ኢትዮጵያ የማዕድን ፖሊሲ እያዘጋጀች ነው | ኤኮኖሚ | DW | 13.02.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

ኢትዮጵያ የማዕድን ፖሊሲ እያዘጋጀች ነው

የኢትዮጵያ መንግሥት ለማዕድን ልማት አዲስ ፖሊሲ በማዘጋጀት ላይ መሆኑን አስታውቋል። ፖሊሲው የውጭ ባለወረቶችን ቀልብ ለመሳብ እና የማዕድን ዘርፉን ለማነቃቃት ያለመ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:54

አዲሱ ፖሊሲ ኩባንያዎች የሚገጥሟቸውን በማቃለል ላይ ያተኩራል

ላለፉት አምስት ወራት ሥራ ፈት ሆኖ የቆየው የዳለቲ የዕብነ በረድ ካባ ትናንት የካቲት 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ማምረት ለመጀመር በሮቹን ከፍቷል። ይኸው ካባ ወደ ሥራ ለመመለስ ያበቃው በኦሮሚያ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተቀስቅሶ የነበረው ግጭት በረድ የማለት አዝማሚያ ካሳየ በኋላ ነው። በብሔራዊ ማዕድን ኮርፖሬሽን የዳሌቲ የዕብነ በረድ ካባ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ገብረፃዲቅ " ኮማንድ ፖስትም ስለተቋቋመ ወደ ሰላም እየተመለሰ ነው። ከመስከረም ጀምሮ በቃ ተቋርጧል" ሲሉ ተናግረዋል።

ዕብነ በረድ የሚመረትበት የዳሌቲ ካባ ከአዲስ አበባ 635 ኪሎ ሜትር በምትርቀው የዳሌቲ ከተማ የተሰየመ ነው። በአካባቢው የሚገኘው ዕብነ በረድ በኢትዮጵያ ታዋቂ ከሚባሉት መካከል አንዱ ሲሆን ላለፉት በርካታ አመታት የአምራቾች ዋንኛ የትኩረት ቦታ ሆኖ ቆይቷል። 

አቶ ጌታቸው እንዳሉት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በምትገኘው ዳለቲ ወደ 27 ኩባንያዎች ዕብነ በረድ ለማምረት ፈቃድ ይኑራቸው እንጂ በሥራ ላይ የሚገኙት 20 ገደማ ብቻ ናቸው። በብሔራዊ የማዕድን ኮርፖሬሽን ሥር የሚገኘው እና አቶ ገብረ ፃዲቅ የሚመሩት ካባ ንብረትነቱ በቅርቡ ከሳዑዲ አረቢያ እስር ቤት የተፈቱት ሼክ መሐመድ አል-አሙዲ ነው። ፈተና
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት እና ኹከት ሳቢያ በአካባቢው ዕብነ በረድ በማምረት ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች ላለፉት አምስት ወራት ገደማ ስራ ፈተው ከርመዋል። የኩባንያዎቹ ፈተና ግን ፖለቲካዊ አለመረጋጋቱ ብቻ አይደለም። አቶ ጌታቸው እንደሚሉት የሰለጠነ የሰው ሐይል ሽሚያ በዘርፉ በተሰማሩ ኩባንያዎች ዘንድ ይታያል። ማዕድናት በሚገኙባቸው አካባቢዎች የሚገኙ መንገዶች ጥራትም ጉዳት እየገጠመው ነው። 

ኃላፊው "አንደኛ በኦሮሚያ እና በክልል ስድስት መካከል አንዳንድ ግጭት እና አለመግባባት አለ። የውጭ ምንዛሪ እጥረት አለ። በተጨማሪ ደግሞ መንገድ አለ። በተለይ የግል ንብረት የሆኑ ኩባንያዎች መስገብገብ አለ። በአንድ ጭነት መኪና እስከ 300 እና 400 ኩንታል ድረስ ስለሚጭኑ መንገዱ ሁሉ ይበለሻሻል። ያንን መንገድ በባለቤትነት የሚጠግን የለም። በአብዛኛው በዚህ በድርጅቱ አቅም እና ጉልበት ነው የሚሰራው። ድልድዮች ከዚህ ቀደም እኛ የሰራናቸው ናቸው። አሁን ግን 300 እና 400 ኩንታል የሚጭን ጭነት መኪና ሲሔድባቸው ውልቅልቃቸው እየወጣ እንቸገራለን" ሲሉ በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎች የገጠማቸውን ፈተና ይዘረዝራሉ። 

በበርካታ ፈተናዎች ከታጠረው የማዕድን ልማት ዘርፍ የኢትዮጵያ መንግሥት ላቅ ያለ ምጣኔ ሐብታዊ ፋይዳ ይጠብቃል። የኢትዮጵያ የማዕድንና ነዳጅ ሚንስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርካቶ እንደሚሉት መንግሥታቸው ለአመታት ዘንግቶት ወደ ነበረው ዘርፍ ፊቱን ማዞሩን ገልጸዋል። ምን አልባትም ይኸው የማዕድን ልማት ዘርፍ ሌሎች የልማት ሥራዎችን ያነቃቃ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ምኒስትሩ በደቡብ አፍሪካ በማዕድን ላይ ባተኮረ ጉባኤ ላይ ባለፈው በተሳተፉበት ወቅት ሲኤንቢሲ ለተባለው የቴሌቭዥን ጣቢያ በሰጡት ቃለ መጠይቅ  "የማዕድን ዘርፍ ላለፉት ሁለት እና ሶስት አስርት አመታት ቅድሚያ ያልሰጠንው ዘርፍ ነው። አሁን ግን የማዕድን ፍለጋ ሌሎች የልማት ዘርፎቻችንን የሚያነቃቃ አድርገን ወስደንዋል። የማዕድን ዘርፍ ለማኅበረ-ፖለቲካዊ ልማት እና የመሠረተ-ልማት ግንባታዎቻችንን እንዲያፋጥን  ተቋማዊ አወቃቀራችንን በማሻሻል ላይ እንገኛለን" ሲሉ ተናግረው ነበር።

ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች አኳያ ኋላ ቀር የሚባለውን የማዕድን እና የነዳጅ እና ጋዝ ልማት ዘርፍ ለማነቃቃት ጥረት ላይ ትገኛለች። ሬውተርስ የዜና ወኪል ምኒስትሩን ጠቅሶ እንደዘገበው የውጭ ባለወረቶችን የሚያበረታታ ማሻሻያ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ተግባራዊ ይደረጋል።

ባለፉት አመታት ለማዕድን አምራች ኩባንያዎች የታክስ ቅናሽ ማድረጓን ያስታወሰው የሬውተርስ ዘገባ በመንግሥት በኩል የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጫናውን ለመቅረፍ የውጭ ባለወረቶችን ቀልብ የመሳብ ፍላጎት መኖሩን አትቷል።

የማዕድንና ነዳጅ ሚንስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርካቶ "ሁሉንም ሕግጋት፤ ብሔራዊውን የማዕድን ልማት ፖሊሲ እና ስትራቴጂ እያሻሻልን ነው" ሲሉ ተናግረዋል። ምኒስትሩ ከሲኤንቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ መንግሥታቸው በተለይ ትኩረት ያደረገባቸው ዘርፎች መኖራቸውን ጠቁመው ነበር።

አገራችንን ወደ ኢንዱስትሪ ለማሻገር ጥረት ላይ እንገኛለን። በዚህም በኢንዱትሪ ማዕድናት ላይ ትኩረት አድርገናል። ወርቅ እና ውድ ሜታል*  የመሳሰሉ ማዕድናት አሉን። የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ውድ ማድኖቻችንን ለዓለም ገበያ መሸጥ ይኖርብናል። ይኸም ሌላው ትኩረታችን ነው። ሌላው ከፍተኛ የመሠረተ-ልማት ግንባታ በማካሔድ ላይ እንገኛለን። የግንባታው ዘርፍ ከማዕድን ልማት ግብዓት እየፈለገ ነው። ስለዚህ ይኸም ትኩረት የምናደርግበት ሌላው ስራ ነው"

የኢትዮጵያ የማዕድንና ነዳጅ ሚንስቴር የማዕድን ልማት ፖሊሲ በማዘጋጀት ላይ መሆኑን ለDW አረጋግጧል። የፖሊሲው አቅጣጫ፤ በዘርፉ የሚታዩ ዋባ ዋባ ክፍተቶች እና የማዕድን ፖሊሲ ማስፈጸሚያ ስልቶች ላይ ውይይት መደረጉን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ላይ የሰፈረ መረጃ ይጠቁማል። ተቋሙ በተዘጋጀው ሰነድ ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጠን ያደረግንው ተደጋጋሚ ሙከራ ግን አልተሳካም።

ወርቅ አምራቹ ኒውሞንት እና የኖርዌይ የማዳበሪያ አምራች የሆነው ያራ ወደ ኢትዮጵያ ጎራ የማለት ፍላጎት ያላቸው ኩባንያዎች መሆናቸውን የሬውተርስ ዘገባ ይጠቁማል።

ደካማው መሠረተ-ልማት፤ የሰለጠነ የሰው ሐይል እጦት፤ እና በፈቃድ አሰጣጥ ዙሪያ ግልፅነት አለመኖሩ ሌሎች ኩባንያዎች የኢትዮጵያን ገበያ እንዲሸሹ ካደረጓቸው ጉዳዮች መካከል እንደሚገኙበት ሬውተርስ ባለሙያዎችን ጠቅሶ ዘግቧል።

በሬውተርስ ዘገባ መሠረት ቢኤችፒ የተባለ የአውስትራሊያ ገበያ ከሰባት አመታት በፊት ኢትዮጵያን ጥሎ ወጥቷል። ሌላ የእስራኤል ኩባንያ ደግሞ ከመንግሥት ጋር በግብር ጉዳይ እሰጥ አገባ ውስጥ በመግባቱ እና በመሠረተ-ልማት መጓደል ምክንያት በኢትዮጵያ የጀመረውን የፖታሽ ልማት ሥራ አቋርጧል።

የማዕድንና ነዳጅ ሚንስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርካቶ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ሲያመሩ የሚፈገጥማቸውን ፈተና ለመቅረፍ መንግሥታቸው ጥረት ላይ መሆኑን ገልጸዋል። "እነዚህ ኩባንያዎች ዓለም አቀፍ ናቸው። ስለ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያውቃሉ። በማደግ ላይ ወዳሉ ኤኮኖሚዎች ሲመጡ ፈቃድ ለማውጣት ሲሞክሩ ፈተናዎች ይገጥሟቸዋል። በሌሎች አካባቢዎች እንደተመለከትኩትም ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር መስራትም ፈተና ይሆናል። ስለዚህ ከመንግሥት በኩል እነዚህን ችግሮች በኢትዮጵያ እየቀረፍን ነው። በአሁኑ ወቅት ብርቱ ማሻሻያ በማድረግ ላይ እንገኛለን። ማኅበራዊ ፈቃድን በቀላሉ ለማግኘት ከሕዝቡን ከኩባንያዎች ጋር እያሳተፍን ነው። ከባለ ድርሻዎች ጋር አጋርነት እየፈጠርን ነው። ከኩባንያዎች በኩል አካባቢያዊ ሁኔታዎችን እንዲረዱ በጥሩ ምግባር ሥራቸውን ማከናወን እንዲችሉ አቅማቸውን እያጠናከርን ነው" ብለዋል። ምኒስትሩ በኢትዮጵያ ለሚሰሩ ኩባንያዎች መንግሥት የተለያዩ ማበረታቻዎች እንደሚያቀርብም ጠቁመዋል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic