1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ፣ ከጎሳ ወደ ኃይማኖት ግጭት

እሑድ፣ ጥር 17 2012

በሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያስተዳድሩ፣ በብድርና ልቆ የተገነቡ የንግድ ተቋማትን፣ ለሺዎች የሥራ እድል የፈጠሩና የሚፈጥሩ፣ ሕንፃዎችን፣ መኪኖችንና ተቋማትን ማንደድ በርግጥ ንብረቱ የሚጠፋበትን ባለቤት፣ ተቀጣሪዉን እና ቤተሰቦችን ብቻ ሳይሆን  ግብር ሰብሳቢዉን መንግስትን ጭምር ሊያሳስብ በተገባ ነበር የሚሉ አሉ።

https://p.dw.com/p/3WmwO
Angriff auf Moschee und Kirche in Motta Amhara
ምስል Alemnew Mekonnen

ኢትዮጵያ፣ ከጎሳ ወደ ኃይማኖት ግጭት

በአብዛኛዉ በፖለቲካ ጥቅም ሽሚያ የሚገፋዉ የኢትዮጵያ የጎሳ ጠብና ግጭት ባለፈዉ ዓመት ከመንፈቅ ሺዎችን መግደል፣ ሚሊዮኖችን  ማፈናቀል፣ ማሰደዱ አነጋግሮ ሳያበቃ፣ የነባሮቹ የኢትዮጵያ ኃይማኖቶች ተከታዮች ይጋጩ፣ የኃይማኖት ተቋማትን ያቃጥሉ፣ ሱቅ መደብሮችን ያነዱ፣ ያወድሙ፣ይመዘብሩ ይዘዋል።

ከጂጂጋ እስከ እስቴ፣ ከሞጣ እስከ ሐረር በሙስሊምና በኦርቶዶክስ ክርስቲያን ስም የተነሱ ኃይላት በድምሩ በመቶ የሚቆጠሩ መሳጅድና አብያተ ክርስቲያናትን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ አቃጥለዋል። በብዙ ዓመታት ልፋትና ጥረት፣ በብድርና ልቆ  የተቋቋሙ፣ ሱቆች፤ ሆቴሌች፣ ሻይና ምግብ ቤቶች፣አገልግሎት መስጪያ መደብሮችን  አጋይተዋል።ሕንፃዎች፣ መኪኖች፣ ባጃጅ የሚባሉ ተሽከርካሪዎችን ሳይቀሩ ሰባብረዋል።

ኢትዮጵያ በትንሽ ግምት ከ20 ሚሊዮን የሚበልጥ ዜጋዋ ሥራ አጥ ነዉ።ዘገቦች እንደሚጠቁሙት ከሰላሳ-እስከ አራባ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ዕዳ የሚያናጥርባት ሐገር ናት።በሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያስተዳድሩ፣ በብድርና ልቆ የተገነቡ የንግድ ተቋማትን፣ ለሺዎች የሥራ እድል የፈጠሩና የሚፈጥሩ፣ ሕንፃዎችን፣ መኪኖችንና ተቋማትን ማንደድ በርግጥ ንብረቱ የሚጠፋበትን-ባለቤት፣ ተቀጣሪዉን እና ቤተሰቦችን ብቻ ሳይሆን  ግብር ሰብሳቢዉን መንግስትን ጭምር ሊያሳስብ በተገባ ነበር።

የሶማሌ ክልላዊ መስተዳድር በክልሉ የተነሱ የጥፋት ኃይሎችን ፈጥኖ መቆጣጠሩ፤ የተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናት እና ጉዳት የደረሰባቸዉን ምዕመናን መደጎሙን መገናኛ ዘዴዎች ዘግበዋል። የኦሮምያ ምክትል ርዕሠ-መስተዳድርም መስተዳድራቸዉ በክልሉ በሚገኙ የኃይማኖት ተቋማት ላይ የሚደርሱ ጥፋቶችን እንደሚቆጣጠር ባለፈዉ መስከረም ቃል መግባታቸዉን ሰምተናል።

ከዚሕ ዉጪ በተለይ ሞጣ ዉስጥ መሳጅድና የሙስሊሞች የንግድ ተቋማት ከወደሙ በኋላ ከፍተኛ ወቀሳና ትችት የሚሰነዘርበት የአማራ መስተዳድር እስካሁን አጥፊዎችን ያልተቆጣጠረበትን ምክንያትም ሆነ፣ ተመሳሳይ ጥፋቶችን ለመቆጣጠር መዘጋጀቱን አይደለም መፈለጉንም በግልፅ አላስታወቀም።

የሌሎች ክልሎች መስዳድሮች፣ የፌደራሉ መንግሥት የፀጥታ አስከባሪዎችም ግጭቶችና ጥፋቶችን ለማስቆም አልጣሩም ተብለዉ በሰፊዉ እየተወቀሱ ነዉ።ቅሬታ፤ ወቀሳና ትችቱ የፖለቲካና የፀጥታ ባለስልጣናት ራሳቸዉ የግጭቱ  አካል ናቸዉ የሚል ጥያቄና ጥርጣሬ እያጫረ ነዉ።

የአንዱ ወይም የሌላዉ ኃይማኖት መሪዎችና ተከታዮች ነን የሚሉ ሰዎች ግጭቱ እንዲባባስ የሚደርጉት ቅስቀሳ፣ ዛቻና በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚያሰራጩት ስድብ፣ ጠብ ጫሪ መልዕክት እንደቀጠለ ነዉ። በዛሬዉ ዉይይታችን ለምን? እንዴት እንላለን።

ነጋሽ መሐመድ

ልደት አበበ