ኢትዮጵያ፤ ባለበት የሚረግጠዉ ድርድር | ኢትዮጵያ | DW | 20.03.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ፤ ባለበት የሚረግጠዉ ድርድር

1997ቱ የምርጫ ማግስት ድርድር፤ የ2002ቱ የቅድመ ምርጫ ድርድር የጎሉትና የቅርቦቹ ናቸዉ። አንዳቸዉም ለአግባቢ ዉጤት አልበቁም።አግባብተዉ ከነበረም ማግባባታቸዉ ተነግሮ ሳበቃ፤ የነበር ዝክራቸዉ አግባብቷል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:17

ኢትዮጵያ፤ ባለበት የሚረግጠዉ ድርድር


የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ እና የተቃዋሚዎቹ ፖለቲከኞች ድርድር-ዉይይት ማለት ከጀመሩ ባለፈዉ ቅዳሜ ለስድስተኛ ጊዜ እንደገና ተሰበሰቡ። ተነጋገሩም። ንግግሩ በርግጥ ድርድር አልነበረም ሥለ ድርድር መደራደር እንጂ። ዉጤት-ሌላ ቀጠሮ። ሌላ ምክንያት፤- የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ምክትል ፕሬዝደንት።

 የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዝደንት።የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር።«ማደር አልነበረበትም»።ግን አደረ።ከማደሩ በፊት እና ከእንግዲሕስ? 

የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ለድርድር ዉይይት በርግጥ እንግዳ አይደሉም። ድሮ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የሸማቂ ሐይላት ድርድር እየተባለ ከካርቱም-ሰነዓ፤ ከካይሮ-ሞቃዲሾ፤ ከሞስኮ-ሐቫና ከሮም-አትላንታ፤ከለንደን -አዲስ አበባ ሌላም ጋ በግልፅም-በሚስጥርም ተነጋረዋል። ሽማግሌዎች ባትለዋል።በዙ ጊዜ፤ ብዙ ገንዘብ ጠፍቷል። ሁሌም አንድ ነገር ይሆናል።ኃይለኛዉ ሁሉንም ይወስዳል። 

ኢትዮጵያ በ1983 የመድብለ ፓርቲ ፖለቲካዊ ሥርዓት ከታወጀባት ወዲሕም ተቃዋሚዎች አንዳቸዉ ከሌላቸዉ በየጊዜዉ ይደራደራሉ፤ ተግባባን ይላሉ።ትብብር ይፈጥራሉ። ወዲያዉ ግን ይበተናሉ። ተቃዋሚዎች ከገዢዉ ፓርቲ ጋር ይደራደራሉ። 1997ቱ የምርጫ ማግስት ድርድር፤ የ2002ቱ የቅድመ ምርጫ ድርድር የጎሉትና የቅርቦቹ ናቸዉ። አንዳቸዉም ለአግባቢ ዉጤት አልበቁም። አግባብተዉ ከነበረም ማግባባታቸዉ ተነግሮ ሳበቃ፤ የነበር ዝክራቸዉ አግባብቷል። ጥሩነቱ የነበሩትን ድርድሮች

Karte Äthiopien englisch

ዉጤት አልቦነበት እየዘከረ ለሌላ ድርድር የሚዘጋጅ ወይም በሌላ ድርድር ስም ተቀናቃኞቹን ለማዘናጋት የሚያደባ ፖለቲከኛ ኢትዮጵያ በየዘመኑ ታፈራለች። ዛሬም-ጭምር።የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር የሺዋስ አሰፋ እንደሚሉት ግን የድርድር «ወጉ» ምን ሆነና። ያሁኑ ደግሞ በሕዝብ ግፊት የመጣ በመሆኑ የተለየ ነዉ።

                             

የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲ (መኢአድ) ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ሙሉጌታ ከበደም ድርድር የሠላማዊ ታጋይ ፓርቲቸዉ አንዱ አላማ ነዉ ባይ ናቸዉ።ያሁኑን ድርድርም በሕዝብ ጫና የመጣ ይሉታል።የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር እና የገዢዉ ፓርቲ ኢሕአዴግ ሊቀመንበር አቶ ሐይለማርያ ደሳለኝ ግን ድርድሩ የሕዝባዊ ተቃዉሞ ግፊት ዉጤት ነዉ መባሉን የሚቀበሉት አይመስሉም።ጠቅላይ ሚንስትሩ ባለፈዉ ሐሙስ ለምክር ቤታቸዉ ባቀረቡት ዘገባ እንዳሉት ፓርቲያቸዉ በድርድሩ የሚሳተፈዉ  ግፊትና ጫና ሥለተደረገበት አይደለም።የፓርቲያቸዉ «ጥልቅ» እና «ተሐድሶ» ያሉት እርምጃ ዉጤት እንጂ።ዳኛዉ ሕዝብ የሚፈርድበት ሥልት፤መንገድ እና ጊዜ በርግጥ አይታወቅም።የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ግን የጠቅላይ ሚንስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ምክንያት አይቀበሉትም።የኢዴፓ ፕሬዝደንት ዶክተር ጫኔ ከበደ አንዱ ናቸዉ።                                            

የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር የሺዋስ አሰፋ ደግሞ የዉጤት ምክንያት፤ የምክንያቱን አብነት ዘርዘር ያደርጉትል።  የመኢአድ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙሉጌታ ከበደ ያክሉበታል።

 የገዢዉ ፓርቲና የተቃዋሚዎቹ መሪዎች ለድርድሩ እንደ ምክንያት የሚጠቅሱት ካቃረናቸዉ ለመደራደር የተስማሙት ባልተስማሙበት ምክንያት ላይ ተመስርተዉ ነዉ ማለት ነዉ።ባልተስማሙበት ምክንያት ተስማምተዉ በጀመሩት ድርድር መድረክ ያቀረበዉ ጥያቄ ሌላ የማያስማማ ምክንያት መስሏል።መምሰል በርግጥ መሆን አይደለም።የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የሚያስተናብረዉ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ መሪ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የፓርቲያቸዉን ጥያቁ ባጭሩ አስረድተዉናል።

ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ብዙዎቹ ለመድረክ ጥያቄ መልስ መስጠት ያለበት ገዢዉ ፓርቲ ነዉ ባዮች ናቸዉ።ሐሳቡ ግን እስካሁን አላግባባም።ባለፈዉ ቅዳሜ የተደረገዉን ስድስተኛ ዙር ንግግር በሌላ ቀጠሮ ያሳደረዉ ልዩነት ግን የመድረግ ጥያቄ ወይም ሐሳብ አይደለም። የአደራዳሪዉ ማንነት እንጂ፤ ይላሉ የሰማያዊ ፓርቲ መሪ የሺዋስ አሰፋ።የሌሎቹ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችም ተመሳሳይ አቋም ነዉ ያላቸዉ። የመኢአድ ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ሙሉጌታ አበበን እንጥቀስ። ከእንግዲሕስ? የመድረክ መሪ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ «ኳሳ ያለችዉ ኢሕአዴግ ሜዳ ነዉ» ዓይነት ይላሉ።

ኢዴፓም ተመሳሳይ እምነት ነዉ ያለዉ። ዶክተር ጫኔ። የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ የእስካሁኑ ንግግር የወሰደዉን ያክል ጊዜ መዉሰድ አልነበረበትም ይላሉ። የከንግዲሁን ቀጠሮም «ጊዜ ማጥፊያ።»

   የመኢአዱ ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ሙሉጌታ አበበ ገዢዉ ፓርቲ በመጪዉ ቀጠሮ አቋሙን ይቀይራል የሚል ተስፋ አላቸዉ።ሌላ ተስፋ።ሌላ ቀጠሮ። መጋቢት 20። ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ

 

 

 

 

 

 

Audios and videos on the topic