ኢትዮጵያ ውስጥ የጋዜጠኞችና ሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እስርና ወከባ አሳሳቢ ነው ተባለ
ሐሙስ፣ መስከረም 16 2017ኢትዮጵያ ውስጥ ካለፉት ጥቂት ዓመታት አንስቶ የጋዜጠኞችና ሰብአዊ መብት ተሟጋቾች አያያዝ እጅግ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ ተገለጠ ። አምነስቲ ኢንተርናሽናል፦ ጋዜጠኞችና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ላይ ጫናው በተለይ ባለፉት ዐሥርና ዐሥራ አንድ ወራት መበርታቱን ገልጧል ።
የጥበብ ሰዎችን ጨምሮ ተቺዎች ላይ እየተሰነዘሩ ያሉ አሳሳቢ ጥቃቶች እየተበራከቱ ነው
ኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኞች፤ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እንዲሁም የጥበብ ሰዎችን ጨምሮ ተቺዎች ላይ እየተሰነዘሩ ያሉ አሳሳቢ ጥቃቶች እየተበራከቱ መምጣታቸው ተገለጠ ። እንግልት፤ እስር እና ጥቃቶቹም በአስቸኳይ እንዲቆሙ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠይቋል ። የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅ አፍሪቃ አጥኚ፥ ወ/ት ሐይማኖት አሸናፊ ጋዜጠኞች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ላይ ጫናው በተለይ ባለፉት ዐሥር እና ዐሥራ አንድ ወራት መበርታቱን ተናግረዋል ።
«አሁን ያሉት አዝማሚያዎች፤ አሁን የምናያቸው እጅግ እጅግ አሳሳቢ የሆኑ ጥቃቶች፦ ጋዜጠኞች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ ተቺዎች ላይ፤ አሁን አሁን እንደምናየው አርቲስቶች ላይም ጥቃቶች እየመጡ ነው ። ሕገወጥ እስሮችም እየመጡ ነው ። አሁኑኑ[በአስቸኳይ] መቆም ያለበት [ድርጊት] ነው ። »
ባለፉት አራት ዓመታት ብቻ 54 ጋዜጠኞች ከሀገር ጥለው መሸሻቸውን ተገልጦ ነበር
ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (CPJ) ከሦስት ወራት በፊት ባወጣው ዘገባ ባለፉት አራት ዓመታት ብቻ 54 ጋዜጠኞች ከሀገር ጥለው መሸሻቸውን ገልጦ ነበር ። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከልም (EHRDC) ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ እና ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው ሀገር ጥለው መሰደዳቸውን ተከትሎ ከሰሞኑ ባወጣው መረጃ እስር እና እንግልት ብሎም ስደቱ መቀጠሉን ጠቅሷል ። የምሥራቅ አፍሪቃ አጥኚዋም ይህንኑ ያስረግጣሉ ።
«በቅርቡ በርካታ ጋዜጠኞች አገር ጥለው ለመሰደድ ተገድደዋል ። ከመሰደዳቸውም በፊት በርካታ ጥቃቶችን ያስተናግዳሉ ። እንደው በመጨረሻ የጠቀስካቸውን ጋዜጠኞች እንኳን ለመጥቀስ ያህል በላይ ማናዬ ለወራት ፍርድ ቤት ሳይቀርብ በወታደራዊ ካምፕ ውስጥ የጤና ሕክምና ሳያገኝ እንደቆየ ይታወቃል ። በቤተሰብ የመጎብኘት እድል እንዳልነበረው ይታወቃል ።»
አምነስቲ ኢንተርናሽናል በላይ እና በቃሉን ጨምሮ ሌሎች ጋዜጠኞችም እንዲፈቱ ጥረት ማድረጉን የምሥራቅ አፍሪቃ አጥኚዋ ወ/ት ሐይማኖት አሸናፊ አክለዋል ። ጋዜጠኞችን እና የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች እየገጠማቸው ነው የተባለው ወከባ፣ እሥር፣ እንግልት፣ ዛቻና ማስፈራሪያ አሳሳቢ መሆኑን የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በተደጋጋሚ እየገለጡ ነው ።
በርካታ ጋዜጠኞችን እና የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች አገር ጥለው እየሸሹ ነው
«እጅግ እጅግ አሳሳቢ በሆነ ቁጥር ጋዜጠኞችን እና የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች አገር ጥለው እየሸሹ ነው ። አገር ጥሎ መሸሽ ማለት ደግሞ ሊያገለግሉት፣ ሽፋን ሊሰጡት ከሚፈልጉት ማኅበረሰብ ያርቃቸዋል፤ ያቆራርጣቸዋል፥ በግላቸውም ከፍተኛ የሆነ ዋጋ ይከፍላሉ ማለት ነው ከሀገራቸው ከወጡ በኋላ ። »
ሁኔታው ኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኝነትን፣ የሰብአዊ መብት መሟገት ሥራን ፤ በአጠቃላይ ሐሳብን በነጻነት የማንሸራሸር እንቅስቃሴን እንደሚያጉልና እንደሚያደናቅፍም አጥኚዋ ተናግረዋል ።
በተለያዩ አካባቢዎች የፀጥታ ችግር ባለባት ኢትዮጵያ ከመንግሥት አካላትም ሆነ ከሌሎች አካላት መረጃ የማግኘት እና የመረጃ ፍሰት ችግር ጎልቶ የሚታይ ነው ።
ጋዜጠኞች በሀገሪቱ ሕግጋት መሠረት መረጃ የማግኘት መብት አላቸው
«መንግሥት እንዲሸፈኑ፣ ለኅብረተሰብ በጣም ዕንዲታወቁ የማይፈልጋቸውን ጉዳዮች እንዳይደርስ የሚከለክልበት [ስልት] ነው ። ጋዜጠኞችን [መገደብ]። ይኼም በጣም በጣም አደገኛ ነው ። መሻሻል ያለበት ነው ። ከፍተኛ ጫና መደረግ አለበት ።»
ጋዜጠኞች በሀገሪቱ ሕግጋት መሠረት፥ ኅብረተሰቡን የሚመለከቱ መረጃዎችን ከመንግሥት አካላት ማግኘት ብሎም እንደልባቸው ተንቀሳቅሰው መሥራት መብታቸው ነው ሲሉም ወ/ት ሐይማኖት አስረግጠዋል ። ይህ ሕገ መንግሥታዊ መብትም ሊከበርላቸው ይገባል ብለዋል ።
ኢትዮጵያ ታግደው የቆዩ ከ260 በላይ ድረ ገጾችን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2010 ዓ.ም መክፈቷን የመብት ተሟጋቾች በመልካም ጅማሮ ተቀብለው ነበር ። በወቅቱም አንድም ጋዜጠኛ ያልታሰረባት ሀገር በሚል «ለጋዜጠኞች አዲስ ዘመን ተከፈተ» በሚልም ተወድሳ ነበር ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ታምራ ዺንሳ