ኢትዮጵያ፤ የእርሻ ልማትና የምግብ ብቃት | ኤኮኖሚ | DW | 03.08.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ኢትዮጵያ፤ የእርሻ ልማትና የምግብ ብቃት

በአሁኑ ጊዜ በአፍሪቃ፤ በተለይም በአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ ላይ ላተኮረ በዓይን ላይ የሚደቀነው የተለመደው የረሃብ አስከፊ ገጽታ ነው። የአካባቢው 12 ሚሊዮን ሕዝብ በወቅቱ የረሃብ ሞት አደጋ ተደቅኖበት የሚገኝ ሲሆን የኢትዮጵያም የድርቅ መለያነት ባለበት ቀጥሏል።

default

ለሁለት አሠርተ-ዓመታት ዓመጽና ስርዓተ-ዓልባነት ሰፍኖ በቆየባት በሶማሊያ የሕዝቡ ለከፋ ለረሃብ መጋለጥ ብዙም አያስደንቅም። በሌላ በኩል ቢቀር አንጻራዊ እርጋታ ባለባቸው በኬንያ ወይም በኢትዮጵያ ግን በተወሰነ መጠን እንኳ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ለክፉ ቀን ራስን ችሎ ለመገኘት አለመቻሉ ብዙ የሚያነጋግር ነው። ኢትዮጵያን በተመለከተ ያለፉት ዓመታት ከፍተኛ የኤኮኖሚ ዕድገት የተደረገባቸው እንደነበሩና ሂደቱ ቀጣይ እንደሚሆንም በተለይም ከመንግሥት በኩል በየጊዜው ሲነገር ነው የቆየው።
ሆኖም ከአሥር በመቶ በላይ የሆነው የኤኮኖሚ ዕድገት በማሕበራዊ ልማት ወይም እንበል በሕዝብ የኑሮ ሁኔታ መሻሻል ያን ያህል ሲከሰት አልታየም። ድህነት፣ የኑሮ ውድነት፣ የመሠረታዊ ምርቶች የዋጋ ንረትና የወጣቱ ስራ አጥነት ዛሬ ከመቼውም በላይ የሕብረተሰቡ አስቸጋሪ ሁኔታ ነጸብራቆች ናቸው። ለመሆኑ ለምንድነው አገሪቱ እስካሁን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ተስኗት የምትገኘው? በዚህና በአገሪቱ አጠቃላይ የእርሻ ልማት ይዞታ ላይ በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የኤኮኖሚ መምሕር የሆኑትን ፕሮፌሰር ስቴፋን ዴርከንን አነጋግሬ ነበር። ኢትዮጵያ ውስጥ ላለፉት ሃያ ዓመታት የልማት ምርምር ሲያካሂዱ የቆዩት ምሁር የምግብ ዋስትናን ጉዳይ በሁለት መልክ ነው የሚመለከቱት።

“የጠቀስከው የምግብ ዋስትና የሚል አባባል ሕዝብ ራሱን ሊቀልብ በቂ ምግብ ያገኛል ወይ የሚለውን የሚያመለክት ነው። እንግዲህ በዚህ አባባል ኢትዮጵያ ብዙዎች የሚያስፈልጋቸውን ምግብ ለማግኘት በሚችሉበት ደረጃ ላይ አይገኙም። እኔ ነገሩን እርግጥ ለያይቼ ነው የምመለከተው። በመጀመሪያ የወቅቱ የኢትዮጵያ መሠረታዊ ችግር ድህነት ነው። እናም በቂ ገቢ የሌላቸው ሰዎች ጥሩ ሕይወት ለመምራት አይችሉም። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ራሷን ለመቀለብ የሚያበቃት አቅም የላትም ማለትም አይደለም። በኔ አመለካከት የምግብ ዋስትናና ሰዎች ራሳቸውን መቀለበ የመቻላቸው ጥያቄ ዋናው ነገር አይደለም። ይሄ በአገር ውስጥ ምግብ ከማምረቱ የተለየ ጉዳይ ነው። በመሠረቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሻሻል መታየቱ አልቀረም። ግን ሂደቱ በጣም አስችጋሪ ነው። ምኑ ስሕተት፤ ምኑ ትክክል ነው በሚለው በመካከላችን ልዩነት ሊኖር ይችላል። ሆኖም ብዙ የምግብ ዋስትና ችግሮች በመኖራቸው ከአንተ ጋር እስማማለሁ። አዎን ረሃብ አለ፤ ድርቅ አለ! ወደፊት ብዙ ነገር መደረግ እንዳለበትም ግልጽ ነው”

በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና ባለመረጋገጡና አገሪቱ ዛሬም በውጭ ዕርዳታ ላይ ጥገኛ እንደሆነች በመቀጠሏ ከድርቅና ከዝናብ እጦት ባሻገር የመንግሥቱን የእርሻ ልማት ፖሊሲም አንድ የችግሩ መንስዔ አድርገው የሚመለከቱት ብዙዎች ናቸው። ኢትዮጵያ ወስጥ አርሶ-አደሩ የመሬቱ ባለቤት አይደለም። በሌላ በሉል ግን በብዙ ሺህ ሄክታሮች የሚገመት ለም መሬት ለውጭ ባለሃብቶች እንዲከራይ ይደረጋል። ይህ ደግሞ በተለይም ውሉ ግልጽ ባለመሆኑ አከራካሪ መሆኑ አልቀረም። ይሁን እንጂ የኦክስፎርዱ ምሁር ስቴፋን ዴርከን የውጭ ባለሃብቶች መግባት ሌሎች የኤኮኖሚ ዘርፎችንም ወደፊት ለማራመድ በሚያመች መንገድ ከተካሄደ ሊበጅም ይችላል ባይ ናቸው።

“የአገሪቱ የእርሻ ፖሊሲ ባለፉት ሃያ ዓመታት፤ በተለይም ባለፉት ስድሥትና ሰባት ዓመታት የተወሰነ አቅጣጫን ተከትሎ ሲራመድ ቆይቷል። እንደ ልማት ኤኮኖሚ ባለሙያ በአንድ በኩል በሌሎች የአፍሪቃ አገሮች የማናየው ሁኔታ እንዳለ መናገር እፈልጋለሁ። መንግሥት በእርሻው ልማት ዘርፍ ለምሳሌ በመለስተኛ እርሻዎች ደረጃ ዕርምጃ ለማድረግ ቢቀር ፍላጎት አሳይቷል። እርግጥ የሚሰራው ትክክል ነው ወይስ ስህተት ልንከራከር እንችላለን። ግን ሙከራ አይደረግም ለማለት አይቻልም። ሌላው ለታላቅ ባለሃብቶች መሬት መሰጠቱ ተጠቅሷል። እዚህ ላይ ሁለት ነገሮችን ለያይተን ማየት አለብን። አንዱ ትናንሾቹ ገበሬዎች የሚገለገሉበት መሬት ለውጭ ባለሃብቶች መሰጠት ወይም አለመሰጠት ነው። እኔ በበኩሌ የውጩ ተሳትፎ ያስፈልጋል ባይ ነኝ። ኢትዮጵያ በእርሻ ላይ ጥገኛ ከሆነ ኤኮኖሚ ወደ ሌሎች የልማት ዘርፎችም መሻገር መቻል ይኖርባታል። እንግዲህ በጥቅሉ ነገሩ መጥፎ ነው ለማለት አይቻልም። ለነገሩ ኢትዮጵያ ውስጥ የማይታረስ ብዙ መሬት አለ። ይሄው ታዲያ በታላቅ መስኖዎች እንዲለማ፣ መዋቅራዊ መስፋፋት እንዲደረግና አትራፊ በሆነ መንገድ ለማምረት እንዲቻል ሰፊ መዋዕለ-ነዋይን ይጠይቃል። ለኢትዮጵያ ትልቁ ጠቃሚ ነገር ደግሞ ኤኮኖሚዋን ማሳደግና የስራ መስኮችን መፍጠር መቻል ነው። አገሪቱን ለማበልጸግ የተለያዩ መንገዶች መፈለግ ይኖርባቸዋል፤ ወደ ምግብ ዋስትናው ተመልሰን ካሰብን”

ይሁንና ሰፋፊ ለም መሬቶችን የሚይዙት የውጭ ባለሃብቶች የሚሹት በአብዛኛው በውጭ ገበዮች ላይ የሚውል የእርሻ ምርትን ማውጣት ነው። ታዲያ እንዲህ ከሆነ አገር ውስጥ ብዙ ነገር አይቀርም። የአገሪቱ ለም መሬቶች በውጭ ኩባንያዎች መያዝ ከዚሁ ሌላ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለብዙዎች መፈናቀልም ሲሆን የአካባቢን ተፈጥሮ የማስጠበቅ ስጋትንም ማስከተሉ አልቀረም። በተለይ በእንዳሁኑ ዓይነት ሚሊዮኖች በሚራቡበት ወቅት ምግብ እየተመረተ ወደ ውጭ ቢሽጥ ሞራልን የሚነካ እንደሚሆን የሚያስቡት ጥቂቶች አይደሉም። ስቴፋን ዴርከን ግን በጉዳዩ ለየት ያለ አመለካከት አላቸው።

“ትልቅ ችግር ነው ብዬ አላስብም። ምግብ አገር ውስጥ መቅረቱ ሰዎች ያነሰ እንዲራቡ አያደርግም። የምግብ ዋስትና ግንኙነት ያለው ከምግብ ምርት ጋር ሣይሆን ይልቁንም ከገቢ ጋር ነው። ሰዎች መግዛት ከመቻላቸው ጋር! ለምሳሌ ሃብታሞቹ ሳውዲዎች እጅግ ብዙ ገንዘበ ከፍለው ሊገዙ የሚፈልጉትን ከፍተኛ ጥራት ያለው ሩዝ በሰፊው ማምረት ቢቻል የስራ መስኮችን ለማስፋፋት የሚረዳ ይሆናል። በመሠረቱ ኢትዮጵያ ምን ወደ ውጭ ትሸጣለች፤ ምንስ ታስገባለች፤ ይህ አይደለም ወሣኙ ነገር። በመጨረሻ ለኢትዮጵያውያን ብልጽግናና ደህንነት የሚበጀው ይሄ ነው። ለምሳሌ ጀርመንን ብንወስድ የምትፈጀውን ምግብ ሁሉ ራሷ አታመርትም። ወደ ሌላው ዓለም ውድ አውቶሞቢሎችን በመሸጥ፤ በዛ ነው ምግብ የምትገዛው። ኢትዮጵያ እንግዲህ ራሷ ብዙ የማትፈጃቸውን ምርቶች፤ ለምሳሌ ከፍተኛ ጥራት ያለውን ሩዝ ወይም ሌላ ነገር በመሸጥ የሚያስፈልጋትን ብትገዛ ክፉ ነገር የለውም”

ጥያቄው አገሪቱ ይህን ከማድረግ ደረጃ ላይ መድረስ መቃረቡ ቀርቶ በዚያ አቅጣጫ እንኳ እያመራች ነወይ ነው። ለነገሩ ኤኮኖሚውን ዘርፈ-ብዙ ለማድረግ ሁኔታው ያን ያህል የማያመችም አይደለም። ኢትዮጵያ ዛሬ በዓለም ላይ በእጣት ከሚቆጠሩት ምዕራቡ ዓለም በቢሊዮን የሚቆጠር የልማት ዕርዳታ ከሚያቀርብላቸው ታዳጊ አገሮች አንዷ ናት። ሆኖም አገሪቱ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ዛሬም በዝቅተኛ ዕድገት ደረጃ የሚገኙ ተብለው ከተደለደሉት የድሃ ድሃ አገሮች ሰፈር ለመውጣት አልቻለችም። በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝብ ለሕልውናው “ሴፍቲይ-ኔት” በመባል በሚታወቀው የዕርዳታ መረብ ላይ ጥገኛ ነው። ይህ ደግሞ ለዚያውም ወዳጅ-ጠላት መለያ የፖለቲካ መሣሪያ ሆኖ ጥቅም ላይ በመዋል በመንግሥት ላይ ወቀሣን የቀሰቀሰ ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል። ወደ እርሻ ልማቱ መለስ ስንል ለመሆኑ ለምንድነው በአገሪቱ ራስን መቻል ያቃተው? የኦክስፎርዱ ምሁር መፍትሄውን የሕዝብን ገቢ ከማሻሻል ጋር አዛምደው ይመለከቱታል።

“የምግብ መብቃቃት ፖሊሲ ለኢትዮጵያ ተስማሚው ፖሊሲ አይመስለኝም። በደቡብ ኢትዮጵያ የሚገኙ ቡና አምራች ገበሬዎች የቡና ዛፎቻቸውን ቆርጠው በቆሎ እንዲተክሉ ቢደረግ ነገሩ ትክክል አይሆንም። ይብስ ያነሰ ገቢ ነው ሊያገኙ የሚችሉት። በሌላ በኩል የአገሪቱ የእርሻ ልማት የሕዝቡን ገቢ ለማሻሻል ለምንድነው በፍጥነት የማያድገው? ይህ በተወሰነ ደረጃ ካለፉት ዓመታት ፖሊሲዎች ጋር የተሳሰረ ሆኖ ሊታይ ይችላል። የኢትዮጵያ መዋቅራዊ ይዞታ እንደምታውቀው አሁንም እጅግ ደካማ ነው። የተሻለና ዘመናዊ የሆነ የምርት ቴክኒክ በሚገባ ወይም በቂ በሆነ መልክ ለገበሬዎች እንዲቀርብ አልተደረገም። ይህን መንግሥትም ለይቶ ያውቀዋል። በጥቅሉ ግን የእርሻ ልማት ፖሊሲው እንዳለ ፍቱን አልነበርም ለማለት አይቻልም። ችግሩ ከሌሎች በአገሪቱ ጥሩ ሊራመዱ ካልቻሉ ነገሮች ጋርም የተያያዘ ነው። መዋቅራዊ ይዞታ ወዘተ...ገበሬዎች ለምሳሌ በወቅቱ ከፍተኛ ዋጋ ወይም ጥራት ያላቸውን ምርቶች ለማምረት ሲጥሩ አይታዩም። ለዚሁም ምክንያቱ በከተሞች ፍላጎቱ የተስፋፋ አለመሆኑ ነው። እንግዲህ ለሌሎች ከዕድገት ጋር ለተዛመዱ ፖሊሲዎች በቂ ትኩተት አልተሰጠም”

የኢትዮጵያ መንግሥት በአዲስ የአምሥት ዓመት ዕቅዱ መሠረት የእርሻ ምርትን በእጥፍ ለማሳደግ ነው የሚያስበው። አገሪቱ በጥቂት ዓመታት ውስጥ በውጭ የምግብ ዕርዳታ ላይ ጥገኛ ከመሆን እንደምትላቀቅም ተነግሯል። ግን በአሠርተ-ዓመታት ያልሆነው በቅርብ ይሳካል ብሎ ማሰብ የሚቻል ነገር ነወይ? ስቴፋን ዴርከን የብዙዎችን ጥርጣሬ መጋራቱን ነው የሚመርጡት።

“በአጭር ጊዜ የሚሆን አይመስለኝም። የመንግሥትን ዕቅድ በተመለከተ ይህን የምታደርገው ኢትዮጵያ ብቻ አይደለች። ፍላጎትህን ጎላ ካላደረግክ ለውጥ ፈላጊ መስለህ አትታይም። በትራንስፎርሜሺኑ ዕቅድ እንደሆነው በጣም ካጋነንከው ደግሞ ከዚያ ለመድረስ የሚያስፈልገው የምርታማነት ደረጃ እጅግ ከፍተኛ ነው። ይህን ማሟላት አይቻልም። ግቡ ከፍ ብሎ ነው የተቀመጠው ለማለት እወዳለሁ። እርግጥ የዕቅዱ አንዳንድ ይዘቶች ሊደረስባቸው ይችሉ ይሆናል። አገሪቱ አንድ ቀን ከድህነት መውጣቷም አይቀርም። ግን መንገዱ ረጅም ነው የሚሆነው። ኢትዮጵያ ብዙ ችግሮች አሏት። ለምሳሌ የባሕር በር የላትም። እንግዲህ በአምሥት ዓመት ውስጥ አገሪቱን ወደተባለው ደረጃ ማሽጋገር የሚቻል አይሆንም። ቢሆን ላደንቀው የመጀመሪያው በሆንኩ ነበር። ነገር ግን በጣም እጠራጠራለሁ”

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ


Audios and videos on the topic