ኢትዮጵያ፥ የምርጫ ዘመቻ፥ ክርክር፥ዉዝግብና ቁርቁስ | ኢትዮጵያ | DW | 17.05.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ፥ የምርጫ ዘመቻ፥ ክርክር፥ዉዝግብና ቁርቁስ

የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የሚሉትን የሚያደርጉ ጀግኖች፣ የማያደርጉትን የማይሉ ብልሆች፣የሕዝብ ፍላጎት አክባሪ-ቅኖች፥ የሐገር ጥቅም፣ተቆርቋሪ አርቆ አሳቢዎች መሆናቸዉን አስመሰክረዉ ቢሆን ኖሮ

default


17 05 10

አንድ ነገር እርግጥ ነዉ።ኢትዮጵያ ዉስጥ የፊታችን እሁድ ምርጫ አለ።ሌላም ነገር እርግጥ ነዉ።
የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ከዛሬ የደረሱት እንደ ዲሞክራሲዉ ወግ እየተከራከሩ፣ እንደ አዉቶክራሲዉ ልምድ ሕይወት፣ አካል እያስጠፉ፣እንደ አዋቂ እየተወያዩ፣ እንደ እንጭጭ እየተተራረቡ፣እንደ ጨዋ ኢትዮጵያዊ በክብር-አንቱ ቅፅል እየተጠራሩ፣እንደ ዋልጌ-እተወራረፉ ነዉ።ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዉን እስከ እሁድና እሁድ የሚገጥማቸዉን፣ የከዕሁድ በሕላ ፖለቲካዊ ጉዟቸዉን ማወቅ አይቻልም።ማወቅ አይደለም መገመት የሚችል ካለ እሱ በርግጥ ነብይ አከል ነዉ።መጠየቅ ግን ማን ገዶን።እርግጠኛዉን ሁነት እያነሳን የማይታወቀዉን ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

ኢትዮጵያና ኢጣሊያ ዉጫሌ ላይ የተፈራረሙት ዉል የአማርኛና የኢጣላያንኛዉ ትርጉም አስራሰባተኛዉ አንቀፁ ላይ እንደሚቃረን ለንጉሠ-ነገሥት ዳግማዊ ሚኒሊክ የተነገራቸዉ ግንቦት ነበር አሉ።1881።ደገኛዉ ኢትዮጵያዊ የግቦትን ወር ከዚያ በፊትም ሆነ በሕዋላ እንደ መጥፎ ወቅት ነዉ-የሚያየዉ።ግንቦት ሞቃት ነዉ።አይታረስበትም።ቢሰረግበት ፍቅር ትዳር አይጠናበትም።ሞፈር፣ ቀንበር፣ ድግር-ቢቆረጥ ቢጠረብበት-ቶሎ ይሰነጣቃል።

ግን ወሩ ምን አደረገ።አጉል እምነት እንጂ።የዉጫሌዉስ ዉል ምን ይወጣለታል።ብቻ ትርጉሙ መዛባቱ መዘዙ ጦርነት ማስከተሉ እንጂ ክፋቱ።የዚያ ዉል መዘዘኛ አንቀፅ ትርጉም በታወቀ በሃያኛዉ አመት ልጅ እያሱ የአያታቸዉ የዳግማዊ ምኒልክ አልጋወራሽ ሆነዉ ተሾሙ።ግንቦት ነበር ወሩ።በኢትዮጵያ የብዙ መቶ አመታት ታሪክ የመጀመሪያዉ ሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር መጀመሪያ ነበር።አምልኮ እንኳን ቢሆን ግንቦት ለትዮጵያ ጥሩ እንጂ መጥፎ ወር የሚባልበት ምን ምክንያት አለ።

እንዲያዉም የቀድሞዉ

An Ethiopian woman

ምርጫ-1997

የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፕሬዝዳንት ያሁኑ የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ሊቀመንበር ኢንጂነር ሐይሉ ሻዉል ባለፈዉ አመት ግንቦት እንዳሉት በተለይ የ1997ቱ ግንቦት ለኢትዮጵያ የድንቅ ሁነት አብነት ነዉ።

ኢንጂነር ሐይሉ የሰማነዉን ሲሉ-ኢትዮጵያዊዉ የ1997ቱን ምርጫ አራተኛ አመት እየዘከረ የዘንድሮዉን አመት አሻግሮ እያማተረ ነበር።የደገኛዉ ኢትዮጵያዊ ልምድም ግንቦት አይሰረግበትም አይልም-ፍቅር ትዳሩ ዳር አይዘልቅበትም-እንጂ።ግንቦትን ልጅ እያሱ ለአልጋወራሽነት ተሾሙበት እንጂ አልነገሱበትም።

ኢትዮጵያዊዉ ከዚያ በፊትና በሕላ ብዙም የማዉቀዉን የሠላማዊ የስልጣን ሽግግርን ተስፋ አደረገበት እንጂ በገቢር አላየበትም።ደርግ ከሕልፈቱ በሕዋላ ብዙዎች እንደሚሉት የኢትዮጵያ ድቀት ምክንያት፥ የኢትዮጵያዉያን ዉድቀት፥ የጦርነት-እልቂት ፍጅት ሰበብ ከነበረ-የዉጫሌዉ ዉል በተፈረመ በመቶኛ አመቱ ሌላ ተስፋ ነበር።1981-ግንቦት።መፈንቅለ መንግሥት።ተሞከረ እንጂ አልተሳካም።

በሁለተኛ አመቱም ሌላ ሁነት ነበር።የደርግ-ሥርዓት ዉድቀት።እንደገና ግንቦት።1983።እንደገና ተስፋ ቃልም ጭምር።-የሠላም፥ የዲሞክራሲ፥ የነፃነት የብልፅግና ቃል-ተስፋ።ዳር መዝለቁ ግን አጠራጣሪ አነጋጋሪም ነዉ።በሰባተኛ አመቱ እንደገና ሌላ ጦርነት።እንደገና ግንቦት።1997 ከተስፋዉ ቅጭት ጋር-የዉጪዉ አለም-ኋላ ቀር፥ ብዙ የማያዉቅ መሐይም፥ የሠላም-ዲሞክራሲ ልምድ የሌለዉ የሚለዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ትልቅ ነገር አሳይቷል።ጨዋ-ታጋሽ፥ አዋቂነቱን አሳይቷል።

በነገሥታት-አምባገነኖች መገዛት መረገጥን እንጂ መሪዎቹን መርጦ መሾምን ያልለመደዉ፣ ችግር ችጋርን እንጂ ድሎት ምቾትን ብዙ የማያወቀዉ፣ ጦርነት-ግጭትን እንጂ ሰላም-መረጋጋትን ብዙ የማያወቀዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመሪዎቹ እና ሊመሩት ከሚመኙት ፖለቲከኞቹ ቀድሞ መብሰሉን በርግጥ ያኔ አስመስክሯል።ኢንጂነር ሐይሉ ከዋናዎቹ ምሥክሮች-አንዱ ናቸዉ።

ዘብድሮም ግንቦት ነዉ።ዘንድሮም ምርጫ አለ።-እሁድ።የሚሆነዉ ግን አሁን አናዉቅም።የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የሚሉትን የሚያደርጉ ጀግኖች፣ የማያደርጉትን የማይሉ ብልሆች፣የሕዝብ ፍላጎት አክባሪ-ቅኖች፥ የሐገር ጥቅም፣ተቆርቋሪ አርቆ አሳቢዎች መሆናቸዉን አስመሰክረዉ ቢሆን ኖሮ የኢትዮጵያዉያን የድሕረ-እሁድ ጉዞን በጎ-መጥፎነት ለመገመት ዛሬና አስከዛሬን መጠበቅ ባላስፈለገ ነበር።አለመሆኑ ነዉ-ሥጋቱ።

ያ ሕዝብ ሥለወደፊቱ ቀርቶ ሥለዛሬ ኑሮዉ፥ የሚያዉቀዉ የፖለቲከኞቹን ብያኔ ጠባቂነቱን ከዚሕ ካለፈም አለማወቁን ማወቁ ነዉ መሆኑ ነዉ ድቀቱ።የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ-መድረክ ባጭሩ ጥምረት ከፍተኛ ባለሥልጣንና ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ መሪ ኢንጂነር ግዛቸዉ ሽፈራዉ ከቅድመ ሁኔታ ጋር ተስፋ አላቸዉ።

ገዢዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር -ኢሕአዴግ ምርጫዉን እንደ ዲሞክራሲዉ ወግ ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንደሚሆን ከብዙ ጊዜ በላይ ብዙ ብሏል።የተቀዋሚ ፓርቲ መሪዎች ግን የገዢዉን ፓርቲ ቃል-አያምኑትም።ከዚሁ ጋር የተቀናቃኝ ፓርቲ መሪዎች እንደ ዲሞክራሲዉ ሥርዓት አስር ጊዜ በአስር ጉዳዮች ላይ ተከራክረዋል።

ክርክሮቹን የተከታተለዉ የአዲስ አበባዉ ወኪላችን ታደሰ እንግዳዉ እንደታዘበዉ ጉድለቶች ባያጧቸዉም የዲሞክራሲ ወግ የተንፀባረቀባቸዉ ነበሩ።
የተነሱት ጉዳዮችም-አብዛኛዉ ኢትዮጵያዊ የሚያወጣ የሚያወርዳቸዉ ናቸዉ።እንደገና ታደሠ እንግዳዉ።

የጤናዉ መስክ እንዲሕ አከራክሯል።

Äthiopien Kinder füllen Kanister mit Trinkwasser

መሠረተ-ልማት፥-
ተከራካሪዎች ወደ መከራከሪያዉ አዳራሾች የገቡና የሚገቡት ግን አባል-ደጋፊዎቻቸዉ እንደታሰሩ፥ ወይም እየተሳሩ፥ እየተወዛገቡ፥አንዳዴም እየተጋጩ ነዉ።ባንዱ የክርክር መድረክ የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ተወካይ እንዳሉት የእስረኛዉ ቁጥር ሺ-በሺ ነዉ።

ግድያም ነበር።ወግዘት-ክስም።በዚሕ መሐል-ግንቦት አስራ አምስት ደረሰ።ምርጫ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ የዚያ ሰዉ ይበለን።

Negash Mohammed

Audios and videos on the topic