ኢትዮጵያ ሳተላይት ለማምጠቅ ዝግጅቷን ጨርሳለች | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 04.12.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ኢትዮጵያ ሳተላይት ለማምጠቅ ዝግጅቷን ጨርሳለች

ኢትዮጵያ ለሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውን ሳተላይት በቻይና ሀገር ከሚገኝ የሳተላይት ማስወንጨፊያ ጣቢያ በታህሳስ ወር ለማምጠቅ አቅዳለች። ከህዋ ላይ ሆና መሬትን ለመመልከት የምታገለግለው ሳተላይት ግብርናን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ኢትዮጵያ የምትፈልጋቸውን መረጃዎችን ለመሰብሰብ እንደምትውል ተገልጿል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:48

ኢትዮጵያ ሳተላይት ለማምጠቅ ዝግጅቷን ጨርሳለች

የኢትዮጵያ የተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች በየዓመቱ ስራቸውን የሚጀምሩት በመስከረም ወር መጨረሻ በጋራ በሚያደርጉት ስብሰባ ነው። በዚሁ ስብሰባ የኢትዮጵያ መንግስት በዓመቱ ውስጥ ሊያከናውናቸው ያሰባቸውን አበይት ጉዳዮች ከሀገሪቱ ፕሬዝዳንት አፍ ያደምጣሉ። ባለፈው ዓመት የፕሬዝዳትነት መንበሩን የተረከቡት ሳህለወርቅ ዘውዴም የኢትዮጵያ መንግስት ዓመታዊ እቅድን መስከረም 26 ቀን 2012 በተካሄደው የሁለቱ ምክር ቤቶች ስብሰባ በዝርዝር አቅርበዋል። ፕሬዝዳንቷ በንግግራቸው ከጠቀሷቸው እና የመገናኛ ብዙሃንን ቀልብ ከሳቡ ጉዳዮች አንዱ ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ሳተላይቷን በዚህ ዓመት ለማምጠቅ የማቀዷ ነገር ነበር። 

“የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሳተላይት በያዝነው ዓመት በታኅሣሥ 2012 ዓ.ም. በቻይና ከሚገኝ የማምጠቂያ ማዕከል ወደ ጠፈር የሚላክ ሲሆን ይህ ሳተላይት ለግብርና፣ ለደን ልማትና ለአካባቢ ጥበቃ አገልግሎት የሚያስፈልጉትን የሳተላይት መረጃዎች ለመቀበል ይውላል” ብለው ነበር ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ በምክር ቤት መክፈቻ ንግግራቸው። 

በብዙዎች ዘንድ ሳተላይት ሲባል መጀመሪያ ፊታቸው መጥቶ ድቅን የሚለው ከአሜሪካው የጠፈር ምርምር ጣቢያ ናሳ ወይም ከተመሳሳይ ማስወንጨፊያ ጣቢያዎች ወደ ህዋ የሚመጥቁ ግዙፍ ሳተላይቶች ናቸው። “ኢትዮጵያ ሳተላይት ልታመጥቅ ነው” የሚለው ዜና ሲናኝም ብዙዎች የጠበቁት እንደዚያ አይነቱን ነው። ሆኖም በቅርቡ የወጡ መረጃዎች የኢትዮጵያ ሳተላይት 72 ኪሎ ግራም ብቻ የምትመዝንን እና “ማይክሮ ሳተላይት” ከሚባሉት የምትመደብ መሆኑን ይፋ አድርገዋል። 

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ሰለሞን በላይ የኢትዮጵያ የሳተላይት ማምጠቅ ፕሮጀክትን በበላይነት ያስተባብራሉ። ኢትዮጵያ የምታመጥቀው ሳተላይት “ማይክሮ” ከተሰኘው ምድብ ውስጥ የገባበትን ምክንያት ያስረዳሉ። “ሳተላይት ብዙ አይነት ምደባ አለው። አንደኛው ከአንድ ሺህ ኪሎ ግራም በላይ፣ ከ500 እስከ አንድ ሺህ፣ ከ10 እስከ 500 ኪሎ ግራም ያላቸው ናቸው። ስለዚህ እኛም ስም ነው። አጠቃላይ ትንሽ ሳተላይት ሲፈለግ ከ10 እስከ 500 ኪሎ ግራም ነው። ሳተላይት  ቲኮ፣ ማይክሮ፣ ፌኖ እየተባለ ይመደባልና ማይክሮ ሳተላይት የሚባሉት ከ10 እስከ 500 ኪሎ ግራም ያላቸው ስለሆኑ ነው ስሙ እንደዚያ የሆነው” ይላሉ ዋና ዳይሬክተሩ። 

ኢትዮጵያ ወደ ህዋ የምታመጥቀው ሳተላይት ለመሬት ምልከታ የምታገልግል እንደሆነ ተገልጿል። “ETRSS-1” የሚል ስያሜ የተሰጣት ሳተላይት በዋነኛነት ለግብርና፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ ምልከታ እና ለማዕድን ዘርፎች ጥቅም ላይ ትውላለች ተብሏል። ሳተላይቷ በየዘርፎቹ ምን ዓይነት ጠቀሜታዎች ልታበረክት እንደምትችል ዶ/ር ሰለሞን እንዲህ ያብራራሉ።

“እንግዲህ አንድ ሳተላይት ሲገነባ ዓላማ አለው። ይሄን ይሄን ይሰራል ተብሎ ነው። ስለዚህ እኛም ሳተላይቱን ስንገባ የአካባቢ ጥበቃ ጥናት ታካሂዳለች። ደኑንም ይሁን ሁሉንም መረጃውን ታመጣለች። ሁለተኛ በግብርና ዘርፍ ለግብርና ምርምር፣ ለግብርና ለመዘመም፣ በቆሎ ያለበትን፣ ስንዴ ያለበትን፤ ስንዴን ለመዘም የመስኖ ሁኔታ፣ የውሃ ሁኔታ፣ የእዚያን ሁሉ ጥናት ያስፈልጋል። ያ ደግሞ ትክክለኛ ጥናት የሚጠናው በሳተላይት መረጃ ላይ በማስደገፍ ነው። 

ሌላኛው ማዕድን ልማትን ይመለከታል። የማዕድን ልማት ጥናት የሚካሄደው እየተሞከረ፣ እየተቆፈረ ነው። ሳተላይት ሲኖረን ግን የማዕድን ልማትን በሳተላይት መረጃ አስደግፎ፣ አጥንቶ፣ የአፈሩንም የሌላውንም እንዲህ አይነት አለ ብሎ ለኢንቬስተር ሙሉ ዝግጅት ማድረግ ይቻላልና ሰፊ ጠቀሜታ ነው ያለው። ሌላው የከተማ እና የገጠር መሬት አስተዳደር ስርዓታችን እያንዳንዱን ፎቶግራፍ አንስቶ ስርዓቱን ለመከታተል እና ለመቆጣጠር ትልቅ የሆነ ጠቀሜታ ስላለው ይሄ ነው። እና ሌሎችም ተዛማጅ ስራዎች ይሰራል” ሲሉ ዶ/ር ሰለሞን የሳተላይቱን ዓላማ ዘርዝረዋል።

ኢትዮጵያ እነዚህን መሰል የሳተላይት መረጃዎች እስካሁን የምታገኘው ይህን አገልግሎት ከሚሰጡ የውጭ ሀገር ድርጅቶች በግዢ ነው። የኢትዮጵያ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በቅርቡ ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው ሀገሪቱ ለሳተላይት ምስሎች ግዢ ብቻ ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ በየዓመቱ ታወጣለች። ዶ/ር ሰለሞን ግን ሀገሪቱ ለሳተላይት መረጃ የምታወጣው ወጪ “ከዚህም የላቀ ነው” ይላሉ። ኢትዮጵያ ሳተላይት ለመገንባት እና ለማምጠቅ ያወጣችውን ወጪ በየዓመቱ ለሳተላይት መረጃዎች ከምታወጣው ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ መሆኑንም ይጠቁማሉ። 

“እንግዲህ የሳተላይት ዓይነት፣ ትላልቅ ሲሆኑ፣ የሚቆዩባቸው ዕድሜ፣ የምንጠቀማቸው መሳሪያዎች እየጨመረ በሄደ ቁጥር ዋጋቸውም እንደዚያ ነው። የሙከራ (experimental) አይደለማ ይሄ፤ ምርምር የምትካሄድበት ሳተላይት ነው። የወጪው መጠን እንደየሳተላይቱ አይነት ነው። ወደዚህ ስንመጣ ደግሞ እንበል እና የሳተላይቱ ዋጋ እና መረጃ በፍጹም አይገናኝም። አንደኛ ቴክኖሎጂውን ራሱ ለሰው ለማሰልጠን፣ ቴክኖሎጂውን ማስተዋወቅ አንደኛው የማይገኝለት ሀብት ነው። ሁለተኛው ደግሞ መረጃው ነው። ሶስተኛው ደግሞ ህዋ (space) ላይ ያለ ሀብት ላይ መግባት ራሱ፣ ምህዋር (orbit) ላይ ማስቀመጥ፣ ይሄም ምህዋር ላይ ነው የሚደረገው እነዚህ ሁሉ ተደምረው ዋጋም ቢሆን ከዚያ በታች እንጂ ከዚያ በላይ አይደለም። ያው እስካሁን ድረስ ሁሉኑም ማምጠቂያውን ጨምሮ ስድስት ሚሊዮን ዶላር ነው” ይላሉ ዶ/ር ሰለሞን።

ኢትዮጵያ የመሬት ምልከታ ሳተላይቷን ወደ ህዋ የምታመጥቀው ከቻይና መዲና ቤይጂንግ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው የማስወንጨፊያ ጣቢያ እንደሆነ ተነግሯል። ሳተላይቷ ከቻይና ብትመጥቅም ሳተላይቱን የመቆጣጠሪያ ጣቢያ ግን አዲስ አበባ ጫፍ እንጥጦ በሚገኘው የስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ቅጽር ግቢ ተገንብቶ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ በመስከረም መጨረሻ የምክር ቤት ንግግራቸው አንስተው ነበር። የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሰለሞን የመቆጣጠሪያ ጣቢያው ግንባታ አሁን መጠናቀቁን እና ወደ 20 የሚጠጉ ባለሙያዎች ለስራው ስልጠና ወስደው ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

“አንድ ሳተላይት እንድትመጥቅ ከተደረገች በኋላ ዋናው ነገር መሬት ላይ መቆጣጠር፣ ትዕዛዝ መስጠት፣ መረጃ እንዲደርስ ማድረግ ነው አይደል?  ስለዚህ ይህን ማድረጊያ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ያለው። እውነት ነው። ይሄም እንጦጦ ኦብዘርቫቶሪ እና የምርምር ማዕከል ነው። ሙከራ እያደረግን ነው። እንጦጦ ኦብዘርቫቶሪ እና የምርምር ማዕከል ማለት ሁለቱንም እንዲያካትት ሲባል ስሙን astronomical observatory አላልነውም። ኦብዘርቫቶሪ የሚለው ስሙ ከመሬት ወደ ሰማይም መመልከት ያስችላል፤ ከሰማይ ወደ መሬትም መመልከት ያስችላል። ስለዚህ ችግር የለውም ሁለቱንም ያጠቃልላል። ብዙ ዲፓርትመንቶች ያሉት ማዕከል ስለሆነ በስሩ በርካታ አገልግሎቶች አሉት። ዋናው ነገር ግን ይሄ ዋናው ማዕከሉ እዚያ ነው። መቆጣጠሪያው፣ መረጃው የሚገኝበት እዚያ ስለሆነ ለዚያ ነው።”

የሳተላይት ቴክኖሎጂ ለቴሌኮሙኒኬሽን ፣ የመሬት እና የህዋ ምልከታ፣ ለከተማ ልማት፣ ዓለማቀፍ የተፈጥሮ ሃብትን ለመቆጣጠር፣ አደጋን ለመከላከል፣ ለካርታ ስራ፣ ለግብርና፣ ለደን ልማት፣ ለሜትሮሎጂ እና ጂፒኤስ እንደሚውል የኢትዮጵያ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ያወጣው መረጃ ያሳያል። ዶ/ር ሰለሞን ኢትዮጵያ በሳተላይት ግንባታ እና ማምጠቅ ላይ ባለሙያዎቿን ማሳተፏ እና በቀጥታ መካፈሏ ምን አንደምታ እንዳለው ይተነትናሉ።  

የዶ/ር ሰለሞን በላይን ትንታኔ እና ሙሉ ዝግጅቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ተስፋለም ወልደየስ

ኂሩት መለሰ


 

Audios and videos on the topic