ኢትዮጵያ እንደ ዩጎዝላቪያ ወይስ…? | ኢትዮጵያ | DW | 02.08.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ እንደ ዩጎዝላቪያ ወይስ…?

ለችግሮቿ ጊዜያዊ መፍትሔ እያበጀች እዚህ የደረሰችው ኢትዮጵያ በበፍቃዱ ኃይሉ አስተያየት እንደ ሶሪያም፣ እንደ ሶማሊያም፣ እንደ ቬንዙዌላም፣ ወይም ደግሞ ዕድል ከቀናት ዴሞክራሲያዊት የመሆን ዕድል አላት። ጥያቄው እንዴት የሚለው ነው።

በፍቃዱ ኃይሉ

ኢትዮጵያ በብሔር የአስተዳደር ወሰን የተከፋፈለውን ፌዴራሊዝሟን ለመመሥረት ደፋ ቀና እያለች በነበረችበት ወቅት፥ ዩጎዝላቪያ እየፈራረሰች ነበር። ሆኖም ከዩጎዝላቪያ ስህተት እንዳልተማረች የሚከራከሩ ፖለቲከኞች የፌዴራሊዝም ስርዓቱ ከተፀነሰበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ድምፃቸው ከዕለት ዕለት እየጎላ ነው። ለመሆኑ ስጋታቸው እውን የሚሆንበት ዕድል ይኖር ይሆን?

የኢትዮጵያ እንደ አንድ አገር የመቀጠል እና ያለመቀጠል ጉዳይ ሲነሳ እንደሟርት የሚቆጥሩት ብዙዎች ናቸው። “ኢትዮጵያ ትፈርስ ይሆን?” የሚለው ጥያቄ ሲነሳ በስሜት “አትፈርስም” ብለው የሚመልሱ ሰዎች የሚሰጧቸው ማስረጃዎች ከምኞት እና ተስፋ የበለጠ መሠረት የላቸውም። ኢትዮጵያ የግዛት አንድነቷን ጠብቃ መዝለቅ የምትችለው አንዳንዶች እንደሚያምኑት “ቅዱስ አገር” ስለሆነች ወይም በተአምር ሳይሆን፥ በመንግሥት እና የዜጎቿ ጥረት፣ ችግሮችን ለመጋፈጥ እና ተነጋግሮ ለመፍታት ባላቸው ቁርጠኝነት ነው።

ኢትዮጵያ እንደ ዩጎዝላቪያ…

ዩጎዝላቪያ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ የዘውዳዊ ስርዓት ውስጥ ያለፈች አገር ነበረች። በዘውዳዊው ስርዓት ውስጥ ሰርቦች የበላይነት ነበራቸው። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተመሠረተው የዩጎዝላቪያ ፌዴራላዊ ሶሻሊስት ሪፐብሊክ ሰባት ክልላዊ መንግሥታት እና ሁለት ራስ ገዝ አስተዳደሮች ነበሩት። ለ27 ዓመታት ያክል በአምባገነናዊ አገዛዝ ዩጎዝላቪያን የመሩት ማርሻል ጆሲፕ ቲቶ እ.ኤ.አ. በ1980 ሲሞቱ የዩጎዝላቪያ ፌዴሬሽን አባላት መሥማማት ስለተሰናቸው እየተፈራረቁ በመግዛት አገራቸውን እንደ አንድ ማስቀጠል የቻሉት ከ10 ዓመታት ላልበለጠ ጊዜ ብቻ ነበር። በወቅቱ የብሔርተኝነት ጣሪያ ላይ ደርሰው እርስ በርስ ሲቆራቆዙ የነበሩት በተለይ ሰርቦች እና ክሮአቶች የሁለት የክርስትና እምነቶች (ኦርቶዶክስ እና ካቶሊክ) ተከታዮች ከመሆናቸው በቀር፣ ጥቂት የታሪክ አረዳድ እና የጋራ ቋንቋቸውን የሚጽፉባቸው (ሲርሊክ እና ላቲን) ፊደል ልዩነቶች ብቻ ነበሩ ማለት ይቻላል። በዚህ ጊዜ ፌዴሬሽኑ ላልቶ ኮንፌዴሬሽን መስሎ ነበር ይባላል። የአባል መንግሥታቱ ብሔርተኝነት እየገነነ ሔዶ ለፓርቲ ስንጥቃት ስለዳረጋቸው፥ ብዙ ነፍስ የጠፋበትን የእርስ በርስ ጦርነት ካደረጉ በኋላ ዩጎዝላቪያ ፈርሳ አሁን በቦታው ሰባት ሉዓላዊ አገራት ተፈጥረዋል።

በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ለተመለከተው ኢትዮጵያ ቀስ በቀስ ወደ ዩጎዝላቪያ እያዘገመች መምሰሏ ምንም አስገራሚ ነገር የለውም፤ ሌላው ቀርቶ በዩጎዝላቪያ ፌዴሬሽን አባል አገራት ያለውን አለመግባባት የኢትዮጵያን ብሔረ-መንግሥታት እየጠቀሱ ቢናገሩት የኢትዮጵያ ታሪክ ሊመሥል ይችላል። በርግጥ አንዱ አገር ከሌላው ልማትም ይሁን ጥፋት ይማራል። ሆኖም በንፅፅሩ የሚዘነጋው የወቅቱ ዓለም ዐቀፍ ፖለቲካ ነው። ወቅቱ ሶቪየት ኅብረት የፈረሰችበት እና ኮሙኒዝም ከፍተኛ ውድቀት የደረሰበት ጊዜ ነበር። የዩጎዝላቪያ ገዢ ፓርቲም ኮሚኒስት እንደመሆኑ የዚህ ዓለም ዐቀፍ ውድቀት ገፈት ቀማሽ መሆኑ አይቀሬ ነበር።

ዓለም ዐቀፍ ሁኔታዎች እንደሚያሳዩት በግጭት ወይም በሽግግር ላይ ያሉ አገራት የመፈራረስ ዕጣ ፈንታቸው ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል። ስለሆነም ኢትዮጵያ የተጋረጠባት ስጋት እንደ ዩጎዝላቪያ መሆን ብቻ አይደለም። ወዲህ እንደ ሶሪያ፣ ወዲያ እንደ ቬንዙዌላም ሊሆን ይችላል።

ኢትዮጵያ እንደ ሶሪያ?

ከዓመታት በፊት የበሽር አል አሳድ መንግሥት የተነሳበትን ተቃውሞ በኀይል መመከት በመጀመሩ ምክንያት የሶሪያ ሕዝብ በዚህ ዘመን የማንጠብቀውን የጦርነት ግፍ እየቀመሰ ነው። ሶሪያ ዛሬ የመንግሥት ወታደሮች፣ የአማፂያን ቡድኖች እና አሸባሪው አይሲስ የሦስትዮሽ ውጊያ የሚያድጉባት የጦር አውድማ ሆና ከ350 ሺሕ በላይ ዜጎቿ ሕይወታቸው ሲያልፍ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩት ደግሞ በመላው ዓለም በስደት ተበትነዋል። ሶሪያ ከተሞቿ ፈርሰዋል። ዕርቀ ሰላም ቢወርድ እንኳን የማይሽር ጠባሳ ያፈራች አገር ሆናለች።

ኢትዮጵያ እንደ ዩጎዝላቪያ በብሔር በተከፋፈለ ፌዴራሊዝም ውስጥ ያለች አገር ብትሆንም፥ ፌዴሬሽኑን አፍርሰን ሉዓላዊ አገራት እንመሠርታለን የሚሉ ኃይሎች ከተነሱ ግን እንደ ዩጎዝላቪያ ሳይሆን እንደ ሶሪያ ማለቂያ የሌለው ትራጄዲ ውስጥ መግባትም ሌላው ዕጣ ፈንታዋ ሊሆን ይችላል። ግጭት አንዴ ከጀመረ አገሪቱ ከበርካታ አቅጣጫዎች በተለያዩ ጥቅም የተቧደኑ ኃይሎች ባለ ብዙ ጎን የጦር አውድማ የመሆን ዕድሏ የሰፋ ነው። ኢትዮጵያን እንደ ዩጎዝላቪያ መከፋፈል ቢያምራት እንኳን እንደ ሶሪያ የጦር አውድማ፣ አሊያም እንደ ሶማሊያ መንግሥት ሆና የመቆየት አደጋዋ የበለጠ የሰፋ ነው።

 

ኢትዮጵያ እንደ ቬንዙዌላ?

 

በአንድ ወቅት የሚያስጎመዥ የኢኮኖሚ ዕድገት የነበራት ላቲን አሜሪካዊቷ ቬንዙዌላ አሁን ላይ ፖለቲካ ወለድ የኢኮኖሚ ቀውስ ማሳያ ሆናለች። ዴሞክራሲን እና ሕዝበኝነትን አምባገነናዊ ስርዓት ለመገንባት ተጠቅመውበታል እየተባሉ የሚወቀሱት ሁጎ ቻቬዝ ቬንዙዌላን ለ14 ዓመታት ገዝተው ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ አገሪቷም ዱካቸውን ተከትላ ወደ አዘቅት ወርዳለች። ዛሬ ቬንዙዌላ በ10 ሚሊዮን ፐርሰንት የገንዘብ ግሽበት፣ 4 ሚሊዮን ቬንዙዌላውያን ስደት እና በ10 ሚሊዮን (የጠቅላላ ሕዝቧን ሲሦ ያክል) ሰብኣዊ ዕርዳታ ፈላጊዎች ሥሟ የሚነሳ አገር ሆናለች። ከዚህም በላይ ሁለት መንግሥታት እኔ ነኝ፣ እኔ ነኝ የሚሉባት አገር ሆናለች። እ.ኤ.አ. በ2018 ምርጫ የቻቬዝ ወራሽ የነበሩት ኒኮላስ ማዱሮ እና የረዥም ጊዜ የቻቬዝ ተቃዋሚ የነበሩት ዩዋን ጉዋይዶ፣ ሁለቱም የአገሪቱ ፕሬዚደንትነት አውጀው - የተለያዩ የዓለም አገራትን ድጋፍ ተካፍለው ሕዝባቸውን ከገባችበት የፖለቲካ ቀውስ የማያወጣ እሰጥ አገባ ውስጥ ናቸው።

ኢትዮጵያ በዚህ የፖለቲካ አካሔዷ ከቀጠለች እንደ ቬንዙዌላ ባለ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ መንግሥታት አገር የማትሆንበትም ምክንያት የለም።

ኢትዮጵያን እንደ ኢትዮጵያውያን

ኢትዮጵያ የግዛት አንድነቷን ጠብቃ ለመጓዝ መቻል አለመቻሏን አጠራጣሪ የሚያደርግ ፈተና ሲገጥማት ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም። ለችግሮቿ ጊዜያዊ መፍትሔ እያበጀች ግን እዚህ መድረስ ችላለች። አሁን ብዙ ፖለቲከኞች ከዩጎዝላቪያ ጋር ቢያመሳስሏትም መጨረሻዋ የዩጎዝላቪያን ብቻ መምሰል አለመመሠሉን መገመት አይችሉም። ኢትዮጵያ እንደ ሶሪያም፣ እንደ ሶማሊያም፣ እንደ ቬንዙዌላም፣ ወይም ደግሞ ዕድል ከቀናት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ልትሆን ትችላለች። ከዚህ ዓይነቱ አጣብቂኝ የሚያወጣት ሕዝባዊ ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረት ብልሕ ውሳኔ አሰጣጥ ብቻ ነው።

ገዢው ፓርቲ በመሪዎች ኩራት የተፈጠረው እና ውስጡ ያለውን ችግር መፍታት ከቻለ ስጋቱ በከፊል ይቀረፋል። ከዚያም ነጻነት እና ስርዓት ወይም ደኅንነት ማስጠበቅ ከቻለ እና ነጻ እና ፍትሓዊ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማሰናዳት ከሠራ፣ ብሎም ውጤቱን በፀጋ ከተቀበለ ብዙው ስጋት ተኖ የመጥፋት ዕድሉም ሰፊ ነው። የተቃዋሚ ፓርቲዎቹ እና ቡድኖችም የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት ይጠበቅባቸዋል።

ኢትዮጵያን ከሌሎች በፈተና ውስጥ ካለፉ እና እያለፉ ካሉ አገራት የሚለያት ምንም የለም። ዕጣ ፈንታዋ በፖለቲከኞቿ ውሳኔ ላይ የተንጠለጠ ነው። ፖለቲከኞቹ እንደ ዩጎዝላቪያ፣ ወይም እንደ ሶሪያ እና ቬንዙዌላ ፖለቲከኞች ወይስ እንደ ኢትዮጵያውያን ፍላጎት ይወስኑ ይሆን የሚለውን ጥያቄ ጊዜ ይመልሰዋል።

በዚህ አምድ የቀረበው አስተያየት የጸሐፊው እንጂ የዶይቸ ቬለ (DW)ን አቋም አያንጸባርቅም።