ኢትዮጵያ በጀርመናዊትዋ ጋዜጠኛ እይታ | ባህል | DW | 21.11.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

ኢትዮጵያ በጀርመናዊትዋ ጋዜጠኛ እይታ

አዉሮጳን እርሱ ፤ ብሩህ ተስፋ እና ተስፋ የሚገኝበት አዲስ አበባ ነዉ ይሰኛል ባለፈዉ ወር መገባደጃ ላይ ዲ ቬልት የተሰኘዉ የጀርመን አንጋፋ ጋዜጣ ያስነበበዉ ርዕስ፣ በጀርመንኛ መጠርያዉ ዲ ቬልት ፤ ማለትም «ዓለም» በመባል የሚታወቀዉ ዕለታዊ የጀርመን ጋዜጣ በጎርጎረሳዉያኑ 1964 ዓ,ም ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት እንዳለቀ ጀምሮ የሚታተም ነዉ።

ጋዜጣዉ እድሜ ጠገብ እንደመሆኑም የአንባቢዉም ቁጥርም ጥቂት የሚባል አይደለም። ጋዜጣዉን፤ በድረ-ገፅም ማንበብ ይቻላል። ባለፈዉ ሰምን ጋዜጣዉ ስለኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያዉያን ያስነበበዉን ፅሁፍ ተመልክተዉ፤ ስለኢትዮጵያ ጥሩ መስማታቸዉን በማድነቅ አብዛኞች አስተያየታቸዉን ሲያሰፍሩ ሌሎች ደግሞ፤ በዓለማችን ሌላ ኢትዮጵያ ተፈጠረች እንዴ? ሲሉ አንዳንዶችም ታድያ አፍሪቃዉያኑ ለምን ወደ አዉሮጳ ይፈልሳሉ የሚል አስተያየታቸዉን በጥያቄ መልክ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ነዋሪዎች በአብዛኛዉ ወጣቶች ናቸዉ ይላል፤ ጀርመናዊትዋ ጋዜጠኛ አንድርያ ሃና ሁኒገር ፤ «አዉሮጳን እርሱ፤ ብሩህ የስራ እና የእድገት ተስፋ የሚታየዉ አዲስ አበባ ላይ ነዉ» ስትል በጀርመኑ ጋዜጣ ባስነበችዉ ጽሁፏ። በጀርመን የኑሮዉ ሁኔታ ምንም አዲስ ነገር የማይታይበት እንደዉ ድብርት የወረረዉ በመሆኑን ያስተዋለ፤ ተስፋ ወደፈነጠቀባት ወደ ምስራቅ አፍሪቃዊትዋ ሀገር መጓዝ ይችላል በማለት ያብራራል፤ የጋዜጠኛዋ ፅሁፍ ከመነሻዉ።

ወደ አፍሪቃ ለመሄድ የተነሳሁት ትላለች ጀርመናዊትዋ ጋዜጠኛ ሁኒገር በፅሁፏ፤ እዚህ በምኖርበት ጀርመን ምንም በህይወት የሚያነቃቃ ነገር ስላላየሁ፤ በአሁኑ ወቅትም የሚደመጠዉ ዜናም ቢሆን ነጋ ጠባ ስለ ጀርመን ምርጫ እና፤ በቀጣይ እየተደረገ ስላለዉ የመንግስት ምስረታ ድርድር፤ ወዲህም ለመግባት እየተንደረደረ ባለዉ የክረምት ወራት ሰበብ ዛፎች ቅጠላቸዉን እየጣሉ፤ አበቦች እየከሰሙ፤ ደመናማዉ እና ጭፍግግ ያለ ብርዳማ የአየር ፀባይ በመኖሩ፤ የብሩህ ተስፋ ዉጋገን ወደሚታይበት እንዲሄድ ገፋፋኝ ስትል ትገልፃለች። ጀርመናዊትዋ ጋዜጠኛ ፤ የአፍሪቃ ህብረት መቀመጫ ስትል የምትገልጻት አዲስ አበባ ከተማ፤ ከባህር ጠለል 2000 ሜትር በላይ ተቀምጣ ማለዳ በቀዝቃዛ አየር እና ጉም ተዉጣ፤ ከአድማስ ባሻገር አጋም የመሰለዉ ፀሃይ ብርሃን መታየት ሲጀምር እና፤ ገና የከተማዋ አየር በመኪና ጢስ ሳይደፈርስ፤ በየጎዳናዉ የሚታይ ነገር ቢኖር፤ ለሩጫ ዉድድር የሚዘጋጁ ስፖርተኞች ናቸዉ፤ በቀን በቀን የማራቶን ሩጫ ልምምድ። ከዝያም የማለዳዋ ፀሃይ ጨለማዉን ካስወገደችበት ሰዓት ጀምሮ፤ የከተማዋ ነዋሪም በየፈርጁ ሩጫን ይጀምራል ለኑሮ ። መኪናዉ በአንድ ወገን፤ ሌላዉ በሌላ ወገን ፤ ለፀሎት ወደ ቤተክርስትያን እና ወደ መስጂድ የሚሄደዉም እንዲሁ። ታድያ ይህን ሁሉ ያየ አዲስ አበባ የያዘችዉ ለማራቶን ዉድድር የሚለማመዱ ሯጮችን ብቻ ሳይሆን ፤ ኗሪዋም በየተሰማራበት ማራቶን ላይ መሆኑን ይረዳል ስትል በስዕላዊ አፃፃፍዋ አጣፍጣ አስቀምጣዋለች። ጀርመናዊትዋ ጋዜጠኛ አንድርያ ሃና ሁኒገር ወደ ኢትዮጵያ ለመሄድ እንዴት ተነሳስታ ይሆን ለዚህ ጽሁፍ የበቃችዉ ፤ እንዲህ ትገልጸዋለች።

« አንዲት ጀርመናዊት ጓደኛዪ ቤት ተከራይታ ለሁለት ዓመታት ኢትዮጵያ ዉስጥ በመኖርዋ ጥሩ የመኖርያ ቦታ ስላላት እና መምጣት እንደምችል ገልፃ ስለጋበዘችኝ ነበር ወደ ኢትዮጵያ የሄድኩት። ከዝያም ኢትዮጵያን እንዳየሁ ተስፋ የሚታይባት ወደፊት በመራመድ ላይ ያለች ሀገር መሆንዋ ታየኝ ። በብዙ የአዉሮጳ ሀገራት ያለዉ ህይወት በአሉበት ቦታ ላይ የመሮጥ አይነት ስሜትን ነዉ የሚያሳድረዉ፤ ግን ኢትዮጵያ ብዙ ሃይል እንዳላት ተሰማኝ፤ ነዋሪዎችዋም በጣም ጠንካራ ናቸዉ። ብቻ የሆነ ነገር ወደፊት ሲራመድ ይታይሻል፤ እናም ይህ ሁሉ ነገር ፤ እኔ ላይ በጣም ትልቅ ስሜት አሳደረብኝ »

አዲስ አበባ ታይላንድ ኤንባሲ አካባቢ ትኖር እንደ ነበር የምትናገረዉ ጋዜጠኛ ሁኒገር አንድ እሁድ ቀን ከጓደኛዋ ይኖሩበት በነበረዉ አካባቢ ኮረብታማ ስፍራ ላይ ቆማ፤ በአንድ በኩል፤ በከፍታ ከቤተክርስትያን የሚፈልቀዉን ቅዳሴና ደወል፤ በሌላ በኩል ከመስጂድ የሚሰማዉን የፀሎት ሥርዓት ደግሞም ይኖሩበት ከነበረዉ ቤት አጭር ርቀት ላይ ከሚገኘዉ ኤንባሲ በኩል የሚሰማዉን የሚዘምሩ የህጻናት ድምፅ እየተረከች፤ በመደነቅም ነዋሪዎችዋ በአብዛኛዉ በቀን ሶስት ግዜ ለፀሎት ቤተክርስትያን አልያም መስጅድ ፤ እንደምሄዱ በከተማዋ ህይወት መታየቱን ትገልፃለች። እሁድ እሁድ የአዲስ አበባን ድምቀት ፤ በአንፃሩ ጀርመን ሀገር የሱቆች መዘጋጋት፤ ጎዳናዉ ሁሉ ረጭ ማለቱን በማሰብ ከኢትዮጵያ ጋር ታነፃጽራለች፤ ጋዜጠኛ ሁኒገር ኢትዮጵያን ለመጀመርያ ግዜ እንዴት አገኘቻት?»

Flash-Galerie Der Blick aus meinem Fenster Addis Abeba Äthiopien

« ወደ ኢትዮጵያ የሄድኩት ባለፉትዓመታት ሁለት ግዜ ነዉ ። በዚህ ጉዞዪ ስድስት ስድስት ሳምንት ነዉ የቆየሁት። በመጀመርያዉ ጉዞዪ ለስድስት ሳምንት አዲስ አበባ ከተማ ነበርኩ። በሁለተኛዉ ጉዞዪ ደግሞ ደቡባዊዉን ኢትዮጵያን ፍሎች ጎብኝቻለሁ። ሃመሮች ጋር ነበርኩ አርባ ምንጭ ነበርኩ ። በጣም አስደሳች ግዜ አሳልፊ ነዉ የተመለስኩት ነበር። »

የኛ ኑሮ ትላለች ሁኒገር በመቀጠል ትረካዋን፤ በአዉሮጳ ማለቷ ነዉ ፤ ኑሮአችን ነጋ ጠባ የፍርሃት የጥንቃቄ የተሞላበት ፤ በአለንበት የምንራመድ የሚመስል ስሜት የሚሰጥ ነገር፤ በአንጻሩ በአፍሪቃ በጥሩ ስሜትን ተጎናፅፎ ፤ ወደፊት በመራመድ ላይ ያለች አይነት ስሜት ያላብሳል ባይናት ፤ ግን ጋዜጠኛ ሁኒገር ኢትዮጵያን እንዴት አግኘቻት ይሆን እንዲህ ትገልጻለች፤

« በዚች ሀገር የሰዓት አቆጣጠሩንም ሌላ ሆኖ ነዉ ያገኘሁት። ብዙ ስራ ነበረኝ ግን የዛኑ ያክል ደግሞ ግዜም ነበረኝ ። በጀርመን ከምኖረዉ አኗኗሬ በጣም የተለየ ሆኖ ነዉ ያገኘሁት። እዚህ ጀርመን ስኖር አንድም ቀን በቂ ግዜ ኖሮኝ አያዉቅም። ሁሌ ሩጫ፤ ሁሌ ሩጫ ። እንደዉም አንድ አይነት አባባል አለ፤ « እኛ ሰዓት መቁጠርያ አለን እነሱ ደግሞ ሰዓት አላቸዉ» ይህን ሁኔታ በርግጥም አፍሪቃ ዉስጥ ነዉ የሚሰራዉ። ግን እዚህ ላይ አፍሪቃ ብዪ ሁሉንም ሀገራት በአንድ አይነት ሁኔታ ማጠቃለል አልፈልግም። እርግጥ ነዉ ብዙ ችግሮች አሉ፤ እንድያም ሆኖ ግን፤ የአፍሪቃ ህብረት መቀመጫ በሆነችዉ አዲስ አበባ ህዝቡ ላይ የሚታየዉ ጥሩ ስሜት፤ በየቦታዉ የሚካሄደዉ ግንባታ፤ የነዋሪዋ የማያቋርጥ እንቅስቃሴ ፤ እዉነትም መጭዉ የተስፋ ህይወት ያለዉ እዚህ ነዉ የሚልን ስሜት ያሳድራል»

የኢትዮጵያን መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እና ያላት የአየር ፀባይ፤ እንደ ጉዞ መዳረሻ እውነትም ለየት ያለች አገር የምትላት ጋዜጠኛ ሁኒገር፤ በቆይታዋ በተለያየ የእድሜ ክልል የሚገኙ እና በልዩ ልዩ ስራ ላይ የተሰማሩ ኢትዮጵያዉያንንም በቅርቡ ተዋዉቃለች። ታድያ ኢትዮጵያዉያኑን እንዴት ትገልፃቸዉ ይሆን? ለሁኒገር ያቀረቡኩት ሌላዉ ጥያቄዪ ነበር።

« በጣም ሰላማዊ እና እንግዳ ተቀባይ ሆነዉ ነዉ ያገኘኋቸዉ ። ግን በእዉነቱ ምን

Äthiopien, Alltag, Bauer, Bäuerin

እንደምያስቡ ለይቼ ማወቅ፤ ለመረዳት አልቻልኩም። ከሰዎች ጋር በምገናኝበት ግዜ በእኩል በሆነ መንገድ ግን ተቀብለዊ ፤ እጅግ በጣም በክብር ሰተዉ አስተናግደዉኛል፤ የምፈልገዉን ነገር አሟልተዉልኛል»

ቀደም ባሉት ዓመታት የምዕራባዉያኑ የመገናኛ ብዙሃን በአብዛኛዉ ስለኢትዮጵያ ረሃብ፤ ድህነት ፤ እንዲሁም ዉስጣዊ የፖለቲካ ችግር፤ በተደጋጋሚ በመዘገቡ፤ በአብዛኛዉ የዉጭ ሀገር ዜጎች ስለኢትዮጵያ እንደሚያስቡት ሁሉ ፤ በምናቧ የምትስላት ሌላ ነዉ እና ታድያ ኢትዮጵያ እንደደረሽ ያየሽዉ ምን ነበር፤ አልኳት ጋዜጠኛ ሄኒገር ትቀጥላለች፤

« ልክ ነዉ እዚህ ስለኢትዮጵያ የምናወራዉ በእርግጥም ስለሚታየዉ የምግብ እጥረት እና ረሃብ ነዉ፤ እዚህ የምናወራዉ በእርግጥም በኢትዮጵያ ስለሚታየዉ አስቸጋሪ የፖለቲካ ሁኔታ ነዉ፤ የምናወራዉ ስለ ስደተኞች ጉዳይ ነዉ። ግን እነዚህ ከባድ ጥያቄዎች ልንፈታላቸዉ ልንረዳቸዉ ይገባናል። በሀገሪቱም ገና ብዙ መሰራት ያለበት ጉዳይ አለ። አዲስ አበባ እንደገባሁ ከፍተኛ ድህነት እንዳለ ነዉ የታየኝ ፤ የኢትዮጵያን ገጠራማ ክፍልን እየተዘዋወርኩ ባየሁም ግዜ፤ ጭንቅላቴ የሚጉላላዉ ጥያቄ፤ ነዋሪዎቹ ከሞላ ጎደል ከገንዘብ ይልቅ ከብቶች ነዉ ያልዋቸዉ እና የሀገሪቱን ዓመታዊ እድገት በሁለት እጥፍ ማደጉን የሚቀመረዉ እንዴት ነዉ? ይህን አይነቱን ሂሳብ ማንኛዉም ባንክ አያሰላዉም የሚለዉ ነበር ። እናም በአንድ በኩል ችግሩ አሁንም አለ ግን ፤ እኔ ስለ ኢትዮጵያ ጉዞዪ በጋዜጣ ላይ ባወጣሁት ዘገባ፤ ሁልግዜ ስለ ረሃብ እና ስለአለዉ ችግር ብቻ ማዉራት እንደሌለብን፤ ሀገሪትዋ በእድገት ጎዳና ልይ መሆንዋን እና ብዙ ነገር መሻሻሉን ማሳየት ፈልጌ ነዉ። ኢትዮጵያ ባለፉት 10 ዓመታት እጅግ ከፍተኛ መሻሻል አሳይታለች።»

Hilton Hotel Addis Abeba

ነዋሪነትዋን በጀርመን መዲና በርሊን ላይ ያደረገችዉ የ29 ዓመትዋ ጀርመናዊት ጋዜጠኛ እና ደራሲ አንድርያ ሃና ሁኒገር፤ ከኢትዮጵያ ከተመለሰች በኋላ ኢትዮጵያን በመናፈቅዋ ኢትዮጵያን በትዝታ ምናብዋ ዳግም ለመቅረብ፤ በበርሊን ከተማ ዉስጥ ያሉትን የኢትዮጵያ የባህል ምግቤቶች እንደምትጎበኝና፤ በእጅዋ እንጀራን ቆርሳ በመብላት፤ እንደምታጣጥም አጫዉታናለች። ጋዜጠኛ ሁኒገር በፈገግታ፤ እህ ህ አለች በመቀጠል፤ በበርሊን የሚገኙት የኢትዮጵያ ምግቤቶች፤ የሚያቀርቡት ወጥ እንደ ኢትዮጵያዉ በርበሬ ሞቅ ያለዉ ስላልሆነ፤ እንደገና ያንን ኮስተር ያለ በርበሬ ያለዉን ዶሮ ወጥና፤ ሚጥሚጣ ነስነስ ያለበትን ክትፎ ለማጣጣም፤ ብሎም ጥሩ የደስታ መንፈስን ዳግም ለመሙላት፤ ወደ ኢትዮጵያ እንደምትሄድ አጫዉታናለች፤ ይበል ብዪ እዚህ ላይ ቃለ-ምልልሱን ገትቼ ፤ በሚቀጥለዉ ስለ ኢትዮጵያ ለመፃፍ ብዕርዋን ልታነሳ ስትዘጋጅ እንድታሳዉቀኝ በመጠየቅ ተሰናበትኳት።

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች