚደንት መሀመድ ሙርሲ ባለፈው ሰኞ ለሀገራቸው ምክር ቤት ባሰሙት ንግግር በግድቡ ግንባታ የተነሳ የዓባይ ውኃ ፍሰት እንዳይቀንስ ማድረግ ሁሉንም አማራጮች ከመውሰድ እንደማይቆጠቡ ማስታወቃቸው ይታወሳል።

ይህ የግብፅ « ፉከራ » እንደማያስፈራት እና የትኩረት አቅጣጫ እንደማያስቀይራት፣ እንዲሁም፣ የግድቡንም ግንባታ ለሴኮንዶች እንኳን እንደማታቋርጥ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ትናንት አስታውቀዋል። ድርድር እንደማይኖርም አክለው ግልጽ አድርገዋል።
« የህዳሴ ግድቡ የኢትዮጵያ የባንዲራ ግድብ ነው። በፍፁም ድርድር አይኖርም ይህንን በተመለከተ። ይህንን ግልጽ አድርገንላቸዋል። በዚሁ ጉዳይ ላይ እንደማንደራደር ነግረናቸዋል። ሌሎች የጋራ ጉዳዮች ካሉ ግን ለመነጋገር ክፍት ነው የሚሆነው። በተረፈ ግን ይኸ በኛ በኩል ያለው ግምት በግብፅ ውስጥ የሚታየውን የፖለቲካ ትኩሳት እና ወደ ውጭ ዓይን ለመወርወር እና አቅጣጫ ለማስቀየር ካልሆነ በስተቀር ለግብፅ ሕዝብም ሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ሁለቱንም መንግሥታትም የሚጠቅም አለመሆኑን እነሱም ያውቁታል ማለት ነው። »

Blick über den Wasserfall Blue Nile Falls in der Nähe von Bahir Dar in Äthiopien


የቀድሞ የግብፅ ወታደራዊ መሪዎች የዓባይን ወንዝ ውኃ ፍሰትን ሊቀንሱ ይቸላሉ የሚባሉ ግድቦችን ለማጥቃት የሚያስችላቸው ዕቅድ እንደነበራቸውም የሮይተርስ ዘገባ አስታውቋል። አንዳንድ የግብፅ ፖለቲከኞች በኢትዮጵያ ላይ የአየር ጥቃት በመጣል ወይም የኢትዮጵያን ዓማፅያን በመደግፍ ግድቡን ከጥቅም ውጭ ማድረግ በሚል ከጥቂት ጊዜ በፊት ሀሳብ የሰነዘሩበት አነጋገራቸው ሳያስቡት በቴሌቪዥን መሰማቱ የሚታወስ ነው። ይህን ዛቻ በተመለከተ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከጥቃት ለመከላከል የሚያስችላትን ርምጃ በማሰላሰል ላይ ስለመሆንዋ አምባሳደር ዲና ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ «እንኳንስ ነፃነትዋን ከማንኛውም አጥቂ ኃይል በመከላከልዋ የምትታወቀው ኢትዮጵያ ትቅርና ማንም ሀገር ካላስፈላጊው ጥንቃቄ አይንቀሳቀስም» ሲሉ መልሰዋል። ይህ በዚህ እንዳለ፣ የአፍሪቃ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዚደንት ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ ኢትዮጵያ እና ግብፅ በወንዙ ውኃ ክፍፍል ጉዳይ ላይ የተፈጠረውን ንትርክ ለማስወገድ እና ሁለቱም ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መፍትሔ በውይይት እንዲያፈላልጉ አሳስበዋል።
ግብፅ አንድ ጠብታ ውሃ እንዲቀርባት እንደማይፈልጉ ያስታወቁት የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር መሀመድ ከማል አምር በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ ጋ ለመወያየት ወደ አዲስ አበባ ይጓዛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ዘግይቶ በደረሰን ዜላ ዘገባ መሠረት ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ይህንኑ ኢትዮጵያ ከግብፅ ጋ የገጠመችውን ውዝግብ በተመለከተ ለኢትዮጵያ ራድዮ እና ቴሌቪዥን መግለጫ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በመግለጫቸው እንዳሉት፣ የግብፅ ባለሥልጣናት እንደዛቱት ጦርነት ይጀምራሉ ብለው አያምኑም፤ ከዚህም ሌላ የግብፅ መሪዎች ጦርነትን ጨምሮ ሁሉንም አማራጮች እንጠቀማለን ማለታቸውን « ካላበዱ በስተቀር » አያደርጉትም ብለዋል። በዚህ ፈንታ፣ የግብፅ ባለሥልጣናት እንዲህ ዓይነቱን አቀራረባቸውን አቁመው ወደ ውይይት እና ንግግር እንዲመለሱ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም አሳስበዋል።

አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሀመድ