ኢትዮጵያ ሦስት የሐዘን ቀናት ልታውጅ ነው | ኢትዮጵያ | DW | 20.04.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ ሦስት የሐዘን ቀናት ልታውጅ ነው

በሊቢያ የአይሲስ ታጣቂ ቡድን የተገደሉት 30 ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን የኢትዮጵያ መንግስት ማረጋገጡን አስታወቀ። ግድያው በኢትዮጵያውያን ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል። የአውሮጳ ህብረት፤የአፍሪቃ ህብረትና ዩ.ኤስ አሜሪካ የታጣቂ ቡድኑን ድርጊት በጽኑ ኮንነዋል።

ሰኞ ሚያዝያ 11 ቀን2007 ዓ.ም ራሱን ‘እስላማዊ መንግስት’ብሎ የሚጠራው አክራሪ ቡድን በማህበራዊ ድረ-ገጾች የበተነው ቪዲዮ የ30 ኢትዮጵያውያንን መርዶ ለዓለም አብስሯል። በምስሉ ላይ ስደተኞቹ «ጠላት የሆነችው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መስቀል ተከታዮች» የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል። ፊታቸውን በጭምብል የሸፈኑት እና ሙሉ ወታደራዊ ትጥቅ የታጠቁት የአክራሪው ቡድን ወታደሮች ስደተኛ ኢትዮጵያውያኑን በሁለት ምድብ ከፍለው ወደ ሞታቸው ሲነዷቸው ታይቷል።የ29 ደቂቃ እርዝማኔ ያለው የቪዲዮ ምስል ብርቱካናማ ቱታ የለበሱ 15 ስደተኞች በምስራቃዊ ሊቢያ የባህር ዳርቻ አንገታቸው በካራ ተቀልቶ ሲገደሉ ጥቁር ቱታ የለበሱ ሌሎች 15 ስደተኞች ደግሞ በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል በጥይት ተደብድበው መገደላቸውን እንደሚያሳይ የመገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በታጣቂ ቡድኑ የተገደሉት 30 ስደተኞች ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን አረጋግጦ ማንነታቸውን ለማጣራት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግስት ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት አስታውቋል። ከነገ ሚያዝያ 13 ቀን2007 ዓ.ም. ጀምሮ ሶስት ብሄራዊ የሃዘን ቀናት በመላው ኢትዮጵያ እንደሚታወጅ የአገሪቱ ሰንደቅ አላም በግማሽ ዝቅ ብሎ እንደሚውለበለብ የኢትዮጵያ መንግስት አስታውቋል።

የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ተጠቃሚ ኢትዮጵያውያን የታጣቂ ቡድኑን እርምጃ በማውገዝ የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል። የአፍሪቃ ህብረት ኮሚሽነር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ ድርጊቱን አውግዘው 54 አባል አገራት ያሉት አህጉራዊው ድርጅት በሊቢያ ጠንካራ መንግስታዊ ተቋማት እንደገና የሚዋቀሩበትንና የአገሪቱ ደህንነት የሚረጋገጥበትን መላ ለመዘየድ ጥረት ያደርጋል ብለዋል።

ራሱን እስላማዊ መንግስት ብሎ የሚጠራው ተቃዋሚ ቡድን በመገናኛ ብዙሃን የለቀቀው የቪዲዮ ምስል ካሁን ቀደም 21 የክርስትና እምነት ተከታይ ግብጻውያን ላይ የወሰደውን እርምጃ በድጋሚ እንደሚያሳይ ሬውተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል። የክርስትናና እስልምና እምነት ተከታዮች ታሪክ በመተረክ የሚጀምረው ይህ ምስል ታጣቂዎቹ አብያተክርስቲያናት፣የእምነት ምልክቶችና የመቃብር ቦታዎች ሲያፈራርሱም አሳይቷል።

ዩ.ኤስ. አሜሪካ ግድያውን ‘አሰቃቂ የጅምላ ጭፍጨፋ’በማለት ስታወግዝ የአውሮጳ ህብረት በበኩሉ ሐይማኖታዊ ልዩነት ለመፍጠር የተፈጸመ ወንጀል ሲል ተቃውሞታል።

እሸቴ በቀለ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic