1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ፤ ከትምህርት ገበታ ውጭ ለመሆን የተገደዱ ሕፃናት

ማክሰኞ፣ ሰኔ 11 2016

ኢትዮጵያ ውስጥ በቅድመ መደበኛ፣ በመጀመሪያ እና 2ኛ ደረጃ ላይ ያሉ17 ሚሊዮን የሚጠጉ ሕፃናት ከትምህርት ውጪ መሆናቸውን ዩኒሴቭ (UNICEF) አስታወቀ። ዩኒሴፍ 3.5 ሚሊዮን የሚገመቱ በአንደኛ ደረጃና በሁለተኛ ደረጃ የሚገኙ ሕፃናት ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ሥጋት መጋለጣቸውንና ይህም ትምህርት ላይ የተጋረጠውን ቀውስ የበለጠ ማባባሱን ገልጿል።

https://p.dw.com/p/4hC4o
የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት
የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅትምስል Denis Balibouse/REUTERS

ከትምህርት ገበታ ውጭ ለመሆን የተገደዱ ሕፃናት

ኢትዮጵያ ውስጥ በቅድመ መደበኛ፣ በመጀመሪያ እና 2ኛ ደረጃ ላይ ያሉ 17 ሚሊዮን የሚጠጉ ሕፃናት ከትምህርት ውጪ መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) አስታወቀ። ዩኒሴፍ 3.5 ሚሊዮን የሚገመቱ በአንደኛ ደረጃ እና በሁለተኛ ደረጃ የሚገኙ ሕፃናት ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ሥጋት መጋለጣቸውንና ይህም ትምህርት ላይ የተጋረጠውን ቀውስ የበለጠ ማባባሱን ገልጿል። 

የኢትዮጵያ ሥርዓተ ትምህርት "ችግር ፈቺ ያልሆነ፣ የሀገሪቱን ኑሮ እና ተጨባጭ ጉዳዮች የማይመለከት መሆኑ" በውጤትም ሆነ በጥራት ማሽቆልቆል እየታየበት መሆኑን አንድ የትምህርት ባለሙያ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። በጦርነትና ግጭት ክፉኛ እየተጎዳ ያለው የኢትዮጵያ የትምህርት ሁኔታ፤ ከዚያም ያለፉት የመንግሥት ሠራተኞች በደሞዝ ማነስ እየተፈተኑ ለትምህርት የሚሰጠውን ዋጋ እየጌዳ ስለመሆኑ ይነገራል። 
የዩኒሴፍ ትምህርትን የተመለከተው መረጃ ምን ያሳያል?

ትምህርት ሚኒስቴር ኢትዮጵያ ውስጥ ከጠቅላላ ትምህርት ሰጪ 47 ሺህ ገደማ ትምህርት ቤቶች ደረጃቸው የላቁት አራት ናቸው ማለቱ ባለፈው ዓመት የተሰማ አስደንጋጭ እውነታ ሆኖ አልፏል። 
በኢትዮጵያ ውስጥ ለሁሉም ሕፃናት ትምህርትን ለማረጋገጥ ጥረቶችን እንደሚመራ ያስታወቀው የመንግሥታቱ ድርጅት የሕፃናት መርጃ ማዕከል ትናንት ባወጣው መረጃ ደግሞ 17 ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያዊያንሕፃናትና ታዳጊ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ናቸው። በእርግጥም የዚህን ቁጥር ተጨባጭነት ከባለቤቱ ለማረጋገጥ ወደ ትምህርት ሚኒስቴር የሥራ ኃላፉዎች ብንደውልም ምላሽ ልናገኝ አልቻልንም።

የአፍሪካ ሕፃናት ቀንን በማስመልከት 'በአፍሪካ ላሉ ሕፃናት ሁሉ ትምህርት መስጠት ጊዜው አሁን ነው!' በሚል በኢትዮጵያ የሚገኘው የዩኒሴፍ ጽ/ቤት፤ መንግሥታት የቅድመ መደበኛ ትምህርትን ቅድሚያ እንዲሰጥ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጪ ቆጣቢ የትምህርት ዝግጅቶችን እንዲያሰናዱ ጥሪ አድርጓል። "ትምህርት ዕድል ብቻ አይደለም" የሚሉት በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ ኃላፊ፣ ትምህርት "ለሕፃናት ሁለንተናዊ ዕድገት እና ለወደፊት ሕይወታቸው ሰፊ እድሎችን ለመክፈት ቁልፍ ነው" ሲሉ መናገራቸውን ድርጅቱ ለ ዶቼ ቬለ በላከው መግለጫ አመልክቷል። 

ዩኒሴፍ በቅርቡ በተገመተ ባለው መረጃ በኢትዮጵያ ውስጥ ከትምህርት ውጪ ናቸው ካላቸው 17 ሚሊዮን የሚጠጉ ሕፃናት መካከል ግማሽ ያህሉ ሴቶች ናቸው። ስለ ተማሪዎች ይህ የመባሉን ያህል "አማራጭ ያጡ ሰዎች ናቸው መምህር እየሆኑ ያሉት" የሚለውን ከራሳቸው ከመምህራን አንደበት መስማት በራሱ ትምህርት ላይ ሌላ የከፋ አደጋ መደቀኑን ያሳያል። ዩኒሴፍ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በቅርበት በመተባበር በትምህርት ፖሊሲ ማዕቀፍ፣ በአጠቃላይ ትምህርት ሥርዓተ ትምህርት ማሻሻያ እና የዲጂታል ትምህርት ስልት እና በሌሎች ዘርፎች የኢትዮጵያን ትምህርት ለማሻሻል እየጣረ መሆኑን ገልጿል። 

የትምህርት ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ሰለሞን በላይ ለዶቼ ቬለ እንዳሉት ከሆነ ግን የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት "ከቅኝ ግዛት" መውጣት ይኖርበታል። የኢትዮጵያ የትምህርት ሁኔታ በመምህር እና በባለሙያ ዕይታ የዚህ ዜና ዘጋቢ ጋዜጠኛ ከዓመታት በፊት ትምህርት ላይ ያተኮሩ ሳምንታዊ የሬድዮ ዝግጅቶችን ለሦስት ዓመታት ግድም ሰርቷል። ዘጋቢው የቅድመ መደበኛ ትምህርት ላይ ጠንክረው የሠሩ መምህራንና ትምህርት ቤቶች ምን ያህል ታታሪ ተማሪዎችን ማፍራት እንደቻሉ በክፍል ውስጥ  ተመልክቷል።

ከዚህ በተጨማሪም በየ መጀመርያ እናሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ብቃት ያላቸው መምህራን እጥረት አሳሳቢ ችግር መሆኑን፣ መምህራን በተረጋጋ ሁኔታ አንድ ትምህርት ቤት ላይ ለረጅም ጊዜ እንደማያስተምሩ፣ በተለይ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለደረጃው የሚመጥኑ እውቀቶችን የቀሰሙ ተማሪዎችን ለማፍራት በብርቱ ሲቸገሩ ጭምር ተመልክቷል። በእርግጥም የመሰረተ ልማት ችግር ሌላው በትኩረት መታየት ያለበት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑንም እንዲሁ። በአማራ ክልል ላለፉት አሥር ወራት በሚደረገው ዉግያ የደረሰውን ጉዳት ሳይጨምር ሰሜን ኢትዮጵያን ክፉኛ ጎድቶ ባለፈው ጦርነት፤ በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ከሰባት ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉና በከፊል መውደማቸውን ትምህርት ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ