ኢትዮጵያ የምርጫ ዝግጅት፤ክፍፍልና ዉዝግብ | ኢትዮጵያ | DW | 02.02.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ የምርጫ ዝግጅት፤ክፍፍልና ዉዝግብ

አምባገነን፤ ወታደራዊ፤ ሶሻሊስታዊ፤ ጦረኛ እየተባለ የሚወገዝ፤የሚወቀስ፤ የሚተቸዉ የደርግ ሥርዓት ከተወገደ ሃያ-አራት ዓመት ሊደፍን እነሆ ወራት ቀሩት።ያኔ የነበረዉ ተስፋ ወይም ቃል የተገባዉ የመድብለ ፓርቲ፤ የዴሞክራሲ፤ የፍትሐዊ ሥርዓት ግንባታ፤ እዚሕ ደርሷል።ከእንግዲሕስ?

ለኢትዮጵያ ለአምስተኛዉ ብሔራዊ ምርጫ መዘጋጀትዋ ሲነገር፤ በምርጫዉ ይሳተፋሉ ተብለዉ ከሚጠበቁት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ሁለቱ ብሔራዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁለትም-አራትም፤ ወይም ሁለትም ምንምም መሆናቸዉን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባለፈዉ ሐሙስ አስታወቋል።የፓርቲዎቹ ክፍፍል፤ የምርጫ ቦርድ ዉሳኔና የምርጫዉ መሳናዶ ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ አብራችሁን ቆዩ።

በኢትዮጵያ ታሪክ የተሻለ ነፃነት፤ ፍትሐዊነትና ግልፅነት እንደተንፀባረቀበት በተመሠከረለት 1997 አጠቃላይ ምርጫ ጠንካራ ተቃዋሚ ተፎካካሪ የበረዉን የአራት ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ቅንጅት የመሠረቱት ፖለቲከኞች የጋራ ቅንጅታቸዉን ወደ አንድ ፓርቲ መለወጥ አይደለም እንደተቀናጀ መቀጠል እንኳን አልቻሉም።

በምርጫዉ ዉጤት ዉዝግብ፤ በግጭት፤ ግድያ፤ በገዢዉ ፓርቲ ጠንካራ ተፅዕኖ መሐል የጠንካራዉ ቀንጅት መሪዎች የገጠሙት እስጥ አገባ ንሮ ቅንጅቱን አመት ባልሞላ እድሜ በትኖታል።የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፈረሰዉን ቅንጅት ስምና ፈቃድ ያኔ ብዙም ለማይታወቁት ለአቶ አየለ ጫሚሶ ለማስረከብ ብዙ ከሚታወቁት የቅንጅት መሪዎች አብዛኞቹ አንድም ወሕኒ እስኪወረወሩ፤ አለያም ምክር ቤት እስኪገቡ፤ ሌሎቹ እስኪበተኑ እንኳን አልጠበቀም።

ጥቅምት 1998-አቶ አየለ ጫሚሶ የሚመሩት ቡድን የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፍቃን ተረከበ።

ዘንድሮ በዘጠነኛ ዓመቱ-ከአዲስ አበባ የተሰማዉ፤ ታሪክ እራሱን ደገመ ያሰኝ ይሆናል።እስካለፈዉ ሐሙስ ድረስ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ (አንድነት) ፓርቲ መሪዎች የነበሩት አቶ በላይ ፍቃዱ፤ አቶ ተክሌ በቀለ፤ አቶ ግርማ ሰይፉ እና ሌሎች የፖለቲካ ጓዶቻቸዉ፤ የድሕረ 1997ቱን ኢንጂነር ሐይሉ ሻዉልን፤ አቶ ልደቱ አያሌዉን፤ ወይም ዶክተር ብርሐኑ ነጋን፤ መሆን አለመሆናቸዉ በርግጥ አለየም።

አቶ ትዕግስቱ አወሉ ግን 1998ቱን አየለ ጫሚሶ መሆናቸዉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባለፈዉ ሐሙስ አወጀ።የቦርዱ ዋና ፀሐፊ አቶ ነጋ ዱፌሳ እንዳነበቡት።

በምርጫ ቦርድ ቋንቋ «የአቶ በላይ ፍቃዱ ቡድን» የቦርዱን ዉሳኔ የገዢዉ ፓርቲ ኢሕአዴግ ደባ ዉጤት ብሎታል።እስከ ሐሙስ ድረስ የአንድነት ፓርቲ ተጠባባቂ የሕዝብ ግንኙነት ሐላፊ የነበሩት አቶ አስራት አብረሐም እንደሚሉት አንድነት ባለፈዉ ሐሙስ «ተዘረፈ»። የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትም ኢትዮጵያ ዉስጥ «ተቀበረ።»

አቶ አበባዉ መሐሪና አጋሮቻቸዉ 1998 አየለ ጫሚሶን ወይም የዘንድሮዉን ትዕግስቱ አወሉን ፖለቲካዊ አቋም መጋራታቸዉ ሲበዛ ያጠራጥራል።አቶ ማሙሽ አማረና ጓዶቻቸዉ ከአቶ በላይ ፍቃዱ፤ ከአቶ ተክሌ በቀለ፤ ወይም ከአቶ ግርማ ሰይፉ ጋር የሚያቀራርባቸዉ የፖለቲካ መርሕ ካለ ከአቶ አበባዉ መሐሪ ጋር አንድ አድርጓቸዉ የነበረዉ የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ዓላማ ነዉ።ብሔራዉ ምርጫ ቦርድ ግን አቶ አበባዉን ከነአየለ ጫሚሶ እና ከትግስቱ አወሉ ጋር አመሳስሎ፤ እነ አቶ ማሙሽን እንደነ አቶ በላይ ፓርቲ አልባ አደረጋቸዉ።

የመኢአድ ፕሬዝዳንት አቶ አበባዉ መሐሪ ዛሬ እንደነገሩን በነአቶ ማሙሽ አማረ የሚመራዉ ቡድን ከዚሕ ቀደም የፓርቲዉ ጠቅላላ ጉባኤ ያሳለፈዉን ዉሳኔ ካከበረ እሳቸዉም ሆኑ ፓርቲቸዉ እነ አቶ ማሙሽን ለመቀበል ዝግጅቱ ናቸዉ።

መኢአድ ከዚያ የሚደረስበት መንገድ ላሁኑ ግልፅ አይደለም።ግልፅ የሆነዉ በምርጫ ዋዜማ ሁለቱ ትላልቅ ፓርቲዎች ከዚሕ ቀደም በነበሩበት ፖለቲካዊ ጥንካሬ ላይ አለመገኘታቸዉ ነዉ።የፓርቲዎቹ መከፋፈል ወይም መዳከም በፋንታዉ የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሠላምና ልማት ተቋም የፖለቲካ አጥኚ አቶ ይነበብ ንጋቱ እንደሚሉት ከመጪዉ ምርጫ አልፎ በፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ላይ የሚኖረዉ ተፅዕኖ ቀላል አይደለም።

እርግጥ ነዉ ኢትዮጵያ ከፊዉዳላዊዉ አገዛዝ ተላቃ ከዘመናዊዉ የፖለቲካ ማሕበር ከተዋወቅችበት ጊዜ ጀምሮ ያወቀቻቸዉ ፖለቲከኞች የገዢ ፓርቲ አባላት ይሁኑ፤ የአማፂ ቡድን፤የገዢ ፓርቲ ተባባሪ ፓርቲ አባላት ይሁኑ፤ የሕብዕ ድርጅት፤የሐገር ዉስጥ ሠላማዊ ትግል አቀንቃኞች ይሁኑ የስደት ፓርቲዎች አባላት አንዳቸዉ ከሌላቸዉ ከመገዳደል፤ መጠፋፋት፤ መወጋገዛቸዉ እኩል የአንድ ፓርቲ አባላትም እርስ በርስ ያልተናቆሩ፤ ያልተፋጁ፤ ያልተለያዩበት ዘመን የለም።

በጋራ ለመቆማቸዉ የየፖለቲከኞቹ ፍላጎት፤ የጋራ «ጠላት» ወይም «ተቀናቃኝ» የሚሉት ሐይል ጥንካሬ ሰበብ ምክንያት እንደመሆኑ ሁሉ ለመጣላት፤ መከፋፈል፤አንዳዴም መገዳደላቸዉ ከየፖለቲከኞቹ ፍላጎት እኩል ያዉ የጋራ «ጠላት» ወይም «ተቀናቃኝ» የሚሉት ሐይል ደባ፤ ሻጥርና ጣልቃ ገብነት ምክንያት መሆኑ ብዙ አያነጋግርም።ከደርግ፤ እስከ ሕወሐት፤ ከመኢሶን እስከ ኢሕአፓ፤ ከኢሕአዴግ እስከ ቅንጅት አያሌ አብነቶች መጥቀስ አይገድም።ዛሬም ይሕ ተደገመወይ ነዉ ጥያቄዉ።የአንድነት ለፍትሕና ለዲሞክራሲ ተጠባባቂ የሕዝብ ግንኙነት ሐላፊ የነበሩት አቶ አሥራት አብረሐም «የእርስ በርስ ሽኩቻ» ከሚለዉ ይልቅ «የዉጪ ሐይል» የሚባለዉ (ኢሕዴግ) ጣልቃ ገብነትን በግልፅ ይኮንናሉ።

የመኢአድ ፕሬዝዳንት አቶ አበባዉ መሐሪ ደግሞ አሁን ለተፈጠረዉ ችግር የኢሐዲግ ዓላማ አስፈፃሚ ተብሎ የሚወቀሰዉን ምርጫ ቦርዱንም፤ የፓርቲያቸዉን አባላትም ይወቅሳሉ።

የፖለቲካ ተንታኝ ይነበብ ንጋቱ እንደሚሉት ግን ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እራሳቸዉ እንጂ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይሁን ገዢዉ ፓርቲ ተጠያቂ አይደሉም።

በተያዘዉ ዕቅድ መሠረት አጠቃላዩ ምርጫ የፊታችን ግንቦት ይደረጋል።በዚሕ ምርጫ ለመወዳደር በርካታ ፓርቲዎች መመዝገባቸዉን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታዉቋል።በ1997 ምርጫ ጠንካራ ተፎካካሪ የነበረዉ ቅንጅት እብዙ ቦታ ሲሰነጣጠቅ የቅንጅትን በርካታ አባላትና እና አብዛኛ ዓላማዎቹን በመያዝ እስካሁን የቀጠሉት አንድነትና መኢአድ በመጪዉ ምርጫ መሳተፍ አለ መሳተፋቸዉ በርግጥ አጠያያቂ ነዉ።

የመኢአድ ፕሬዝዳንት አቶ አበባዉ መሐሪ እንደሚሉት ደግሞ ምርጫ ቦርድ ለዕጩ መመዝገቢያ የቆረጠዉን ቀነ ገደብ ካላሻሻለ ፓርቲያቸዉ በርጫዉ ሊሳተፍ አይችልም።

የፖለቲካ ተንታኝ ይነብብ ንጋቱ እንደሚሉት በምርጫ ቦርድ አዉቅና ያገኙት የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫዉ ተሳተፉም -አልተሳተፉ ልዩነታቸዉ የምርጫዉን አድማስና የአማራጮችን ብዛት ማጥበቡ አያጠያይቅም።

አምባገነን፤ ወታደራዊ፤ ሶሻሊስታዊ፤ ጦረኛ እየተባለ የሚወገዝ፤የሚወቀስ፤ የሚተቸዉ የደርግ ሥርዓት ከተወገደ ሃያ-አራት ዓመት ሊደፍን እነሆ ወራት ቀሩት።ያኔ የነበረዉ ተስፋ ወይም ቃል የተገባዉ የመድብለ ፓርቲ፤ የዴሞክራሲ፤ የፍትሐዊ ሥርዓት ግንባታ፤ እዚሕ ደርሷል።ከእንግዲሕስ? አቶ አስራት የተስፋ የቆረጡ ይመስላሉ።ሌላዉስ?ሌላ ጊዜ ለማየት ያብቃን።ነጋሽ መሐመድ ነኝ እስከዚያዉ ቸር ያሰማን።

 

 

Audios and videos on the topic