ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ቀውስ ያሰጋት ይሆን? | ኤኮኖሚ | DW | 30.03.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ቀውስ ያሰጋት ይሆን?

የኢትዮጵያ መንግስት ለመሰረተ-ልማት ግንባታዎች ከቻይና ብቻ 17.6 ቢሊዮን ዶላር ተበድሯል። የኢትዮጵያ መንግስት ለሰፋፊ የመሰረተ-ልማት ግንባታዎች እና የማምረቻ ዘርፉን ለማሳደግ ከውጭ አገራት የሚበደረው ገንዘብ መጠን ያሰጋቸው ባለሙያዎች ግን ከአመት አመት በሚጨምረው ብድር ምክንያት አገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ያሰጋታል እያሉ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:30

ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲ-47 በተባለች አውሮፕላን የመጀመሪያ በረራውን ከአዲስ አበባ በአስመራ ወደ ግብጽ ዋና ከተማ ካይሮ ያደረገው መጋቢት 30 ቀን 1938 ዓ.ም. ነበር። ትራንስ ዎርልድ ከተሰኘ የዩናይትድ ስቴትስ አየር መንገድ ጋር በሽርክና የተመሰረተው ኩባንያ 70ኛ የልደት ምስረታውን እያከበረ ነው። ከሌሎች የኢትዮጵያ መንግስታዊም ይሁን መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በተለየ አገሪቱ ያለፈችበትን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ውጣ ውረድ የተሻገረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬ 92 ዓለም አቀፍ እና 19 የአገር ውስጥ መዳረሻዎች ያሉት ሲሆን በአፍሪቃ በስኬታማነቱ ከቀዳሚዎቹ ተርታም ይመደባል።

አየር መንገዱ በነደፈው 'ርዕይ 2025' መሰረት ምቹ እና ደህነቱ የተጠበቀ የበረራ አገልግሎት ለደንበኞቹ በማቅረብ በጎርጎርሳዊው 2025 ዓ.ም. በአፍሪቃ ግንባር ቀደም አገልግሎት አቅራቢ የመሆን እቅድ ሰንቋል።

በጎርጎሮሳዊው 2015 ዓ.ም. ብቻ 1.7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ የውጭ እዳ ካለባቸው የመንግስት ኩባንያዎች መካከል አንዱ ነው።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፤ስኳር፤ባቡር መንገድ ፤የባህር ትራንስፖርት እና ኢትዮ-ቴሌኮም ኮርፖሬሽኖች ከውጭ አገራት እና ኩባንያዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ የተበደሩ ናቸው። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ከሁለት አመት በፊት ባወጣው ዘገባ በጎርጎሮሳዊው 2012/13 የበጀት አመት መጠናቀቂያ የኢትዮጵያ የውጭ ብድር 11.2 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን አስታውቆ ነበር። ባለፉት ጥቂት አመታት ለኢትዮጵያ የመሰረተ-ልማት ግንባታዎች እና ማስፋፊያዎች ብድር በማቅረብ ረገድ ቻይና፤ህንድ እና ቱርክን የመሳሰሉ አገራት ቀዳሚ ሆነዋል።

ከዓመት ዓመት እድገት የሚያሳየው የኢትዮጵያ የብድር መጠን የሚያሳስባቸው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ከሚያነሷቸው ጥያቄዎች መካከል ተበዳሪ ተቋማት አሊያም መንግስት ያላቸው የመክፈል አቅም እና አበዳሪዎች ሊወስዱት የሚችሉት እርምጃ ይጠቀሳሉ። ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ በአዲስ አበባ እና ለንደን ዩኒቨርሲቲዎች የኢኮኖሚክስ ዶክተር ናቸው። ፕሮፌሰሩ ከሌሎች የሙያ አጋሮቻቸው ጋር አዲስ አበባ ላይ የማህበራዊ ጥናት ተቋም ባዘጋጀው ጉባኤ ላይ ሲመክሩ ኢትዮጵያ ያለባት የብድር መጠን በጨመረ ቁጥር ለአደጋ ያጋልጣታል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ አዲስ አበባ ላይ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ የኢትዮጵያ መንግስት ባለፉት አመታት ለመሰረተ-ልማት ግንባታዎች ከቻይና 17.6 ቢሊዮን ዶላር፤ ከቱርክ ወደ ሶስት ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም ከህንድ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር መበደሩን ገልጠዋል። ፕሮፌሰሩ ከውጭ አገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚፈሰውን መዋዕለ-ንዋይ ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆነ በማለት ይከፍሉታል። በኢትዮጵያ መንግስት ለሚከወኑ እቅዶች ከውጭ አገራት የሚገኝ የብድር ገንዘብን ቀጥተኛ ያልሆነ ከሚለው ምድብ ውስጥ አስቀምጠውታል።

በዓለም ባንክ መረጃ መሰረት ኢትዮጵያ ከጎርጎሮሳዊው 2012-2016 ባሉት አመታት ስድስት ቢሊዮን ዶላር ከባንኩ ተበድራለች። የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው ዓመት መስከረም ወር ለዓለም ገበያ ባቀረበው የዩሮ ቦንድ አማካኝነት 1.5 ቢሊዮን ዶላር ተበድሯል። በበተጻራሪው አገሪቱ ከውጭ ንግድ የምታገኘው ገቢ ባለፈው ዓመት ከነበረበት ሶስት ቢሊዮን ዶላር ወደ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ ብሏል። ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳን የመሳሰሉ የኢኮኖሚ ልሒቃን ኢትዮጵያ ኤኮኖሚዋን ከቀውስ ለመታደግ የንግድ ሚዛኑን ማስተካከል፤በየዓመቱ ጭማሪ የሚያሳየውን ብድር መጠን መፈተሽ እንዳለባት ይመክራሉ።

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic