ኢትዮጵያ ከፍተኛ የብድር ጫና ሥጋት አለባት ተባለ | ኤኮኖሚ | DW | 09.05.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የብድር ጫና ሥጋት አለባት ተባለ

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ከሰሐራ በታች የሚገኙ የአፍሪቃ አገሮች ያለ ቅጥ መበደር በማብዛታቸው እና የመንግሥታት የበጀት ጉድለት በማየሉ የዕዳ ጫና እንደጠነከረባቸው አስታውቋል።  ድርጅቱ ትናንት ባወጣው የአፍሪቃ ምጣኔ ሐብት ምልከታ ኢትዮጵያን ከፍተኛ የብድር ጫና ሥጋት ካለባቸው አገራት ጎራ መድቧታል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:09

የአፍሪቃ አገሮች የብድር ጫና በርትቶባቸዋል

የዓለም የገንዘብ ድርጅት (IMF)ከሰሐራ በታች የሚገኙ የአፍሪቃ አገራት የምጣኔ ሐብት እድገት መነቃቃት ቢታይበትም የዕዳ ጫና እየበረታባቸው እንደሆነ አስጠንቅቋል። በድርጅቱ ምዘና መካከለኛ የዕዳ ጫና ካለባቸው አገራት ተርታ ትመደብ የነበረችው ኢትዮጵያ አሽቆልቁላለች። ዘገባው ኢትዮጵያ እና ዛምቢያን "የከፋ የዕዳ ጫና ሥጋት" ወዳለባቸው ጎራ ቀላቅሏል። 
የዓለም የገንዘብ ድርጅት ከዚህ ድምዳሜ ለመድረስ የየአገሮቹን የዕዳ አስተዳድር እና የምጣኔ ሐብት ይዞታ መፈተሹን ዘገባውን ያጠናቀረውን የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ቡድን በበላይነት የመሩት ፓፓ ን'ድያዬ ይናገራሉ። ባለሙያው እንደሚሉት እንደ ኢትዮጵያ ያሉት ከሰሐራ በታች የሚገኙ የአፍሪቃ አገሮች መንግሥታቶቻቸው ለሚሰሯቸው ሥራዎች ብድር ማብዛታቸው ለዕዳ ጫና ዳርጓቸዋል። 

"በየአገሮቹ ባሉ አጠቃላይ ጠቋሚዎች እና የመንግሥታቱ ለወደፊት የመበደር ፍላጎት ላይ  ምዘና አድርገናል። ኢትዮጵያን ጨምሮ በአማካኝ ከ6 በመቶ በላይ በሆነ ፍጥነት እያደጉ የሚገኙ አገሮች አሉ። የእድገታቸው ምሥጢር በዋናነት የመንግሥት መዋዕለ-ንዋይ ነው። የዚህ መዋዕለ-ንዋይ የገንዘብ ምንጭ ደግሞ ብድር ነው። ትልቁ ፈተና የአገራቱን የምጣኔ ሐብት እድገት ለግሉ ዘርፍ ከማዛወሩ ላይ ነው"

በዘገባው መሠረት ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ የምታቀርበው ሸቀጥ ቀንሶ የምትሸምተው በመብዛቱ ምክንያት በጎርጎሮሳዊው 2017 ዓ.ም. የበጀት ጉድለቷ ጭማሪ አሳይቷል። በገቢ ማሽቆልቆል ሳቢያ ይኸው የበጀት ጉድለት እየሰፋ መሆኑንም ዘገባው ጠቁሟል። 

ኢትዮጵያ የገባችበትን የዕዳ ጫናም ይሁን ላለባት የበጀት ጉድለት መፍትሔ ፍለጋ በምጣኔ ሐብት ፖሊሲዋ የምትወስዳቸው እርምጃዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ የዓለም የገንዘብ ድርጅት ጥቆማ ሰጥቷል። በ137 ገፆች የተቀነበበው ሰነድ እንደሚለው በጎርጎሮሳዊው 2018 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ከአገር ውስጥ የምትሰበስበውን ገቢ በማጠናከር የማመጣጠን እርምጃ ትወስዳለች ተብሎ ይጠበቃል።  ን'ድያዬ እንደሚሉት የዕዳ ጫናው የከፋባቸው ሁሉ በምጣኔ ሐብት ፖሊሲዎቻቸው እርምጃዎች እንዲወስዱ ይጠበቃል።

"በአሁኑ ወቅት ስድስት አገሮች በዕዳ ጫና ውስጥ ይገኛሉ። ዘጠኝ ደግሞ የዕዳ ጫና ውስጥ የመግባት ከፍተኛ ሥጋት ያለባቸው ናቸው። አንድ አገር ከፍተኛ የዕዳ ጫና ሥጋት አለበት ማለት ግን በቀጥታ የዕዳ ጫና ውስጥ ይገባል ማለት አይደለም። ለእነዚህ አገሮች ከዚህ ቀደም ቃል የገቧቸውን የማመጣጠን እርምጃዎች መውሰድ እጅግ ጠቃሚ ነገር ነው። የእኛ ትንበያ እንደሚጠቁመው የማመጣጠን እርምጃዎቹ ገቢራዊ ከተደረጉ ዕዳው ቀንሶ መረጋጋት ይፈጠራል። ዋንኛው ትኩረት ሊሆን የሚገባው ይኽ ነው"


የአፍሪቃ አገሮች አለቅጥ መበደር በማብዛታቸው ወደ ዕዳ ቀውስ እያመሩ ነው የሚለውን ሥጋት አስቀድሞ የገለጸው የዓለም ባንክ ነበር። በዓለም ባንክ መረጃ መሠረት ከፍተኛ የዕዳ ጫና ሥጋት ውስጥ የሚገኙ አገሮች ቁጥር በጎርጎሮሳዊው 2013 ዓ.ም ስምንት ብቻ ነበር። ከአምስት አመታት በኋላ ወደ 18 አድጓል። በዓለም ባንክ የአፍሪቃ ዋና የምጣኔ ሐብት ባለሙያው ዶ/ር አልበርት ዙፊያክ ከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ ገብተዋል ብለው ከጠሯቸው አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ነበረች።

"በዘገባችን ከፍተኛ የዕዳ ጫና ሥጋት ያለባቸውን አገሮች በዝርዝር አስቀምጠናል። ግልፅ ሆኖ የሚታየው በዝርዝሩ የተቀመጡ አብዛኞቹ ለንቋሳ አገሮች መሆናቸው ነው። ከፍተኛ የዕዳ ጫና ሥጋት አለባቸው ከተዘረዘሩት መካከል ብሩንዲ፣ ኬፕ ቨርዴ፣ ካሜሩን፣ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ፣ ቻድ፣ ሁለቱ ኮንጎዎች፣ ኤርትራ፣ኢትዮጵያ ጋና ይገኙበታል"

 በዓለም የገንዘብ ድርጅት ትንበያ መሠረት ከሰሐራ በታች የሚገኙ የአፍሪቃ አገራት የምጣኔ ሐብት በአማካኝ በ3.4 በመቶ ያድጋል። ባለፈው አመት 2.8 በመቶ ለነበረው የምጣኔ ሐብት እድገት መነቃቃት ዓለም አቀፍ እድገት እና የሸቀጦች ዋጋ መጨመር ዋንኛ ምክንያቶች ናቸው። በዓለም ገበያ የነዳጅ እና ልዩ ልዩ ሸቀጦች ዋጋ ማሽቆልቆል የአፍሪቃ አገሮችን ለዕዳ ጫና የዳረጓቸው ምክንያቶች መሆናቸውን ፓፓ ን'ድያዬ  ይናገራሉ።  

"ከሰሐራ በርሐ በታች የሚገኙ የአፍሪቃ አገሮች ከፍተኛ የመሰረተ-ልማት ጉድለት እና የልማት ፍላጎት ይታይባቸዋል። አብዛኞቹ አገሮች ደግሞ ተበድሮ ያን መሠረተ-ልማት በመገንባት የምጣኔ ሐብታቸውን ለማሳደግ እና የተባበሩት መንግሥታት ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ፈቃደኛ ናቸው። ነዳጅ ወደ ውጪ ይልኩ የነበሩ አገሮች በዋጋ ማሽቆልቆል ሳቢያ የከፋ ጫና ውስጥ ገብተዋል። ከዚህ በተጨማሪ ለዓመታት በዘለቁ ግጭቶች ውስጥ የሚዳክሩ እንዲሁም ምጣኔ ሐብታቸውን የሚፈትን የጸጥታ መጓደል የገጠማቸው አገሮችም አሉ"

የዓለም የገንዘብ ድርጅትም ይሁን የዓለም ባንክ እንደሚሉት ከሰሐራ በታች ከሚገኙ የአፍሪቃ አገሮች 40 በመቶው ከዕዳ ጫና ውስጥ ተዘፍቀዋል፤ አሊያም እንደ ኢትዮጵያ ወደዚያው እየተንደረደሩ ነው። የዓለም የገንዘብ ድርጅት ዘገባም ይሁን የተቋሙ የምጣኔ ሐብት ባለሙያ ፓፓ ን'ድያዬ አገሮቹ በዚሁ ከቀጠሉ ያለባቸውን ዕዳ ለመክፈል የሚያደርጉት ሙከራ አክሳሪ ሊሆን ባቸው እንደሚችል ጠቁመዋል። ዘገባው ያደጉት አገሮች ለአፍሪቃውያኑ ከማበደር ሊያፈገፍጉ እንደሚችሉ፤ ቢያበድሯቸው እንኳ የወለድ ምጣኔው ከሰሐራ በታች ለሚገኙት ተመራጭ እንደማይሆን ሥጋቱን ገልጿል። 


የአፍሪቃ አገሮች በጎርጎሮሳዊው 2017 ዓ.ም ብቻ 7.5 ቢሊዮን ዶላር የብድር ቦንድ በዓለም ገበያ አቅርበዋል። ይኸ ከጎርጎሮሳዊው 2016 አኳያ በ10 እጥፍ ይልቃል። በያዝንው አመትም ተጨማሪ የ11 ቢሊዮን ዶላር የብድር ቦንድ ወደ ዓለም ገበያ አቅርበዋል፤ አሊያም ሊያቀርቡ አቅደዋል። ከጎርጎሮሳዊው 2013-2017 ባሉት አመታት የአፍሪቃ የውጭ ምንዛሪ ብድር በ40 በመቶ መጨመሩን የዓለም የገንዘብ ድርጅት መረጃ ይጠቁማል። ከአፍሪቃ አጠቃላይ ብድር 60 በመቶው በውጭ ምንዛሪ የተደረገ ነው። በጎርጎሮሳዊው 2017 ዓ.ም. የወለድ ክፍያ ከአጠቃላይ የአገሮቹ ወጪ 12 በመቶ ድርሻ አለው። በዓለም የገንዘብ ድርጅት ግምገማ መሠረት ቻድ፣ ኤርትራ፣ ሞዛምቢክ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፣ ደቡብ ሱዳን እና ዚምባብዌ ለይቶላቸው ከዕዳ ጫና ውስጥ ገብተዋል። 
በዓለም የገንዘብ ድርጅት የአፍሪቃ ቢሮ ዳይሬክተሩ አበበ አዕምሮ ሥላሴ የአኅጉሪቱ ዕዳ ያደገበት ፍጥነት እጅግ አሳሳቢ ከሆነባቸው መካከል ናቸው። ዳይሬክተሩ የአፍሪቃ አገሮች በብድር የምጣኔ ሐብት እድገታቸውን ለማፋጠን መሞከራቸው አዋጪ እንደማይሆን ተናግረው በፖሊሲዎቻቸው የማመጣጠን እርምጃ ሊወስዱ ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። መንግሥታት ወጪያቸውን ለመሸፈን መበደር የተለመደ  አሰራር ቢሆንም በረዥም ጊዜ ግን ከአገር ውስጥ በሚሰበስቡት ላይ ሊታመኑ እንደሚገባ ጠቁመዋል።  ፓፓ ን'ድያዬ የድርጅታቸውን ዘገባ እያጣቀሱ አፍሪቃ የግብር አሰባሰቧን እንድታሻሽል፤ የግል ዘርፉንም እንድታጠናክር ይመክራሉ

"በዚህ ዘገባ ሁለት የትንታኔ ምዕራፎች አሉ። አንደኛው አገሮቹ የአገር ውስጥ ገቢያቸውን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን የሚጠቁም ነው። በዚህም ላላቸው የእድገት ፣ የመሠረተ-ልማት እና የሰብዓዊ ልማት ፍላጎቶቻቸው በራሳቸው ክፍያ መፈጸም ይችላሉ። ከሰሐራ በታች በሚገኙ የአፍሪቃ አገራት የግብር ገቢ እጅግ አነስተኛ ነው። የግብር ገቢያቸውን ማሳደግ አለባቸው። ይኸ ግን የግብር ክፍያን ማሳደግ ማለት አይደለም። የግብር አሰባሰብ ሥርዓቱን አፈፃጸም ማጠናከር መንግሥታት የምጣኔ ሐብት እድገታቸውን ሳይጎዱ ገቢያቸውን ለመጨመር እድል ይሰጣቸዋል። ሁለተኛው ትንታኔ የግል መዋዕለ-ንዋይ ማሳደግን ይመለከታል። ይኸ ቀጠናው በተወሰነ ጊዜ ዘላቂ እና ጠንካራ እድገት እንዲያገኝ ስለሚያግዝ እጅጉን አንገብጋቢ ነው"
የአሜሪካው ብሮኪንግስ የጥናት ማዕከል እንደሚለው ግን የአፍሪቃ የዕዳ ጫና የከፋ ደረጃ ላይ ደርሷል። ድርጅቱ የዓለም ባንክ እና የዓለም የገንዘብ ድርጅት የአፍሪቃ አገሮች የዕዳ ቀውስ ውስጥ ከመግባታቸው በፊት እርምጃ መውሰድ አለበት ሲል ይውሳል። ብሮኪንግስ እንደሚለው ሁለቱ ተቋማት ከናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪቃ፣ አንጎላ፣ ኢትዮጵያ እና ኬንያ አንዳቸው የዕዳ ጫና ውስጥ እስኪዘፈቁ ድረስ በቸልታ እየተመለከቱ ነው። 


እሸቴ በቀለ
ኂሩት መለሠ
 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች