1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ ከመሬት ጋ ተያያዥ አዋጅ ጸደቀ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 18 2016

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 34ኛ መደበኛ ስብሰባ፦ «የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሳ የሚከፈልበትን እና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቁሙበት የተባለ» አዋጅን አፀደቀ ።

https://p.dw.com/p/4hU9Z
Äthiopien Parlament Addis Abeba
ምስል Solomon Muche/DW

አዋጁ የያዛቸው ዝርዝር ጉዳዮች

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 34ኛ መደበኛ ስብሰባ፦ «የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሳ የሚከፈልበትን እና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቁሙበት የተባለ» አዋጅን አፀደቀ ። የተጋነነ የካሳ ተመን እና የክፍያ ጥያቄን በማስቀረት ፍትሐዊነትን ለማስፈን ይረዳል በሚል ማሻሻያ የተደረገበት አዋጅ፤ ለልማት ሥራ የተፈለገን መሬትም ይሁን ንብረት የመገመት፣ ካሳ የመክፈል እና የማንሳት ሥራን ሙሉ በሙሉ ለክልሎች እና ለከተማ አስተዳደሮች የሰጠ ነው ። ምክር ቤቱ በባንክ ሥራ ረቂቅ አዋጅ ላይም ተወያይቷል ። የውጭ ባንኮች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሠሩ የሚፈቅደው ይህ ረቂቅ አዋጅ የእጅ አዙር የኢኮኖሚ ቅኝ ግዛትን እንዳያስከትል ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ የሚያስችል ድንጋጌ እንዲኖረው ተጠይቋል ። የ

አዋጁ የያዛቸው ዝርዝር ጉዳዮች

ዛሬ በነበረውየሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  33ኛ መደበኛ ጉባኤ በአራት ተቃውሞ እና በስድስት ድምፅ ተዓቅቦ በአብላጬ ድምፅ የፀደቀው "ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትን፣ ካሳ የሚከፈልበትን እና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቁሙበትን ሁኔታ ለመወሰን" የወጣው የማሻሻያ አዋጅ፤ "ለልማት ተነሺዎች ከሚከፈለው የካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ የመሠረተ ልማት ገንቢው ተቋም ካሳ እንዲፈጽም፣ የወሰን ማስከበር ሥራዎችን እንዲያከናውን እንዲሁም መሠረተ ልማቱንም እንዲገነባ" ይፈቅዳል። ይህም አላስፈላጊ ጫና እና የጊዜ ብክነትን ያስቀራል ተብሏል።

ለልማት የሚነሱ ንብረቶች ከሚያወጡት ዋጋ በላይ እጅግ የተጋነነ ዋጋ እንዲከፈል ጥያቄ እየቀረበባቸው መሆኑ፣ የእርሻ ማሳዎች ከሚሰጡት ምርት በላይ እጅግ የተጋነነ ምርታማነት ከአንድ ማሳ እንደሚገኝ ተደርጎ ዋጋ እየቀረበላቸው በመሆኑ፣ መንግሥት ላልተገባ የካሳ ክፍያ ወጪ እየተዳረገ መሆኑ ለማሻሻያው አስፈላጊነት ምክንያት ሆነው ቀርበዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Solomon Muchie/DW

ከዚህ በፊት የፌደራል መንግሥት ለሚከናውነው የመሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ ከመሬት ይዞታቸው ለሚለቁ ባለይዞታዎች ካሳ የመክፈል ግዴታን ይወጣ የነበረው ራሱ የፌዴራሉ መንግሥት ሲሆን በማሻሻያው ግን ይህንን ኃላፊነት የሚወጡት ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች ወይም ወረዳዎች እንዲሆኑ ደንግጓል። እነዚህ የመስተዳድር አካላት የሚሰጡት ክፍያ "የንብረት ካሳ፣ የልማት ተነሺ ድጋፍ፣ የኢኮኖሚ ጉዳት ካሳ፣ የማሕበራዊ ትስስር መቋረጥ እና የሥነ ልቦና ጉዳት ካሳን" የሚያካትት መሆኑ በተሻሻለው አዋጅ ተካትቷል።

ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ካሣ የመክፈል አቅም እንደማይኖራቸው የተከራከሩ የምክር ቤት አባላት በአዲስ መልክ የተዋቀሩ ክልሎች "የሠራተኛ ደመወዝ የመክፈል አቅም ባጡበት ወቅት" መሰል ካሳዎችን እንዲከፍሉ አስገዳጅ ሕግ ማውጣቱ ተገቢነት የለውም ብለዋል።

የምክር ቤት አባላዬት ገንዘብ ያለው ለልማት የሚንቀሳቀስ አካል መሬት ካለው ሰው ጋር አብሮ ማደግ የሚችልበት አሰራር እንዲኖር፣ ቂም እና ቁርሾ የሚያስከትል የካሳ አወሳሰንና አከፋፈልን የሚያስቀር አሰራር እንዲዘረጋ፣ ለልማት የሚፈለግን መሬት በገንዘብ ብቻ ሳይሆን በመሬት ጭምር መካስ እንዲጠናከር ጠይቀዋል።

ምክር ቤቱ የተወያየበት የባንክ ሥራ አዋጅ

ምክር ቤቱ ሌላው የተወያየበት ሕግ የባንክ ሥራ ረቂቅ አዋጅ ሲሆን ድንጋጌው "ማንኛውም የውጭ ባንክ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ በባለቤትነት የሚይዘው የውጭ ባንክ ተቀጥላ እንዲያቋቁም ወይም የውጭ ባንክ ቅርንጫፍ እንዲከፍት ወይም የባንክ አክሲዮኖችን እንዲይዝ ሊፈቀድለት ይችላል" በሚል ደንግጓል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Solomon Muchie/DW

በተመሳሳይ "የውጭ ሀገር ዜጎች ወይም በውጭ ሀገር ዜጋ ባለቤትነት የተያዙ የኢትዮጵያ ድርጅቶች የባንክ አክሲዮን እንዲይዙ ሊፈቅድ ይችላል" በሚል ተደንግጓል።  ከዚህም ባለፈ "የውጭ ባንኮች ነባር የሀገር ውስጥ ባንኮችን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ በግዢ አማካኝነት እንዲይዙ" ረቂቁ ይፈቅዳል። የምክር ቤት አባላት የውጭ ባንኮች ለሀገር በቀሎቹ አደጋ እንዳይሆኑ፣ ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት እንዲበጅ ጠይቀዋል።

የባንክ ሥራ ረቂቅ አዋጅ በምክር ቤቱ በሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ በዝርዝር እንዲታይ ተመርቷል።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ