ኢትዮጵያ የልዑል ዓለማየሁ አፅም እንዲመለስ ግፊት እያደረገች ነው | ኢትዮጵያ | DW | 13.05.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ የልዑል ዓለማየሁ አፅም እንዲመለስ ግፊት እያደረገች ነው

ኢትዮጵያ የልዑል ዓለማየሁን አፅም ጨምሮ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ቅርሶቿን ከብሪታኒያ ለማስመለስ ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች። ከ150 አመታት ገደማ በፊት ከኢትዮጵያ ተወስዶ በብሪታኒያ ሕይወቱ ያለፈው የልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ አፅም እንዲመለስ የመጀመሪያውን ጥያቄ ያቀረቡት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ነበሩ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:43

ከአምባሳደር ፍሰሐ ሻውል ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ

ኢትዮጵያ ከ150 አመታት በፊት በብሪታኒያ ወታደሮች ተወስዶ በዚያው ሕይወቱ ያለፈው እና በቤርክ ሻየር በሚገኘው የዊንድሶር የልዑላን መኖሪያ ቅጥር ግቢ የተቀበረው የልዑል ዓለማየሁ አፅም እንዲመለስላት ግፊት በማድረግ ላይ ትገኛለች። ከጥቂት ወራት በፊት የኢትዮጵያ የባህል ምኒስትር ወደ ብሪታኒያ ባቀኑበት ወቅት ይኸንንው ጥያቄ አንስተው ነበር። 

አባቱ አጼ ቴውድሮስ በመቅደላ አፋፍ ራሳቸውን ሲያጠፉ ከሁለተኛ ባለቤታቸው እቴጌ ጥሩወርቅ ውቤ የሚወለደው ልዑል ዓለማየሁ እድሜው ስምንት ብቻ ነበር። በልጅነቱ ባሕር ተሻግሮ ብሪታኒያ የገባው ልዑል ዓለማየሁ በእንግሊዝ በተማረባቸው ትምህርት ቤቶች የነበሩ መምህራን ሁሉ መልካም ወዳጆቹ እንደነበሩ ታሪኩን የፃፉ ባለሙያዎች መስክረዋል። እርሱ ግን ከትምህርት ይልቅ ለስፖርት የተሻለ ፍቅር ነበረው፡፡እግር ኳስ እና ራግቢም ይጫወት ነበር፡፡መምህራኑ ወታደራዊ ሳይንስ እንዲያጠናም ግፊት አድርገዋል። እናም በጎርጎሮሳዊው መስከረም 1878 ወደ ሳንድረስት ወታደራዊ ትምህርት ቤት ካለ ፈተና እንዲገባ ተደረገ።

በወታደራዊ ትምህርት ቤት ደስተኛም ሆነ ውጤታማ አልነበረም።  እናም ለእረፍት እንደወጣ አልተመለሰም። ዓለማየሁ በብሪታኒያ በኖረባቸው አመታት ከኢትዮጵያ ሁለት ደብዳቤዎች ደርሰውት ነበር።  አንዱ ከእናቱ እናት ወይም ከአያቱ ሲሆን የሁለተኛው ደብዳቤ ላኪ ማንነት አይታወቅም። ሁለቱም ደብዳቤዎች የዓለማየሁን መመለስ የሚናፍቁ ነበሩ። 

ስደተኛው ልዑል በጎርጎሮሳዊው ኅዳር 14 ቀን 1879 ዓ.ም. በጥቂት ቀናት ህመም ከዚህ አለም በሞት ሲለይ እድሜው 19 ብቻ ነበር። በንግስት ቪክቶሪያ ፈቃድ በዊንድሶር የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተመቅደስ የቀብር ስነ-ስርዓቱ ተፈፀመ። 

የኢትዮጵያ ሚሊኒየም ሲከበር የልዑል ዓለማየሁን አፅም ወደ ኢትዮጵያ ለማስመለስ ጥረት ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም ስኬታማ አልሆነም። የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ የልዑል ዓለማየሁ አፅም እንዲመለስ ያቀረቡትን ጥያቄ ንግሥት ኤልሳቤጥ አልተቀበሉትም። በብሪታኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ፍሰሐ ሻውል እንደሚሉት ኢትዮጵያ ከልዑል ዓለማየሁ አፅም ባሻገር በብሪታኒያ የሚገኙ 1,000 ሺሕ በላይ ቅርሶች እንዲመለሱላት ግፊት እያደረገች ትገኛለች።

እሸቴ በቀለ
ኂሩት መለሰ 
 

Audios and videos on the topic