1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ታሪፍን በየሦስት ወሩ ቢያንስ በ10 በመቶ ልትጨምር ነው

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ነሐሴ 8 2016

የኢትዮጵያ መንግሥት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ታሪፍ በየሦስት ወሩ ቢያንስ በ10% ለመጨመር ተዘጋጅቷል። ጭማሪው መንግሥት ከዓለም ባንክ 1.5 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ እና ብድር ባገኘበት ሥምምነት የተካተተ ነው። በሥራ ላይ ያለው ተመን ዕዳ ክፍያን ጨምሮ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ወጪ የሚሸፍነው 18% ብቻ ነው

https://p.dw.com/p/4jSzo
አምፖል
የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም ባንክ 1.5 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ እና ብድር ባገኘበት ሥምምነት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ታሪፍ በየሦስት ወሩ ቢያንስ በ10% ለመጨመር ግዴታ ገብቷል። ምስል Maksym Yemelyanov/Zoonar/picture alliance

የኢትዮጵያ መንግሥት የኤሌክትሪክ ታሪፍን ቢያንስ በየሦስት ወሩ በ10 በመቶ ሊጨምር ነው

የኢትዮጵያ መንግሥት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ታሪፍን በየሦስት ወሩ ቢያንስ በ10 በመቶ ለመጨመር ተዘጋጅቷል። የታሪፍ ጭማሪው የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም ባንክ ጋር በተፈራረመው እርዳታ እና ብድር ሊከናወኑ ከታቀዱ ሥራዎች መካከል አንዱ ነው። መንግሥት “ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ ዘላቂ እና አካታች ዕድገት የልማት ፖሊሲ ክወና” አንድ ቢሊዮን ዶላር እርዳታ እና 500 ሚሊዮን ዶላር ብድር ያገኘበት ሥምምነት የተፈረመው ባለፈው ነሐሴ 23 ቀን 2016 ነበር።

በሥምምነቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ተግባራዊ ሊያደርግ ግዴታ ከገባባቸው ጉዳዮች መካከል “የኢነርጂ ዘርፉን የፋይናንስ ዘላቂነት ማጠናከር” የሚለው ይገኝበታል። ዓለም ባንክ ይፋ ያደረገው ሰነድ የኢትዮጵያ መንግሥት የአራት ዓመታት የኤሌክሪክ ታሪፍ ማሻሻያ ማጽደቁን ያሳያል። በማሻሻያው መሠረት በመጀመሪያው ዓመት ብቻ በየሦስት ወሩ ደንበኞች ለኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚከፍሉት ታሪፍ ቢያንስ በ10 በመቶ ይጨምራል።

የዕቅዱ የመጨረሻ ግብ በሚቀጥሉት አራት ገደማ ዓመታት ማለትም እስከ ጎርጎሮሳዊው 2028 የሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ዘርፍ የሥራ ማስኬጃ እና የዕዳ ክፍያ ወጪውን ሙሉ በሙሉ እንዲመልስ ማድረግ ነው። የኤኮኖሚ ባለሙያው አቶ ኢድሪስ ሰዒድ “የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዕዳቸውን መክፈል እስከማይችሉበት ደረጃ በመድረሱ ይኸ ማሻሻያ አስፈላጊ ሆኖ ተቀምጧል” ሲሉ ይናገራሉ።

ችግሩ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የክፍያ ተመን ዝቅተኛ በመሆኑ የተከሰተ መሆኑን የገለጹት አቶ ኢድሪስ ሁለቱ ተቋማት “በፋይናንስ ዘላቂ እንዲሆኑ እና የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን በሀገሪቱ ማስፋፋት እንዲቻል ከተፈለገ ራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስ አለባቸው የሚል ድምዳሜ ላይ የተደረሰ ይመስለኛል” ሲሉ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ
ዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ብድር እና እርዳታ የሰጠበትን ሥምምነት የተፈራረሙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ እና የባንኩ የኢትዮጵያ ቢሮ ዳይሬክተር ማርያም ሳሊም ናቸው። ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ታሪፍ ከቀጠናው ሀገራት ሲነጻጸር ዝቅተኛ መሆኑን የገለጹት የኤኮኖሚ ባለሙያው “ማሻሻያው አስፈላጊ ነው” የሚል አቋም አላቸው። “አለበለዚያ ዘላቂ ያልሆነ የኢነርጂ ዘርፍ ይኖረን እና መንግሥት በተለያዩ ዕቅዶች ያስቀመጠውን የተደራሽነት ግብ ለማሳካት ትልቅ እንቅፋት” እንደሚሆን አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ከጎርጎሮሳዊው 2006 እስከ 2018 ባሉት ዓመታት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ታሪፍ ምንም አይነት ለውጥ እንዳልተደረገበት ዓለም ባንክ ይፋ ያደረገው ሰነድ ይጠቁማል። በሰነዱ መሠረት ከ2018 እስከ 2021 ባሉት ዓመታት በአንጻሩ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ በ180 በመቶ እንዲጨምር ተደርጓል። ይሁንና መንግሥት የሚሰበስበው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ታሪፍ ከተቋማቱ የሥራ ማስኬጃ እና የዕዳ ክፍያ መሸፈን የቻለው 18 በመቶ ብቻ ነው። 

ነባሩን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ታሪፍ “መንግሥት ብዙውን እየደጎመ” መቆየቱን የሚናገሩት ኢድሪስ ዋና ዓላማው “በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ በሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ የሚኖረውን ጫና መቀነስ ነው” ሲሉ ያስረዳሉ። ይሁንና ኢትዮጵያ የምትጠቀምበት የድጎማ ሥርዓት መክፈል የሚችሉትን ጨምሮ “ሁሉንም ማኅበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ” በመሆኑ “ውጤታማ አይደለም” የሚል አቋም አላቸው።

የመንግሥት ንብረት የሆኑት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በፋይናንስ ረገድ የዘላቂነት ችግር ያለባቸው፤ “ከፍተኛ የፊስካል ሥጋት” የፈጠሩ እንደሆኑ የዓለም ባንክ ሰነድ ይጠቁማል።

ታላቁ የኅዳሴ ግድብን ጨምሮ ግዙፍ የኃይል ማመንጫዎች በማስገንባት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተለይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ቅርቃር ውስጥ ከከተቱ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አንዱ ነው። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሰጠው 2.8 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ብድር የተበላሸ ብድር እንደሆነ የዓለም ባንክ ሰነድ ያሳያል።

ታላቁ የኅዳሴ ግድብ
ንግድ ባንክ ታላቁ የኅዳሴ ግድብን ጨምሮ ግዙፍ የኃይል ማመንጪያዎች በማስገንባት ላይ ለሚገኘው ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሰጠው 2.8 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ብድር የተበላሸ ብድር እንደሆነ የዓለም ባንክ ሰነድ ያሳያል።ምስል AFP/Maxar Tech

ከባንኮች አጠቃላይ ሐብት 58 በመቶ ገደማ ድርሻ ያለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደ የኢትዮጵያ ኤክትሪክ ኃይል ላሉ ተቋማት በሰጠው የተበላሸ ብድር ምክንያት ከፍተኛ ችግር ውስጥ ወድቋል። የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የወሰዱት ብድር ከባንኩ አጠቃላይ ሐብት 60 በመቶ ድርሻ አለው። አብዛኛው ደግሞ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የተሰጠ ነው። ለተቋማቱ ብድር ሲሰጥ መንግሥት የገባውን ዋስትና ማክበር አልቻለም።

የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ ለንግድ ባንክ የኢትዮጵያ መንግሥት ዋስ በመሆን “ብዙ የብሔራዊ ባንክ መመሪያዎች ተለሳልሰው” ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ብድር መሰጠቱ የችግሩ ዋንኛ መሠረት እንደሆነ ይናገራሉ። ድርጅቶቹ ብድሩን መክፈል ተስኗቸው ወደ ኢትዮጵያ መንግሥት ይዙር ሲባል ዶክተር አብዱልመናን እንደሚሉት “በቀጥታ የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለ ዕዳ ሆነ ማለት ነው።”

የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ንግድ ባንክ ከካፒታሉ በላይ ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ብድር እንዲሰጥ “በመደበኛ የባንክ አሠራር በፉጹም መፈቀድ አልነበረበትም” ሲሉ ይተቻሉ። የብሔራዊ ባንክ፣ የንግድ ባንክ፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እና የመንግሥት ባለሥልጣናት ሀገሪቱን ለከፍተኛ ዕዳ ለዳረገው ውሳኔ እስካሁን ተጠያቂ አልሆኑም።

መንግሥት ተግባራዊ በሚያደርገው የኤኮኖሚ ማሻሻያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና ከዓለም ባንክ ጋር ባደረጋቸው ድርድሮች አከራካሪ ከነበሩ ጉዳዮች አንዱ የንግድ ባንክ እጣ ፈንታ እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናግረዋል። ባንኩን ከውድቀት ለማዳን የፋይናንስ ዘርፍ ማጠናከሪያ ከተባለው ፕሮጀክት (Financial Sector Strengthening Project) ዓለም ባንክ 700 ሚሊዮን ዶላር ለመንግሥት ሰጥቷል።

መንግሥት በበኩሉ የንግድ ባንክን ካፒታል ለማሳደግ እና የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ዕዳ ለመሰረዝ የ870 ቢሊዮን ብር ቦንድ እንዳወጣ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ይፋ ያደረገው ሰነድ ያሳያል። በቦንድ መልክ የተሰጠው 870 ቢሊዮን ብር የዕዳ እና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የነበረባቸውን የንግድ ባንክ ዕዳ ሙሉ በሙሉ የሚሰርዝ ነው።

ከዓለም ባንክ ጋር በተፈረመው ሥምምነት መንግሥት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትን ጨምሮ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ግልጽነት ለማጠናከር ግዴታ ገብቷል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ንግድ ባንክን ከውድቀት ለማዳን ዓለም ባንክ 700 ሚሊዮን ዶላር ሲሰጥ የኢትዮጵያ መንግሥት የ870 ቢሊዮን ብር ቦንድ እንዳወጣ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ይፋ ያደረገው ሰነድምስል Eshete Bekele/DW

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የታሪፍ ማሻሻያ ለማድረግ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል። ለደንበኞች የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት፣ የኃይል ማመንጫ እና ማሰራጫ መስመር ግንባታዎችን ለማፋጠን፣ እንዲሁም የተቋማቱን የብድር ጫና ለመቀነስ ማሻሻያው ያስፈልጋል ተብሎ ታምኖበታል።

የኤኮኖሚ ባለሙያው አቶ ኢድሪስ የታሪፍ ማሻሻያው “በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ማኅበረሰቦችን ፋታ በሚሰጥ ሁኔታ የተዋቀረ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። በማሻሻያው “ብዙ መብራት የሚጠቀሙ ሰዎች ብዙ እንዲከፍሉ ይደረጋል።” ለዚህም በወር ከ50 ኪሎዋት በታች የሚጠቀሙ ማኅበረሰቦች ዝቅተኛ ክፍያ እንዲከፍሉ ሊደረግ መታቀዱን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ማሻሻያው ተግባራዊ ተደርጎ የሚሰበሰበው ገቢ ግን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሥራ ማስኬጃ እና የዕዳ ክፍያ ወጪ ሙሉ በሙሉ ሊሸፍን የሚችል አይደለም። ባለፈው ዓመት ተቋማቱ ከደንበኞቻቸው የሚሰበስቡት ገቢ ከሥራ ማስኬጃ እና የዕዳ ክፍያ ወጪያቸው 18 በመቶ ብቻ ይሸፍን ነበር። ማሻሻያው ተግባራዊ ከሆነ በኋላ በጎርጎሮሳዊው 2027 መጨረሻ ይኸ ወደ 70 በመቶ ከፍ እንደሚል ይጠበቃል። ዘርፉ ከማሻሻያውም በኋላ 3.4 ቢሊዮን ዶላር የፋይናንስ ጉድለት እንደሚኖርበት የዓለም ባንክ ሰነድ ይጠቁማል።

የኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ የሚጨምረው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ተግባራዊ ባደረገው የኤኮኖሚ ማሻሻያ ምክንያት ዜጎች የዋጋ ግሽበት በገጠማቸው ወቅት ነው። ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት እስከ 30 በመቶ የደረሰ የዋጋ ግሽበት አስተናግዳለች።

ብር
የኤሌክትሪክ አገልግሎት ታሪፍ ጭማሪ የብርን የመግዛት አቅም ካዳከመው የውጪ ምንዛሪ ግብይት ማሻሻያ ጋር ተደማምሮ ኢትዮጵያውያንን ሊፈትን እንደሚችል ባለሙያዎች ይሰጋሉ። ምስል MICHELE SPATARI/AFP

“የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ማሻሻያ ተካሒዷል” የሚሉት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን የዓለም ባንክ ሰነድ በ2017 አጋማሽ የዋጋ ግሽበት ከ35 እስከ 40 በመቶ ሊደርስ እንደሚችል መጥቀሱን በዜጎች ላይ ለሚደራረበው ችግር እንደ ማሳያ ያነሱታል። “ይኸ ሁሉ ችግር ባለበት እንደገና የኤሌክትሪክ ታሪፍ መጨመሩ ነገሮችን ማባባስ ነው የሚሆነው” የሚሉት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው መጪው ጊዜ ለኢትዮጵያውያን “በጣም ከባድ” እንደሚሆን ይሰጋሉ።

አቶ ኢድሪስ የመንግሥት የኤኮኖሚ ማሻሻያ ተጨማሪ የዋጋ ግሽበት ጫና ሊያስከትል እንደሚችል ቢስማሙም ማሻሻያው ግን አስፈላጊ እንደሆነ ይሞግታሉ። “የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በገንዘብ ራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስ ካልቻሉ” ከኤሌክትሪክ ኃይል ለራቀው 46 በመቶ ኢትዮጵያዊ አገልግሎቱን ማዳረስ እንደማይቻል ያስረዳሉ።  

“ማሻሻያው የተወሰነ የዋጋ ግሽበት ጫና ሊኖረው ይችላል” የሚሉት አቶ ኢድሪስ የክፍያ ጭማሪው ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የማኅበረሰብ ክፍል እንዳይጎዳ ሆኖ ከተሻሻለ “የዋጋ ግሽበት ጫናውን መቀነስ ይቻላል የሚል ዕምነት አለኝ” በማለት አስረድተዋል።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ