1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ምን ያህል ምቹ ናት?

ፀሀይ ጫኔ
ረቡዕ፣ ግንቦት 21 2016

የቤት አውቶሞቢል የኤለክትሪክ ካልሆነ ወደ ሀገር እንዳይገባ የኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔ ካሳለፈ ወራት ተቆጥረዋል። ያም ሆኖ የመኪናዎቹ ውድ መሆን፣ የኤለክትሪክ አቅርቦት ፣ የባትሪ መሙያ ጣቢያዎች ፣ የመለዋወጫ እና የጥገና ማዕከላት እጥረት ተግዳሮቶች መሆናቸው ይነገራል።

https://p.dw.com/p/4gQn0
የኤለክትሪክ መኪና ባትሪ በመሙላት ላይ
የኤለክትሪክ መኪና ባትሪ በመሙላት ላይምስል Torsten Sukrow/SULUPRESS.DE/picture alliance

ኢትዮጵያ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ምን ያህል ምቹ ናት?


የኢትዮጵያ መንግሥት በነዳጅ የሚሠሩ የቤት አውቶሞቢሎች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ ከወሰነ ከግማሽ ዓመት በላይ ሆኖታል። መንግስት በምትኩ በኤለክትሪክ የሚሰሩ የቤት መኪናዎችን ከውጭ ማስመጣትን ወይም በሀገር ውስጥ መገጣጠምን ያበረታታል።የውሳኔው መነሻ የአየር  ብክለትን እና የነዳጅ ወጭን ለመቆጠብ መሆኑን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ዶክተር ዓለሙ ስሜ በወቅቱ ገልፀው  ነበር።ኢትዮጵያ በነዳጅ የሚሠሩ መኪኖችን በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ለመተካት ዝግጁ ነች?
ሚኪ አወቀ በሚል ስም በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ተሽከርካሪዎችን በተመለከተ መረጃ በመስጠት የሚታወቀው፤ የአውቶሞቲቭ ባለሙያው እና የትራንስፖርት አማካሪው አቶ ብሩክ አወቀ የመንግስትን የውሳኔ መነሻ ይጋራል።

ያም ሆኖ ብሩክ  በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ምቹ ሁኔታ አለ ብሎ አፉን ሞልቶ አይናገርም።ምክንያቱም መንግስት ህብረተሰቡ የኤለክትሪክ ተሽከርካሪዎችን እንዲጠቀም በሚያበረታታው ልክ ለዚህ የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶችን ቀድሞ በማሟላት ረገድ የተሰራ ስራ የለም ባይ ነው።እስካሁን ባለው ሁኔታ የኤለክትሪክ ተሽከርካሪዎችን  ሀይል መሙላት / ቻርጅ ማድረግ/ የሚቻለው በመኖሪያ ቤቶች ብቻ ሲሆን፤ይህም በኤለክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሂድ  የሀይል እጥረት ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት አለው።

ብሩክ አወቀ፤ የአውቶሞቲቭ ባለሙያ እና የትንስፖርት አማካሪ
ብሩክ አወቀ፤ የአውቶሞቲቭ ባለሙያ እና የትንስፖርት አማካሪምስል Privat

በመኖሪያ ቤት ባትሪ ለሙሙላትም ቢሆን፤ በተለይ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ለሚኖሩ ተጠቃሚዎች  ምቹ አለመሆኑ ሌላው ፈተና መሆኑን ገልጿል።

በዓለም ላይ የኤሌትሪክ ተሽከርካሪዎች ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ሲሆን፤በቅርቡ የተደረገ የሸማቾች  ዳሰሳ ጥናት እንዳመለከተው ከአንድ ሶስተኛ በላይ የሚሆኑት አሜሪካውያን አዲስ መኪና ለመግዛት ከፈለጉ በእርግጠኝነት የሚያስቡት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ለመግዛት ነው። የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መግዛት ከሚፈልጉ ሰዎች መካከል 77 በመቶ የሚሆኑት የነዳጅ ወጭ መቆጠብን እንደ ዋና ምክንያት ይጠቅሳሉ። ነገር ግን ባትሪ ለመሙላት  በቂ ቦታ ከማግኘት ጋር ተያይዞ  60 በመቶ የሚሆኑት  የኤለክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለመግዛት ያመነታሉ።

በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ መኪና የሚያሽከረክሩ ሰዎች ደግሞ የሀይል መሙያ ቦታዎች እጥረት ብቻ ሳይሆን፤ በቂ የኤለክትሪክ ሀይል ፣ የጥገና ማዕከላት እና የመለዋወጫ ዕቃዎች አለመኖርም  ተጨማሪ ችግሮቻቸው ናቸው።
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ አብዛኞቹ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሚጠቀሙት ሊቲየም የሚባለውን ባትሪ ሲሆን፤ እንደ ብሩክ ገለፃ ይህ ባትሪ የሚሰጠው ዋስትና ደግሞ፣ እስከ 10 ዓመት ድረስ ነው።ነገር ግን ዋስትናውን በተመለከተ ሀገር ውስጥ ወኪል ባለመኖሩ ችግር ሲያግጥም ዋስትናውን ለመጠቀም አስቸጋሪ መሆኑም ተጨማሪ ተግዳሮት ነው።

​​​​​​የኤለክትሪክ መኪና ባትሪ በመሙላት ላይ
​​​​የኤለክትሪክ መኪና ባትሪ በመሙላት ላይምስል Action Pictures/imago images

እንደ ዓለም አቀፉ ኢነርጂ ኤጀንሲ የኤሌትሪክ ተሽከርካሪዎች በጎርጎሪያኑ 2023  ዓ/ም ከአጠቃላይ የመኪና ገበያ አንድ አምስተኛውን ይይዛል። በጎርጎሪያኑ 2022 ዓ/ም በዓለም ላይ ከ10 ሚሊዮን በላይ የኤሌክትሪክ መኪኖች የተሸጡ ሲሆን ይህ አሃዝ በ2023 መገባደጃ  14 በመቶ አድጓል።በተያዘው የጎርጎሪያኑ 2024 ዓ/ም ሽያጩ 17 ሚሊዮን እንደሚጠጋ መረጃው ያሳያል።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወረት እንዳያልፍባቸው ለማድረግ እና  ከነዳጅ ይልቅ በኤለክትሪክ የመጠቀም ሀሳብ የበለጠ ምቹ እንዲሆን ዋጋቸውን የበለጠ ተመጣጣኝ የማድረግ አዝማሚያዎች አሉ። በትራንስፖርት ዘርፍ የ10 ዓመት ዕቅድ ውስጥ ለታዳሽ ኃይል ቅድሚያ የሰጠው የኢትዮጵያ መንግስትም፤ የኤክትሪክ መኪና ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የሚጣለውን ግብር ዝቅ አድርጓል። ያም ሆኖ አሁን ባለው ገበያ አንድ አነስተኛ የኤለክትሪክ መኪና ለመግዛት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ብሮችን ማውጣት ይጠይቃል። ይህም ለአብዛኛው ህብረተሰብ የሚቻል አይደለም።
በሌላ በኩል መንግሥት ያሳለፈውን ውሳኔ አፈፃጸም በተመለከተ  እስካሁን መመሪያ ይፋ ባለማድረጉ ወደ ሀገር ለሚገቡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ግልጽ የሆነ የባትሪ መስፈረት አለመኖርም ሌላው ችግር  ነው።"የእርጅና ቅናሽ" ሲቀር የመኪና ዋጋ ጨመረ
ብሩክ እንደሚገልፀው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እንደ ባትሪ መጠናቸው የሚጓዙት ርቀት ይለያያል።እንደ ቮልስ ቫገን እና ቶዮታ ያሉ የኤለክትሪክ ተሽከርካሪዎች አንዴ በተሞላ ባትሪ እስከ ከ500 እስከ 600 የሚደርስ ኪሎሜትር ሊጓዙ ይችላሉ። አነስተኛ በሚባሉት የኤለክትሪክ ተሽከርካሪዎች ደግሞ ከ300 እስከ 400 ኪሜ ይጓዛሉ።ከዚህ አንፃር ከተማ ውስጥ ለሚንቀሳቀስ አንድ አሽከርካሪ ባትሪው በአማካኝ  እስከ ሶስት ቀን ሊያቆየው እንደሚችል ያስረዳል። ነገር ግን በአሽከርካሪዎቹ  ዘንድ መደረግ ያለባቸው ጥንቃቄዎች አሉ። 

እንደ ዓለም አቀፉ ኢነርጂ ኤጀንሲ የኤሌትሪክ ተሽከርካሪዎች በጎርጎሪያኑ 2023  ዓ/ም ከአጠቃላይ የመኪና ገበያ አንድ አምስተኛውን ይይዛል። በጎርጎሪያኑ 2022 ዓ/ም በዓለም ላይ ከ10 ሚሊዮን በላይ የኤሌክትሪክ መኪኖች የተሸጡ ሲሆን በተያዘው የጎርጎሪያኑ 2024 ዓ/ም ሽያጩ 17 ሚሊዮን እንደሚጠጋ መረጃው ያሳያል።
እንደ ዓለም አቀፉ ኢነርጂ ኤጀንሲ የኤሌትሪክ ተሽከርካሪዎች በጎርጎሪያኑ 2023  ዓ/ም ከአጠቃላይ የመኪና ገበያ አንድ አምስተኛውን ይይዛል። በጎርጎሪያኑ 2022 ዓ/ም በዓለም ላይ ከ10 ሚሊዮን በላይ የኤሌክትሪክ መኪኖች የተሸጡ ሲሆን በተያዘው የጎርጎሪያኑ 2024 ዓ/ም ሽያጩ 17 ሚሊዮን እንደሚጠጋ መረጃው ያሳያል።ምስል Dylan Stewart/Image of Sport/ Newscom/picture alliance

ብሩክ እንደሚለው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ባለ8፣16 እና በ32 አምፔር የኃይል መሙያ ያላቸው ሲሆን፤ 8 አምፔር የኃይል መሙያ ያለው ተሽከርካሪ ቤት ውስጥ በሚገኝ መደበኛ  7 ኪሎዋት የኤለክትሪክ አቅም፤ ባትሪ ለመሙላት ከ12 ስዓት በላይ ፤32 አምፔር ላለው ተሽከርካሪ ደግሞ  እስከ 8 ሰዓት ሊፈጅ ይችላል።ይህም ቤት ውስጥ በኤለክትሪክ የሚሰሩ ስራዎችን በሙሉ ያስተጓጉላል።ከዚህ አኳያ በሀገሪቱ ፈጣን የባትሪ መሙያዎችን ተደራሽ ማድረግም ሌላው ወሳኝ ነገር ነው።ከዚህ ባሻገር በነዳጅ እና ኤለክትሪክ የሚሰሩ «ሃይብሪድ» የሚባሉትን ተሽከርካሪዎች መጠቀም ሌላው መፍትሄ መሆኑን ብሩክ ይገልፃል።መንግሥት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መኪኖችን ዕድሜ ሊገድብ ነው

ከዓለም አቀፉ የካርቦን ልቀት 0.3 ድርሻ ያላት ኢትዮጵያ፤ ወደ 40 በመቶ የሚሆነው የአየር ብክለት በነዳጅ ከሚሰሩ በ1.2 ሚሊዮን ተሽከርካሪዎቿ የሚመጣ ነው። ስለሆነም የአካባቢ ብክለትን ለመከላለክል እና ከውሃ ሀይል  የሚገኝን ርካሽ የኤለክትሪክ ሀይል በመጠቀም በውጭ ምንዛሬ የሚገባ የነዳጅ ወጭን ለማስቀረት የኤለክትሪክ መኪና በኢትዮጵያ ጠቃሚ ነው። ነገር ግን ለእነዚህ ተሽከርካሪዎች የሚሆኑ ግብዓቶችን እና የባትሪ መሙያ ቦታዎችን ማመቻቸትን የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶችን ማሟላት እጅግ አስፈላጊ እና ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን ባለሙያው አመልክቷል።ዋስትና የሚሰጡ ወኪሎች በሀገር ውስጥ እንዲኖሩ አስገዳጅ መመሪያ ማውጣትም በመንግስት በኩል ሌላው መሰራት ያለበት ስራ ነው።
የኤሌክትሪክ መኪናዎች አይነት በገበያ ላይ እየጨመረ ሲሆን፤ ቴስላ ግንባር ቀደም ከሆኑት የኤለክትሪክ መኪናዎች ውስጥ አንዱ ነው። ከቴስላ በተጨማሪ ሌሎች የመኪና አምራቾችም  በየአመቱ አዳዲስ የኤሌክትሪክ መኪና አማራጮችን ወደ ገበያው እያስገቡ ነው።
በጎርጎሪያኑ እስከ 2025  ደግሞ እንደ አልፋ ሮሚዮ ፣ ቤንትሌይ እና አፕል /የቴክኖሎጂ ኩባንያው/ ያሉ አዳዲስ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ዝርዝር ገበያ ላይ እንደሚውል ይጠበቃል።
አብዛኛው የኤለክትሪክ መኪናዎች ሽያጭ በቻይና፣ አውሮፓ እና ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ገበያዎች ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ ቻይና በዓለም አቀፍ ደረጃ  በሽያጭ 60 በመቶውን በመያዝ በቀዳሚነት ትመራለች።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ
እሸቴ በቀለ