ኢትዮጵያ፤ የጋዜጠኞች የሥራ እንቅስቃሴ | ኢትዮጵያ | DW | 09.03.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ፤ የጋዜጠኞች የሥራ እንቅስቃሴ

ኢትዮጵያ ዉስጥ በኦሮሚያ ክልል የሚካሄደዉን የተቃዉሞ እንቅስቃሴ ለመዘገብ የተንቀሳቀሱ የዉጭ ጋዜጠኞች ታሥረዉ መለቀቃቸዉ ተነገረ። የዉጭ ዜጎች የሆኑት ጋዜጠኞች የታሠሩበት ምክንያት እንዳልተነገራቸዉ ዶቼ ቬለ ያነጋገረዉ አንደኛዉ ጋዜጠኛ ገልጿል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 02:23

አዲስ አበባ ዩኑቨርሲቲ

በምሥራቅ አፍሪቃ ለዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የሚዘግቡ ጋዜጠኞች ማኅበር ጋዜጠኞቹ ሥራቸዉን ለመሥራት ሲሞክሩ የደረሰባቸዉ ወከባ ሀገሪቱ ዉስጥ እየከፋ የመጣዉን የፕሬስ ነፃነት ይዞታ እንደሚያመለክት ለዶቼ ቨለ ገልጿል።

ለብሉምበርግ የኢንተርኔት ድረገጽ የሚዘግበዉ ጋዜጠኛ ዊልያም ዴቪሰን ኢትዮጵያ ዉስጥ ላለፉት አምስት ዓመታት በሙያዉ እንደሠራ ይናገራል። በእነዚህ ጊዜያት በተለያዩ አጋጣሚዎችና አካባቢዎች ለመንግሥት ስሱ በሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ዘገባዎችን ለማቅረብ ሲንቀሳቀስ ችግሮች ቢገጥሙትም ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ ያደረዉ ግን ባለፈዉ ሐሙስ ለዓርብ አጥቢያ ነዉ። ተይዞ የታሠረበትን ምክንያት ባያዉቀውም እቅዱ ግን ምዕራብ ሐረርጌ ዉስጥ ያለዉን የተቃዉሞ እንቅስቃሴ ለመዘገብ ነበር።

«የተያዝኩት አዋሽ ከተማ አቅራቢያ ነዉ። ዓላማዬ ግን ኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሐረርጌ ያለዉን እንቅስቃሴ ለመዘገብ ነበር። እስካሁን ለምን እንደታሠርኩ አላዉቅም። ነገ ከመንግሥት ባለስልጣን ጋር ስለጉዳዩ እነጋገራለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።»

ጋዜጠኛ ዊልያም ዴቪሰን ብቻም አልነበረም በወቅቱ የተያዘዉ ለሌላ መገናኛ ብዙሃን የሚሠራ ጋዜጠኛ እና አስተርጓሚያቸዉም ጭምር ነበሩ። በምሥራቅ አፍሪቃ ለዉጭ መገናኛ ብዙሃን የሚዘግቡ ጋዜጠኞች ማኅበር ሊቀመንበር ኢሊያ ግሪድነፍ ጋዜጠኞቹ አስፈላጊዉን ፈቃድ ይዘዉ የሚንቀሳቀሱ በመሆኑ የተያዙበትን ምክንያት ምንነት አለመገለፁ ለእነሱም ጭምር አስደንጋጭ እንዳደረገዉ ያስረዳሉ።

«ለዚህም ነዉ ታሥረዉ ለተለቀቁት ጋዜጠኞች ሁሉ አስደንጋጭ የሆነዉ በዚህ ምክንያት ነዉ። ምክንያቱም የሚያስፈልገዉ የመኖሪያም ሆነ በጋዜጠኝነት ኢትዮጵያ ዉስጥ የመሥራት ፈቃድ ጭምር አላቸዉ። ግን ከአዲስ አበባ ወጥተዉ ወደኦሮሚያ ክልል ሲያመሩ በፌደራል ፖሊስ እንዲቆሙ ተደርገዉ ታሠሩና እዚያዉ አደሩ። የኢትዮጵያ መንግሥት የፕረስ ነፃነትን ለማፈን ከሚያደርገዉ ርምጃ ሌላ ለምን ይህ እንደተደረገ የሚያዉቁት ምንም ነገር የለም። በቅርብ ሳምንታትም በዘፈቀደ በርካታ ጋዜጠኞች ታሥረዋል። ይህ ደግሞ ያለዉ ለረዥም ጊዜ ኢትዮጵያ ዉስጥ የዘለቀዉን የፕረስ ነፃነት ችግር ያመላክታል።»

ኢሊያ ግሪድነፍ በጉዳዩ ላይ ከመንግሥት ማብራሪያ ለማግኘት ማኅበሩም ሆነ ታሥረዉ የተለቀቁት ጋዜጠኞች መሞከራቸዉን ሆኖም እስካሁን እንዳልተሳካላቸዉም ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ዉስጥ የተከሰተዉ ድርቅ የከፋ ረሀብ ሊያስከትል ይችላል በሚል የዓለምን ትኩረት መሳቡን ያመለከቱት ግሪድነፍ በርካታ ጋዜጠኞችና መገናኛ ብዙሃን ይህን ጉዳይ ለመዘገብ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ መንግሥትን እንዳላስደሰተም ጠቅሰዋል። ከዚህም በተጨማሪ የሌላ ዜጋ የሆኑት ሁለቱ ጋዜጠኞች እዚያ ስላለዉ ግጭትና የህዝቡንም ስጋት ለመዘገብ ወደኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሐረር ሲጓዙ መያዛቸዉ በሀገሪቱ ያለዉ የፕረስ ነፃነት ይዞታ አሳሳቢነቱ እየተባባሰ መሄዱን እንደሚያሳይም አመልክተዋል። ኢሊያ ግሪድነፍ ኢትዮጵያ ዉስጥ የጋዜጠኞች ይዞታም የታወቀ ነዉ ይላሉ።

« ኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ላይ ያላት አመለካከት የታወቀ እዉነታ ነዉ ብዬ አስባለሁ። በርካታ የሀገር ዉስጥ ጋዜጠኞችንና ዘጋቢዎችን ሥራቸዉን በመሥራታቸዉ ብቻ በየጊዜዉ ወደወህኒ ይወርዉራሉ ያስራሉ። ማዋከቡም ተባብሷል፤ በቅርቡ የሆነዉም ፕረሱ ላይ የሚፈፀመዉ የማዋከቡ ርምጃ የደረሰበትን የሚያመላክት ነዉ።»

የከፋ የፕረስ ነፃነት እንዳላት የምትተቸዉ ኢትዮጵያ ባለፈዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ድንበር የለሽ ዘጋቢዎች ባወጣዉ ዘገባ ከ180 ሃገራት 142ኛ ደረጃ ተቀምጣለች።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic