1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ ችግር ስለበዛባት ለጀማሪ ኩባንያዎች ብዙ ዕድል አለ- አቶ አዲስ አለማየሁ

ረቡዕ፣ መስከረም 27 2013

አቶ አዲስ አለማየሁ አዋጪ የንግድ ሥራ ሐሳብ ካላቸው ሥራ ፈጣሪዎችና ጀማሪ ኩባንያዎቻቸው ጋር ይሰራሉ። መኖሪያ ቤትና የግል መኪናውን ሸጦ የካልሲ ማምረቻ ፋብሪካ ለማቋቋም የወጠነው ኑርልኝ ዘላለም የገንዘብ ችግር ሲገጥመው የታደጉት አቶ አዲስ ናቸው።ባለፈው እሁድ ሥራ የጀመረው ፋብሪካ በቀን ከ190 ሺሕ በላይ የተለያዩ አይነት ካልሲዎችን ያመርታል

https://p.dw.com/p/3jaBt
Äthiopien Wirtschaft l Dante Strick- und Sockenhersteller - Kazana Group
የካዛና ግሩፕ ሊቀ-መንበር አቶ አዲስ አለማየሁ እና የዳንቴ ካልሲ ማምረቻ ፋብሪካ መሥራች እና ሥራ አስኪያጅ ኑርልኝ ዘላለምምስል Addis Alemayehou

«የጀማሪ ኩባንያዎች ፈተናዎችና የባለወረቶች ሚና»

በባሕር ዳር ከተማ የተቋቋመው ዳንቴ ፋብሪካ ባለፈው ሳምንት እሁድ የመጀመሪያውን ጥንድ ካልሲ ለማምረት ከመብቃቱ በፊት መሥራቹ ኑርልኝ ዘላለም በያዘው ውጥን ጓደኞቼ እምነት አልነበራቸውም። የግል ሥራውን አቋርጦ የራሱን ኩባንያ ለመመሥረት ሲነሳ ባለቤቱን ጭምር ተስፋ አስቆርጦ ነበር።

"ጓደኞቼ ኑርልኝ ያበደ ሐሳብ ይዞ እየነሆነለለ ነው አሉ። ሁለት ጓደኞቼ ብቻ አልሸሹኝም። አልፎ አልፎ እየመጡ የቤት ኪራይ እየከፈሉ፤ የሻይ የቡና እየሰጡኝ ይሔዱ ነበር። መሐል ላይ ነገሮች ፈታኝ ሆኑ። አንድ ልጅ አለን። የሚስቴ ደሞዝ ከእኔ ገቢ አንፃር ለእኛ ቤት ምንም አልነበረም። በእሷ ደሞዝ ብቻ መኖር ሲጀመር አንድ አመት ለመቋቋም ሞከረች። ልጃችን ለትምህርት ሲደርስ ተስፋ መቁረጥ ጀመረች" የሚለው ኑርልኝ ዘላለም ተወልዶ ያደገው፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምክርቱንም ያጠናቀቀው በባሕር ዳር ከተማ ነው። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተማረ በኋላ በፌድራል ዋና ኦዲተር ቢሮ፣ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ እና በቱርክ የጨርቃ ጨርቅ አምራች ኩባንያዎች በሙያው ሰርቷል። ከተቀጣሪነት ወደ ፋብሪካ ባለቤትነት ያደረገው ሽግግር የሚጀምረው የመኖሪያ ቤት እና የግል መኪናውን ከመሸጥ ነው።

"ባሕር ዳር ላይ አባታችን ያወረሰን አንድ ቤት ነበረ። እሱ ቤት ነው የተሸጠው። መኪና ነበረኝ የምጠቀምበት፤ እሱን ነው የሸጥኩት። አንድ ልጅ አለኝ፤ ስድስት ሰባት ሺሕ ብር የቤት ኪራይ እከፍላለሁ፤ ሚስቴ አንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ትሰራለች። ሥራ አቋርጬ፤ ቤት እና መኪና ተሸጦ ቀውስ ሲገጥም የቤት ኪራይ መክፈል አልችልም ነበር" ሲል በወቅቱ የገጠመውን ፈተና መለስ ብሎ የሚያስታውሰው ወጣት በአዲስ አበባ ከግብርና ሚኒስቴር ፊት ለፊት በነፃ የሚያገኘውን ዋይፋይ እየተጠቀመ ድንጋይ ላይ ተቀምጦ ሸሪክ እስከማፈላለግ ደርሶ ነበር።

ኑርልኝ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገረው ካልሲ የሚያመርት ፋብሪካ ለማቋቋም የንግድ ፈቃድ ያወጣው ከሶስት አመታት በፊት ነበር። ለሥራው የሚያስፈልገውን ቦታ በባሕር ዳር ከተማ የተከራየው ኑርልኝ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሊዝ ፋይናንሲንግ በተባለው አሰራር ለኑርልኝ በሚሰጠው ብድር ለማምረቻ የሚያስፈልጉትን ማሽኖች ሙሉ ወጪ ሊሸፍን ውል ነበራቸው።

"በሊዝ ፋይናንሲግ [የኢትዮጵያ ልማት ባንክ] መቶ በመቶ የማሽኑን ወጪ ይሸፍናሉ። የሥራ ማስኬጃውን እኛ ይዘን እንነሳለን። የቱርክ ፋብሪካዎች ጥሬ ዕቃ በብድር እንዲሰጡኝ፤ የሥራ ማስኬጃውን የሚደግፉኝ ነበሩ።  በመሀል [የኢትዮጵያ ልማት ባንክ] መቶ ፐርሰን ሊዝ የነበረውን 20 በመቶ ወጪውን ሸፍን አሉ። ስለዚህ 80 በመቶ ከባንኩ 20 በመቶ ደግሞ ከእኔ ሲሆን የእኔን የሥራ ማስኬጃ ባንኩ ወሰደው። ያኔ የመጋዘን ኪራይ መክፈል አልቻልኩም። ብድሩን ለመፍቀድም አንድ አመት ዘገዩ። መጀመሪያ ከተነሳንው በጀት ከአንድ አመት በኋላ የዶላር የምዛሪ ተመን ከ21 ብር ወደ 25 ብር ገደማ ሲገባ፤ ቻይና ያለው የማሽን አቅራቢ ዘገያችሁ ብሎ ዋጋ ሲጨምር ይዘን ከተነሳንው ጨመረ። የአንድ አመት የመጋዘን ኪራይ በወር 30 ሺሕ ብር በአመት ወደ 360 ሺሕ ብር ስንከፍል ቆየን" ይላል።  

Äthiopien Wirtschaft l Dante Strick- und Sockenhersteller - Kazana Group
በባሕር ዳር ከተማ የተቋቋመው ዳንቴ የካልሲ ማምረቻ ፋብሪካምስል Addis Alemayehou

ዕቅዱ ተንገራገጨ። ጓደኞቹ "ኑርልኝ ያበደ ሐሳብ ይዞ እየነሆነለለ ነው" ያሉት ይኼኔ ነበር። ይኸ ሁሉ ሲሆን ፋብሪካውን ሥራ የሚያስጀምሩት ማሽኖች ከኑርልኝ ዘንድ አልደረሱም። ስለዚህ አጋር መፈለግ ነበረበት። የካልሲ ፋብሪካዎችን ጨምሮ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ አስር ኩባንያዎች እና ግለሰቦች "ከ30 እስከ 50 በመቶ ድርሻ ወስደው" በሽርክና አብረውት እንዲሰሩ አማከረ። ሐሳቡን ያደመጡ አብረውት ለመሥራት ፈቃደኛ እንደነበሩ የሚያስታውሰው ኑርልኝ እንደሚለው "ያኔ በአገሪቱ የነበረው ቀውስ እና አለመረጋጋት ደፍረው በባሕር ዳር ኢንቨስት ለማድረግ አላስቻላቸውም።" ይኼኔ ነበር ኑርልኝ በፋና ቴሌቭዥን በሚተላለፍ የሥራ ፈጣሪዎች ውድድር ወደ ተመለከታቸው አቶ አዲስ አለማየሁ ዘንድ ሊክድኢን በተባለው የባለሙያዎች ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ መልዕክት የሰደደው።

መልዕክቱ "ፕሮጀክቴ በባንክ ጸድቋል። ይኸን ያክል ገንዘብ በባንክ አስቀምጥ ተብያለሁ። እኛ ሥራውን ስንጀምር 800 ሺሕ ብር ነበረ። በባንክ አስቀምጡ የተባልንው 1.5 ሚሊዮን ብር ሆነ። ከያዝኩት 800 ሺሕ ብር ላይ ለመጋዘን ኪራይ ከፍለን ገንዘቡ ወርዷል። የጸደቀ ብድር ነው። ከእኛ ጋር ስራ" የሚል ነበር።

ከአቶ አዲስ አለማየሁ "የንግድ ሥራ ዕቅድህን ለፕራግማ ኮንሰልቲንግ ላክ አለ" የሚል መልስ የደረሰው ኑርልኝ የተባለውን አደረገ። ከአስራ አምስት ቀናት በኋላ አቶ አዲስ በሰጡት ቃል መሠረት ፕራግማ የመዋዕለ ንዋይ አማካሪ ኩባንያ ባለሙያዎች መልስ ሰጡ። "ቢዝነሱን ከእነሱ ጋር ማውራት ጀመርን። ተቀበሉት። ሥራው ያዋጣል ብዬ ብቻ ሳይሆን ሥራው እንዴት ይሰራል? የት ያልቃል? የት ይደርሳል የሚለውን ብዙ ነገር ከተነጋገርን በኋላ ደስተኛ ሆኑ" በማለት ሒደቱን ያስረዳል።  

ኑርልኝ የጠቀሳቸው አቶ አዲስ አለማየሁ በመጨረሻ ዳንቴ የተባለው ፋብሪካ ካልሲ ማምረት እንዲጀምር የንግድ ሥራ ዕቅዱን ገምግመው የሚያስፈልገውን ገንዘብ ያቀረቡለት ባለወረት ናቸው። ኑርልኝ እና ፕራግማ የተባለው የመዋዕለ ንዋይ አማካሪ ኩባንያ በአዋጪነቱ ላይ ከተስማሙ በኋላ የንግድ ሥራ ዕቅዱን ወደ ማስተካከል አመሩ።

መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው ፕራግማ የመዋዕለ ንዋይ አማካሪ በካዛና ግሩፕ ሥር ከሚገኙ አስራ አራት ኩባንያዎች አንዱ ነው። የካዛና ግሩፕ ሊቀ-መንበር አቶ አዲስ አለማየሁ በኢትዮጵያ የግሉ ክፍለ ኤኮኖሚ ወጣት የስራ ፈጣሪዎችን እና ጀማሪ ኩባንያዎች በመደገፍ ከሚታወቁ ግንባር ቀደም ባለወረቶች አንዱ ናቸው።

Äthiopien - Junge Young Unternehmer pitchen Ihre Start-Up-Ideen für potentielle Investoren
የካዛና ግሩፕ ሊቀ-መንበር አቶ አዲስ አለማየሁ ምስል BlueMoon Ethiopia

"ሁሉ ነገር ገና አልተነካም ብዬ ነው የማምነው። የማምረቻው ዘርፍ፣ የግብርናው ዘርፍ፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ብትል፤ ሁሉን ነገር ገና ሀ ብለን የምንጀምር አገር ነን" የሚሉት አቶ አዲስ ካዛና ግሩፕ በማናቸውም የሥራ ዘርፍ የሚቀርቡ የንግድ ሥራ ዕቅዶችን ገምግሞ አዋጪ ሆነው ከተገኙ አብሮ እንደሚሰራ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

"ፕራግማ ኢንቨስትመንት ኮንሰልቲንግ በተባለው ተቋም መርዕድ እና ካሊድ የሚባሉ ልጆች አሉ።የእነሱ የመጀመሪያ ሥራ ልጆች ወይም ድርጅቶች እና ጋ ማመልከቻ ሲያስገቡ እውነት ድርጅቱ አለወይ? ሐሳቡ ያዋጣል ወይ? ዘርፉን እናጠናለን። እነዚህ ከተሰሩ በኋላ ከዚያ ወደ ወረቀት ሥራ እንገባና ምን ያክል መዋዕለ ንዋይ በምን ያህል የአክሲዮን ድርሻ የሚለውን በመደራደር ነው ኢንቨስት የምናደርገው" ብለዋል አቶ አዲስ።

የቴሌቭዥን መርሐ-ግብሮችን እና ፊልሞች በክፍያ ለማሰራጨት የተቋቋመው አቬቶል፣ የደረቅ ጭነት ማመለሻ ኩባንያዎችን ከደንበኞቻቸው ለማገናኘት ያቀደው አክሮስ ኤክስፕረስ፣ ቃና ቴሌቭዥን እና ካልሲ የሚያመርተው የኑርልኝ ዳንቴ ኩባንያ ጭምር በካዛና ግሩፕ ሥር ይገኛሉ። በኢትዮጵያ ገበያ ለእንደነዚህ አይነት ጀማሪ ኩባንያዎች በርከት ያሉ ፈተናዎች ቢኖሩም አቶ አዲስ "ሁሉም ድርጅቶች እየሰሩ ነው። ፈተና አለ። አንድ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ኩባንያ ነው ያለን። ኔትወርክ ሲቋረጥ ወይ ችግር ሲኖር ሁለተኛ ምርጫ የለህም። ያም ሆኖ ሥራ እየሰራን ነው። ከእኔ ይበልጥ [ከኢትዮጵያ] ውጪ አገልግሎት የሚሰጡ፤ ደንበኞች ያሏቸው፤ የሶፍትዌር ማበልጸግ ሥራ የሚሰሩ ልጆች አውቃለሁ። ሁሉ ነገር አሪፍ እስኪሆን እንጠብቅ ካልን ብዙ ጊዜ እንጠብቃለን ማለት ነው። እኔ እንዲያውም አሁኑኑ ሥራውን ጀምረን እያለማመድን የምናሰለጥነውን እያሰለጠንን ሥራውን መቀጠል ነው ብዬ ነው የማምነው። ስለዚህ አሁን ባለው ሁኔታ ምን መስራት እንችላለን? አሁን ባለው ሁኔታ የት መጀመር እንችላለን? ብለን ነው እነዚህን ነገሮች የጀመርንው" ብለዋል።

ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው የንግድ ፈቃዱ ከወጣ ከሶስት አመታት በኋላ ለገጠሙት ፈተናዎች መላ እየዘየደ ባለፈው ሳምንት ማምረት የጀመረው ዳንቴ የካልሲ ማምረቻ ነው። ፋብሪካው ለጎልማሶች እና ዕድሜያቸው ከስምንት አመት በላይ ለሆናቸው አዳጊዎች በቀን ከ15 ሺሕ በላይ ዶዘን ወይም ከ190 ሺሕ በላይ የተለያዩ አይነት ካልሲዎችን ያመርታል።

"ከውጪ ጥሬ ዕቃ ለማምጣት ኤክስፖርት ማድረግ አለብህ። የተሻለ ትርፍ ለማግኘት ደግሞ በአገር ውስጥ ገበያ መሸጥ አዋጪ ነው" የሚለው ኑርልኝ ከዳናቴ ምርቶች "40 በመቶውን ወደ ውጪ ለመላክ 60 በመቶውን ደግሞ ለአገር ውስጥ ገበያ ለመሸጥ" አቅዷል።  

በአዲስ አበባ መርካቶ፤ በባሕር ዳር እና በጎንደር ማከፋፈያዎች ለመክፈት መዘጋጀታቸውን የገለጸው ኑርልኝ "ጥራቱን የጠበቀ ጥሬ ዕቃ የምናገኘው ከቻይና፣ ከባንግላዴሽ፣ ከቱርክ እና ከመሳሰሉት አገሮች ነው። እኛ አገር ያሉ ጥሬ ዕቃዎች ብዙውን ጊዜ የምርቱ ጥራት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። ከውጪ ማስገባት በማንችል፤ የዶላር እጥረት በሚኖር ጊዜ የውጭ አገር የጥራት ደረጃ ያላቸው ክሮችን ወደ ኢትዮጵያ የሚያስገቡ አቅራቢዎች አሉ። በእነሱ ተክተን እንጠቀማለን። አሁን በአንድ ፈረቃ ነው እየሰራን ያለንው። የደንበኞቻችን ትዕዛዝ ሲደርስ በሶስት ፈረቃ እንሰራለን። በ25 ማሽኖች በአጠቃላይ ወደ 45 ሰራተኛ አካባቢ ቀጥረናል" ብሏል።

Äthiopien Wirtschaft l Dante Strick- und Sockenhersteller - Kazana Group
በባሕር ዳር ከተማ የተቋቋመው ዳንቴ የካልሲ ማምረቻ ፋብሪካምስል Addis Alemayehou

አዲስ አበባ ተወልደው ኬንያ ያደጉት አቶ አዲስ የኢትዮጵያ ገበያ እንደ ኑርልኝ ላሉ ለጀማሪ ኩባንያዎች እና ሥራ ፈጣሪዎች ፈታኝ በመሆኑ ይስማማሉ። "ኩባንያውን ቶሎ ማስመዝገብ፤ ሁለተኛ ደግሞ ትልቁ ማነቆ የሚሆነው የፋይናንስ ጉዳይ ነው። ብዙ ጊዜ አሜሪካን ወይም በምዕራቡ አገሮች ጀማሪ ኩባንያዎች ገንዘብ የሚያገኙት ወይ ከግለሰብ ወይ ግለሰቦች አንድ ላይ ሆነው ኢንቨስት የሚያደርጉበት መልክ አለ። አሁን እኛ አዲስ አበባ ውስጥ አዲስ ኤንጅልስ ብለን ያቋቋምንው ያንን ለማድረግ ነው። አንድ ስድስት ጓደኛሞች አንድ ላይ ሆነን ኢንቨስት እናደርጋለን። ያ እንደ ቬንቸር ልትቆጥረው ትችላለህ። ገንዘብ ያለው ሰው ፎቅ መግዛት ይችላል፤ ወይ የአስር ሚሊዮን ብር መኪና መግዛት ይችላል፤ ወይ ድርጅቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ይችላል። የኬንያ መንግሥት የጀማሪ ኩባንያዎች ፈንድ እና ፖሊሲ ሊቀይር ነው። የተሻለ አበረታች ለማድረግ ማለት ነው። እኛ በባንክ አገልግሎትም ፣ በፊንቴክም ሆነ በሁሉም ዘርፍ ከኬንያ  ቢያንስ አንድ አስር አስራ አምስት አመት ወደ ኋላ ነን ብዬ ነው የማየው። ግን ደስ የሚለው ግን ኢትዮጵያ ሁሉንም ቀስ ብለን ስለምንጀምር ሳናጠፋ ብዙ የምንማራቸው ነገሮች አሉ። ገና ከመጀመራችን ሌሎቹ እንዴት ሰርተውታል? ምን መማር እንችላለን? ለእኛ የሚሆነው የትኛው ነው? ብለን ነው በመንግሥትም በኩል ፖሊሲም የምናወጣው፤ በግሉም ዘርፍ እንደዚያ ነው። እኔ ኬንያ ስላደኩ እዚያ ብዙ ግንኙነት ስላለኝ እዚያ ሔጄ አይቼ፤ ኬንያ ውስጥ የሚያዋጣ ሥራ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ያዋጣል ብዬ ነው የማምነው።

የኑርልኝ ዳንቴ ካልሲ ማምረቻ ፋብሪካ እውን ሆኖ ሥራ እንዲጀምር የሚያስፈልገውን የገንዘብ መጠን ከካዛና ግሩፕ ያገኘው ከአንድ አመት በፊት ነው። ይኸ ለኑርልኝ ትልቅ እፎይታ ነበር። "እናትህ ሞታ በዘጠኝ በአስር አመትህ ተመልሳ ብትመጣ እና ልጄ ብላ አብራህ ብትኖር ማለት ነው። አዲስ ወንድም የሚሆንህ፤ ነገር የሚያቀልልህ ሰው ነው። የሆነ ነገር ስታወራው ነገሮችን እንዴት ማቅለል እንዳለበት ያውቃል" ብሏል።

እንደ ኑርልኝ ያሉ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች እና ጀማሪ ኩባንያዎቻቸው የመስሪያ ቦታ፣ የመስሪያ ገንዘብ እና የጥሬ ዕቃ እጦትን የመሳሰሉ ፈተናዎች አሉባቸው። የካዛና ግሩፕ መሥራች አቶ አዲስ አለማየሁ ከከፍተና የትምህርት ተቋማት በብዛት የሚመረቁ ወጣቶች መኖራቸውን ጠቅሰው ሥራ መፍጠር አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን ያስረዳሉ።

ከሶስት አመታት በኋላ ውጥኑ ፈር የያዘለት ኑርልኝ "አንድ የሥራ ፈጣሪ፤ አንድ ወጣት አዲስ ኩባንያ [ያመረትኩትን] ሸጬ ገቢ አገኛለሁ ብሎ ሲያስብ አብሮ ምን ማሰብ አለበት መሰለህ፤ በቀን ሶስቴ ይበላ የነበረውን ምግብ አንድ ጊዜ ብቻ ሊበላ እንደሚችል ማሰብ አለበት። ሁለተኛው ከአየር ጤና ፒያሳ ሙሉ ታክሲ ይጠቀም ከነበረ፤ ከአየር ጤና ጦር ኃይሎች በታክሲ ሔዶ ቀሪውን በእግሩ መሔድ መቻል አለበት። የእኔ የለመድኩት ሕይወት ተዛብቶ ነው ነገ የምቆመው ብሎ፤ ያ የሚዛባበትን የአንድ አመት ወይም የሁለት አመት ጊዜ አስቀድሞ መቀበል እና መሞከር አለበት። ቀድሞ ከተሳካለት በጣም ጥሩ ነው። ቀድሞ ካልተሳካለት ግን ሞራሉ አይወድቅም" በማለት ቀድሞ መዘጋጀት እንደሚገባ ጠቁሟል።

"ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም ብዙ ችግር አለ" የሚሉት አቶ አዲስ ይኸ ለወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ዕድል እንደሆነ ያምናሉ። "ወጣቶች አንደኛ ለችግር መፍትሔ የሚያመጣ የሥራ ሐሳብ ማምጣት አለባቸው። ሁለተኛ በቅጡ ጥናት መስራት አለባቸው" ያሉት አቶ አዲስ ሥራ ፈጣሪዎች እንደ ካዛና ግሩፕ ወዳሉ በገንዘብ ሊደግፏቸው ወደሚችሉ ኩባንያዎች ሲቀርቡ ምን ያክል ገንዘብ እንደሚያስፈልግ በአግባቡ መረዳት እና ማሳመን እንደሚገባቸው ገልጸዋል። "ለሥራው 100 ሺሕ ብር የሚጠይቁ ከሆነ በትንሹ እንኳን 2000 ሺሕ እና 3000 ሺሕ ብር የራሳቸውን ቢያዘጋጁ ባለወረቱን ያበረታታል" ብለዋል አቶ አዲስ።  

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ