ኢትዮጵያ፤ የተቃዉሞዉ አንደኛ ዓመት | ዓለም | DW | 14.11.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ኢትዮጵያ፤ የተቃዉሞዉ አንደኛ ዓመት

የኢትዮጵያ መንግሥት ተቺ፤ ተቃዋሚ ምናልባትም መካሪዎቹን የሚወነጅልበት ቅፅሎች አሉት።«አሸባሪ፤ የአሸባሪ ተባባሪ፤ ፅንፈኛ ዲያስፖራ፤ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓትን የሚንድ» ወዘተ።ጋዜጠኞች ጭብጥ ይዘዉ ሲዘግቡ ደግሞ መንግሥት የጋዜጠኝነት መታወቂያ የለጠፈላቸዉን ካድሬዎቹን ሐሰት «እያጎረሰ» በሚቆጣጠራቸዉ መገናኛ ዘዴዎቹ ቅጥፈት «ያስገሳቸዋል።»

አውዲዮውን ያዳምጡ። 13:06
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
13:06 ደቂቃ

ኢትዮጵያ፤ የተቃዉሞዉ አንደኛ ዓመት

 

ከትንሺቱ የምዕራብ ኦሮሚያ ከተማ ጊንጪ እስከ ታሪካዊቷ የኢትዮጵያ ከተማ ጎንደር፤ ከርዕሠ-ከተማ አዲስ አበባ እስከ ደቡብ ኢትዮጵያ ኮንሶ፤ ከአማራ መስተዳድር ርዕሰ ከተማ ባሕርዳር እስከ ምሥራቅ ኢትዮጵያ አወዳይ የተቀጣጠለዉ ሕዝባዊ ተቃዉሞ ዓመት ደፈነ።ቅዳሜ።ተቃዉሞዉ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት በሃያ-አምስት ዓመት ያገዛዝ ዘመኑ ከገጠመዉ ፈተናዎች ሁሉ ከባዱ እና ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ነዉ።የመንግሥት ተቃዉሞዉን ለማስቆም ጦር ሠራዊት ከማዝመት እስከ የባለሥልጣናት ሹም-ሽር፤ የአዲስ አበባ ከተማ ዕቅድን ከመቀየር፤ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከ መደንገግ የሚደርሱ እርምጃዎችን ወስዷል።ዉጤቱ? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

                              

አምና በዚሕ ሰሞን ጊንጪ ላይ ለተቃዉሞ አደባባይ የወጣዉ ሕዝብ ጥያቄ ግልፅና ቀላል ነበር።የአዲስ አበባ የተቀናጀ ማስተር ፕላን በተባለዉ ዕቅድ የኢትዮጵያ መንግሥት የአካባቢዉን መሬት ከገበሬዎች ቀምቶ ለባለ ሐብቶች መስጠቱን ያቁም የሚል።አፀፋዉ ግን ያዩ እንደሚሉት ከባድ ነበር።ግድያ፤ድብደባ፤ እስራት እና አፈሳ።

የአይን ምስክሮች እንደሚሉት ተቃዉሞዉ፤ ተቃዋሚዉ ያነሳዉ ጥያቄ እና የፀጥታ አስከባሪዎች የሐይል እርምጃ ጊንጪ ላይ የተጀመረ ዓይደለም።

                                 

ተቃዉሞዉ በአብዛኛዉ የኢትዮጵያ ግዛቶች መዛመቱ-አንድ፤ የተቃዉሞዉ  ምክንያት ከሐብት ክፍፍል ወይም ከመሬት

ባለቤትነት ወደ አስተዳደር መጓደል፤ ከመካለል፤ወደ ማንነት፤ ከሰብአዊ መብት ወደ ፍትሕ መከበር ማደጉ-ሁለት፤ ዓመት መድፈኑ-ሰሰዎስት የጊንጪዉን የመጀመሪያ ያደርገዋል።የፀጥታ አስከባሪዎች የሐይል እርምጃም እየተጠናከረ፤እየከፋ፤እየሰፋ ሔደ።አፈናዉ በመጠናከሩ የቢቢሲዋ ዘጋቢ ያኔ እንዳለችዉ የመንግሥት ፀጥታ አስከባሪዎች የገደሉትና ያሰሩትን ሰዉ ብዛት፤ የገደሉና ያሰሩበትን ትክክለኛ ምክንያት ለመዘገብ የፈለጉ ነፃ መገናኛ ዘዴዎች መረጃ ለማግኘት ተቸግረዉ ነበር።ዛሬም ብሷል።

                        

«በተለያዩ ከተሞች ባብዛኛዉ ተማሪዎች እና ሌሎችም በአደባባይ እየተቃወሙ ነዉ።መረጃ ማግኘት በጣም፤ በጣም አስቸጋሪ መሆኑም ተዘግቧል።ይሕ ባለሥልጣናቱ ምን ያሕል አፋኞች እንደሆኑ የሚያመለክት ነዉ።ሰዎች እንደሚናገሩት አምቦ ከተማ ብቻ በርካታ ተማሪዎች በጥይት ተደብድበዉ ተገድለዋል።ሌሎች ቆስለዋል።»

መግደል፤ አካል ማጉደል፤ ማሰር ማፈኑ ግን ተቃዉሞዉን በየአካባቢዉ ከማቀጣጠል ባለፍ የተከረዉ ነገር የለም።ከጊንጪ አወዳይ፤ ከአምቦ ሻሸመኔ፤ ከኮፈሌ ባሌ እያለ ኦሮሚያን አዳርሶ ጎንደር ገባ።

ኮንሶ ቀጠለ።ደብረዘይትም።ግድያ፤እስራት፤ አፈናዉም ተጠናቀረ።ፀጥታ አስከባሪዎች የሚወስዱት የሐይል እርምጃ ተቃዉሞዉን ባለማስቆሙ መንግሥት መስከረም ላይ ያስቸኳይ ጊዘ አዋጅ ደነገገ።ከጊንጪዉ ተቃዉሞ የመስከረሙ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከ ተደነገበት ጊዜ ድረስ በአብዛኛዉ ፀጥታ አስከባሪዎች በተኮሱት ጥይት ከ800 በላይ ሰዎች መገደላቸዉን የተለያዩ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች አስታዉቀዋል።አንዱ አምንስቲ ኢንተርናሽናል ነዉ።

የአምንስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅ አፍሪቃ አጥኚ አቶ ፍሰሐ ተክሌ በቅርቡ እንዳሉት የተገደለዉ ሰዉ ቁጥር ከ800 ቢበልጥ እንጂ አያንስም።በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ታስረዋል።የደረሱበት ያልታ

ወቁ፤ የቆሰሉና የተሰደዱትን ብዛት ያወቀ አይደለም የገመተም የለም።በንብረት ላይም ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።የዉጪ ባለሐብቶች ሐገሪቱን ጥለዉ ወጥተዋል።የኢትዮጵያ መንግሥት በአስር የሚቆጠሩ ፋብሪካዎች፤ በርካታ መኪኖችና ሌሎች ቁሳቁሶች መጋየታቸዉን እስታዉቋል።የኪሳራዉን መጠን ግን እስካሁን በይፋ አላስታወቀም።

የመብት ተሟጋቾች፤ መንግሥት ተቃዉሞዉን ለማፈን የደነገገዉን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን «የሕዝብን ሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይበልጥ የሚደፈልቅ» ብለዉታል።የቀድሞዉ የኢትዮጵያ የሕዝብ ተዋካዮች ምክር ቤት ብቸኛ የተቃዋሚ ፓርቲ እንደራሴ አቶ ግርማ ሰይፉ ደግሞ አዋጁን እንዲሕ ነበር የገለፁት።

                            

የአዉሮጳ ሕብረት እና ዩናይትድ ስቴትስም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት የዜጎች መብቶች እንዳይደፈለቁ አደራ ብለዋል።ኢትዮጵያዊዉ የፍልስፍና ምሁር ዶክተር ዳኛቸዉ አሰፋ ደግሞ አዋጁን መንግሥት እራሱን ከሕግ ማዕቀፍ ያወጣበት በማለት ገልፀዉታል።

                            

የኢትዮጵያ መንግሥት ተቺ፤ ተቃዋሚ ምናልባትም መካሪዎቹን ሁሉ የሚወነጅልበት የተለያዩ ቅፅሎች አሉት።«አሸባሪ፤ የአሸባሪ ተባባሪ፤ ፅንፈኛ ዲያስፖራ፤ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓትን የሚንድ» ወዘተ።ጋዜጠኞች ጭብጥ ይዘዉ ሲዘግቡ ደግሞ መንግሥት የጋዜጠኝነት መታወቂያ የለጠፈላቸዉን ካድሬዎቹን ሐሰት «እያጎረሰ» በሚቆጣጠራቸዉ መገናኛ ዘዴዎቹ ቅጥፈት «ያስገሳቸዋል።»

በተቺ ተቃዋሚ፤ በጋዜጠኞች እና በመብት ተሟጋቾች ላይ የመንግሥት ባለሥልጣናት የሚያወርዱት

የስድብ ናዳ፤ አፈሳም ሆነ እስራት በመንግሥት ላይ የተነሳዉን ሕዝባዊ ተቃዉሞ አቅጣጫ ለማሳት እስካሁን የተከረዉ አለመኖሩ ነዉ ዚቁ።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም የሕዝብን ጥያቄ አዳፈነ እንጂ መልስ አልሆነም።አዋጁ ከተደነገ ወዲሕ ኢትዮጵያ በአብዛኛዉ ከኢንተርኔት ዓለም ተቋርጣለች።ከዉጪ የሚያሰራጩ ነፃ መገናኛ ዘዴዎች ከአዋጁ በፊትም በኋላም ይታፈናሉ።አዋጁ የሰዎችን የእርስበርስ እንቅስቃሴ ገድቦታል።አስፈርቷል የነጆዉ ነዋሪ እንዳሉት ደግሞ አዋጁ ወንዱን ጭምር «እያስማጠዉ» ነዉ።

                             

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ያጣራል ተብሎ የተሰየመዉ ቦርድ የነጆዉ ነዋሪ እንዳሉት ሥለሚገደሉ፤ ሥለሚቀጠቀጡት፤ ሥለሚጠፈጠፉት ኢትዮጵያዉያን እስካሁን ያለዉ ነገር የለም።

ሥለተወረሰ ንብረት፤ ሥለተዘረፈ ሐብት፤ ሥለተዘጋ ተቋምም ምንም አልተናገረም።ባለፈዉ አንድ ወር ዉስጥ ከአስራ-አንድ ሺሕ ስድት መቶ በላይ ሰዎች መታሰራቸዉን ግን ቦርዱ ነግሮናል።የጎንደሩ መምሕር ይሕን ቁጥር አይቀበሉትም።ጎንደር እንበለ ወጣት ቀርታለች።

                            

የነጆዉ ነዋሪ አከሉበት።መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ከደነገገ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ የካቢኔ ሽም ሽር አድርጓል።የገዢ ፓርቲ ተጣማሪዎች በየአካባቢያቸዉ ጥልቅ እና ተሐድሶ የሚሉትን ስብሰባ አድርገዋል።

የአምስቲ ኢተርናሽናሉ አጥኚ እንደሚሉት ግን ሕዝብ ባደባባይ የተሰለፈዉ የካቢኔ ሹማምንት እንዲቀያየሩ ለመጠየቅ አይደለም።

                               

የቀድሞዉ የምክር ቤት እንደራሴም በዚሕ ይስማማሉ።ተቃዋሚዎችን መግደል፤ ማሰር፤ ማጋዙ መፍትሔ አልሆነም።የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈናን ማጠናከር እንጂ በመብት ተሟጋቾች እና በተቃዋሚዎች ዘንድ ከመፍትሔ አልተቆጠረም።የካቢኔ ሹም ሽር የሕዝብ ዋና ጥያቄ አይደለም።አንድ ቦታ ግን የሆነ መፍትሔ መኖር አለበት፤ መደረግም አለበት።ዶክተር ዳኛቸዉ ሕዝብ ገብቶታል ይላሉ።

                                         

ለአቶ ግርማ «መፍትሔዉ ቀላል ነዉ»ተቃዉሞዉ የተቀሰቀሰዉ ገዢዉ ፓርቲ እና አጋሮቹ በመቶ፤ በመቶ ድምፅ መመረጡን ባስታወቀ በመንፈቁ፤ በመቶ በመቶ ድምፅ ያስመረጣቸዉ እንደራሴዎቹ የመጀመሪያ ጉባኤያቸዉ ባደረጉ፤ ወይም የጠቅላይ ሚንስትር ሐይለማርያም ካቢኔ ቃለ መሐላ በፈፀመ በወሩ ነበር።አምና ጥቅምት።ገዢዉ ፓርቲ በመቶ በመቶ ድምፅ አሸነፍኩ ባለ በመፈንቁ ይሕን ያሕል ተቃዉሞ ሲገጥመዉ የተቃዉሞዉን ምክንያት መመርመር፤ የሕዝብን ጥያቄ ማድመጥ ሁነኛ መፍትሔዎችን ለመፈለግ መጣር ነበረበት።ግን የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ይሕን ለማድረግ የሐላፊነት ስሜት፤ ስነልቡና ከሁሉም በላይ ብልሕነትን ይጠይቃል። እስኪ ቸር እንመኝ።

ነጋሽ መሐመድ 

አርያም ተክሌ

 

 

 

 

 

Audios and videos on the topic