ኢትዮጵያ ለምን ለከፋው የኮሮና ወረርሽኝ ትዘጋጅ? | ኢትዮጵያ | DW | 21.03.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ ለምን ለከፋው የኮሮና ወረርሽኝ ትዘጋጅ?

"የቫይረሱ ዕድገት እየተራባ የሚሔድ (exponential growth) ነው። ለምሳሌ እንበልና  50 ሰው መጀመሪያ ላይ ቢያዝ ከ15 ቀን በኋላ 2000 ሰው ይኖረናል። ቀጥሎ ደግሞ በአንድ ወር ውስጥ ወደ 91 ሺሕ አካባቢ ሰዎች ሊያዙ ይችላሉ" በዲላ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጤና ትምህርት ቤት ኃላፊ አቶ ትዝአለኝ ተስፋዬ

በኮሮና ወረርሽኝ ረገድ ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም እና አቶ ትዝአለኝ ተስፋዬ በአንድ ነገር ይስማማሉ። በሁለቱም እምነት ኢትዮጵያ እና አፍሪካ ለከፋው ቀውስ መዘጋጀት አለባቸው። ጄኔቫ እና ዲላ ሆነው እንደ ሰደድ እሳት የሚንቀለቀለውን ወረርሽኝ ለመግታት በየፊናቸው የሚታትሩት ዶክተር ቴድሮስ እና አቶ ትዝአለኝ የኢትዮጵያን የጤና ሥርዓት አቅም ጠንቅቀው ያውቃሉ። ከዚያ ባሻገር ተሕዋሲው ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍበት መንገድ እንደ ኢትዮጵያ የቀረበ ማህበራዊ መስተጋብር ላለው አገር ፈታኝ መሆኑ ባለሙያዎቹን ሥጋት ላይ የጣለ ጉዳይ ነው። ጉዳዩ ያሳሰባቸው የዓለም ጤና  ድርጅት ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም «አፍሪካ ሆይ ንቂ፤ የእኔ አህጉር ንቂ» የሚል ጥሪ እስከ ማቅረብ ደርሰዋል።

በዲላ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጤና ትምህርት ቤት ኃላፊ አቶ ትዝአለኝ ተስፋዬ ኢትዮጵያ ለከፋው ልትዘጋጅ ይገባት ሲሉ ይሞግታሉ። «ነገ ምን ሊከሰት እንደሚችል አናውቅም። ወረርሽኝ በባህሪው ነገ ምን ሊከሰት ይችላል የሚለውን እንኳን አይደለም እኛ በዓለም ያሉ ባለሙያዎች ተሰብስበው መተንበይ አይችሉም። የሚያዋጣን [ሊከሰት የሚችለውን] መጥፎ ሁኔታ መተንበይ ነው። ነገ የከፋው ይመጣል ብሎ መዘጋጀት ያስፈልጋል" ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

ከሰሐራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገራት በኮሮና ተሕዋሲ መያዛቸው በምርመራ የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም በአንዳች ወቅት በከፍተኛ ፍጥነት ሊጨምር እንደሚችል ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም አስጠንቅቀዋል። "ያልተመረመሩ አሊያም ሪፖርት ያልተደረጉ ሊኖሩ ይችላሉ" ያሉት ዶክተር ቴድሮስ «በሌሎች አገሮች የቫይረሱ ሥርጭት ከሆነ ጊዜ በኋላ በከፍተኛ ፍጥነት ሲጨምር ተመልክተናል። ስለዚህ አፍሪካ ለከፋው መዘጋጀት አለባት። ዝግጅቱ ዛሬ ሊጀመር ይገባል» የሚል ምክር ለግሰዋል።

ኮሮና ኢትዮጵያን ለምን በተለየ ያሰጋል?

Bildergalerie Corona Tschechien Grenzkontollen

በአሜሪካ እና አውሮፓ ጥብቅ ክትትል እየተደረገ ነው

በኢትዮጵያ የጤና ሚኒስቴር መረጃ መሠረት ከመጋቢት 3 እስከ መጋቢት 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ባሉት ሰባት ቀናት በኮሮና ተሕዋሲ መያዛቸው የተረጋገጠ ዘጠኝ ሰዎች ይገኛሉ። አራት ጃፓናውያን፣ ሶስት ኢትዮጵያውያን፣ አንድ ብሪታኒያዊት እና አንድ አውስትራሊያዊ ናቸው። በተሕዋሲው በምርመራ ከተረጋገጠ ዘጠኝ ሰዎች ግንኙነት ያላቸው ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት ገልጿል።

አቶ ትዝአለኝ ኢትዮጵያ በቅጡ ካልተዘጋጀት ይኸ ቁጥር በአሳሳቢ ደረጃ ሊጨምር እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ። "የቫይረሱ ዕድገት እየተራባ የሚሔድ (exponential growth) ነው። ለምሳሌ እንበልና  50 ሰው መጀመሪያ ላይ ቢያዝ ከ15 ቀን በኋላ 2000 ሰው ይኖረናል። ቀጥሎ ደግሞ በአንድ ወር ውስጥ ወደ 91 ሺሕ አካባቢ ሰዎች ሊያዙ ይችላሉ" ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ዓለምን ያመሰው ይኸን ወረርሽኝ እንዳይስፋፋ ለማገድ ያስፈልጋሉ ያላቸውን እርምጃዎች ወስዷል። የአዲስ አበባ "መሸታ ቤቶች" እና ጭፈራ ቤቶች ከዛሬ ጀምሮ መዘጋታቸውን ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ 30 አገራት የሚያደርገውን በረራ መሠረዙን ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናግረዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ ተለይተዋል ካሏቸው 30 አገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚያቀኑ መንገደኞች በለይቶ ማቆያ ለአስራ አራት ቀናት እንዲቆዩ ይደረጋል። ኢትዮጵያ ከዩኒቨርሲቲዎች በቀር ትምህርት ቤቶቿን ዘግታለች። የስፖርት ውድድሮችም አይካሔዱም።በማረሚያ ቤቶች የእስረኞች ጉብኝት ተከልክሏል። ይኸ የእስረኞችን ቤተሰቦች፤ የሐይማኖት መሪዎች እና ጠበቆቻቸውን ይጨምራል።

የኢትዮጵያ የጤና ሥርዓት የከፋውን መቋቋም ይችላል?

ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም እንዳሉት ግን የሰው ለሰው ግንኙነትን በመቀነስ የኮሮና ወረርሽኝን ለመግታት የሚደረገው ጥረት በቂ አይደለም። በምርመራ፣ ተሕዋሲው የተገኘባቸውን ሰዎች በመነጠል እና የተገናኟቸውን አፈላልጎ በማግኘት ረገድ የሚሰራው ሥራ በአፋጣኝ ማደግ አለበት።

በዲላ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጤና ትምህርት ቤት ኃላፊ አቶ ትዝአለኝ ተስፋዬ "የኮሮና በሽታ በጣም አደገኛ የሆነበት ዋንኛ ምክንያት መተላለፊያ መንገዱ ቀላል ነው። በተለይ ደግሞ ማኅበረሰባዊ መሥተጋብራችን ቅርብ ለሆነ እጅግ በጣም በቀላሉ መተላለፍ የሚችል በሽታ ነው። እኛ እርስ በርስ በጣም ቅርብ ነን" ሲሉ ይናገራሉ።

ኮሮና የቻይና፣ የጣልያን፣ የፈረንሳይ፣ የኢራን የጤና ሥርዓቶችን ክፉኛ ፈትኗል። በጀርመኑ ሐይድልበርግ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ሳይንቲስት የሆኑት ዶክተር ዘገዬ ኃይሉ «የኮሮና በሽታ 2019 ( #COVID19) ዘመናዊ ሕክምና ላላቸው አገራት ከፍተኛ ጭንቀት ሆኗል። አሁን ባለው ሁኔታ ስናየው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ቀጥሎ ከፍተኛ ማኅበራዊ ሥጋት በሁሉም አቅጣጫ የፈጠረ ሆኖ ነው የተገኘው" ሲሉ የተፈጠረውን ቀውስ ያስረዳሉ።

"በተሕዋሲው ከተያዙ ሰዎች 20 በመቶው ለህክምና ወደ ሆስፒታል ስለሚያመሩ እና በሽታው አሁን ያለው የመተላለፍ ባሕሪ እና ያለው የሆስፒታሎች አቅም አለመመጣጠን ይኸን ክስተት በጣም አስጊ እንዲሆን አድርጎታል። ሁለተኛው ለዚህ በሽታ መድሐኒት አለመኖሩ ነገርየው እንዲባባስ አድርጎታል» ሲሉ ዶክተር ዘገዬ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

ታዲያ ኢትዮጵያ በሐብት፤ በእውቀት እና በሰለጠነ የሰው ኃይል  የደረጀ የጤና ሥርዓት ያላቸውን አገሮች ክፉኛ የፈተነ ወረርሽኝ ቢከፋባት ምን ያክል መቋቋም ትችላለች? በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህር እና በጥቁር አንበሳ  ሆስፒታል የሕክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ሲሳይ ለማ «አሁን በአገራችን ያለው የጤና አቅርቦት ኮሮና ሳይጨመር እንኳ በሥነ-ሥርዓቱ ግልጋሎት መስጠት ይችላል ወይ?» ሲሉ ይጠይቃሉ። የሚሰጡት መልስ የኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት ያሉበትን ውስብስብ ችግሮች የሚጠቁም መፃኢውን ፈተናም ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው።

Pakistan Coronavirus Covid

የሙቀት ልኬት የመጀመሪያው መለያ ሆኖ ያገለግላል

ዶክተር ሲሳይ «የጽኑ ሕሙማን ክፍል ያላቸው ሆስፒታሎች አገራችን ውስጥ ስንት ናቸው? እንደ ሀገር ከ200 በላይ ለህሙማን አተነፋፈስ እገዛ የሚያደርጉ መሳሪያዎች (mechanical ventilator) ያሉን አይመስለኝም። አብዛኞቹ ሆስፒታሎቻችን እንደ ፊት መሸፈኛ፤ ጓንት፣ ስሪንጆች፣ ጉሉኮስ እና ኦክስጅን የመሳሰሉ መሠረታዊ ግብዓቶች የሏቸውም። ለጽኑ ሕሙማን ሕክምና የሚሰጥ የሰለጠነ ባለሙያ ቁጥር አናሳ ነው። ያሉትም ከተሞች አካባቢ ነው» ሲሉ ያብራራሉ።

ከሳምንት ገደማ በፊት የጤና ምኒስትር ድዔታ ሆነው የተሾሙት ዶክተር ደረጀ ዱጉማም ቢሆኑ የኢትዮጵያ ተቋማት አቅም አገራቸው በኮሮና ሳቢያ ሊገጥማት የሚችለውን ፈተና ለመቋቋማቸው ማረጋገጫ የሚሰጥ መልስ የላቸውም። ዶክተር ደረጀ መስሪያ ቤታቸው ተጨማሪ ሶስት ሰዎች በኮሮና መያዛቸውን በምርመራ አረጋግጦ ይፋ ካደረገ በኋላ ለብሔራዊው ቴሌቭዥን "የአልጋ መጠናችን በጣም ያነሰ ነው። ጽኑ ሕሙማን የሚታከሙበት የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎቻችን እና የጤና ባለሙያ ዝግጅት በራሱ የግል ሆነ የመንግሥት ጤና ድርጅቶች ውስጥ በብዛትም  በጥራትም ያነሱ ናቸው" ሲሉ ተናግረዋል።

የኮሮና ጠባይ እንዴት ያለ ነው?

ከዋሽንግተን እስከ አዲስ አበባ፤ ከጀርመን እስከ ጣሊያን ዜጎች አንገብጋቢ ላሏቸው የለት ተለት ፍጆታዎች እንዲሰለፉ፤ ከዚህ ቀደም እምብዛም የማይጠቀሙባቸው ቁሳቁሶች በበእግር በፈረስ እንዲያፈላልጉ ያስገደደው ኮሮና መጀመሪያ ብቅ ያለው ከወደ ቻይና ነበር። እስከ መጋቢት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ በዓለም ዙሪያ 245,400 ሰዎች በተሕዋሲው ተይዘዋል፤ 10,000 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን ተነጥቀዋል።  የሕክምና ባለሙያዎች እንዳሉት ትኩሳት፣ ሳል እና ለመተንፈስ መቸገር ዋንኛ ምልክቶቹ ናቸው

"ቫይረሱ ከትንፋሻችን ጋር በሚወጡ ብናኞች ውስጥ ከአንድ ሜትር እስከ ሁለት ሜትር ይጓዛል። [ቫይረሱ] ብዙ መሄድ አይችልም፤ ክብደት አለው። በአካባቢው ባሉ ዕቃዎች ላይ ያርፋል። ንክኪ ሲኖር እጃችን ላይ ሊያርፍ ይችላል" የሚሉት ዶክተር ሲሳይ ለማ በስኳር፣ ልብ እና ደም ግፊት ሕሙማን እና ዕድሜያቸው የገፋ ሰዎች ላይ እንደሚበረታ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል። የበሽታ መከላከል አቅማቸው ከጤናማዎች አንፃር የተዳከመ፤ ትንባሆ የሚያጤሱ እና አልኮል የሚጠጡ ሰዎችም ጥንቃቄ ሊያደርጉ  እንደሚገባ ዶክተር ሲሳይ እስካሁን የሕክምና ባለሙያዎች በእጃቸው የገባውን መረጃ መሰረት አድርገው ይመክራሉ።

Symbolbild Hände waschen

እጅን መታጠብ ኹነኛው መፍትሔ ነው

የመዘናጋት ጣጣ

ኢትዮጵያ የመጀመሪያው በኮሮና የተያዘ ሰው መኖሩን ይፋ ባደረገች ማግሥት የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ ብልፅግና ፓርቲ በአዲስ አበባ የገቢ ማሰባሰቢያ አካሒዷል። መጋቢት 3 ቀን መረጃው ይፋ ተደርጎ እሁድ  መጋቢት 5 ቀን በሺሕዎች የሚቆጠሩ በአዲስ አበባ የአደባባይ ሩጫ ተሳትፈዋል። እንዲህ አይነቱ በርከት ያሉ ሰዎችን በአንድ ቦታ የሚያሰባስብ መርሐ ግብር ከተፈጠረው ሥጋት አኳያ ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የሕክምና እና የማኅበረሰብ ጤና ባለሙያዎች የሚቀበሉት አይደለም። መዘናጋት ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያንን ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል አቶ ትዝአለኝ ያሰጋቸዋል።

"ጣልያን በጣም እየተሰቃየች ያለችበት ዋንኛ  ምክንያት የመከላከያ እና መቆጣጠሪያ እርምጃዎችን አስቀድመው ባለመውሰዳቸው ነው። ተዘናግተው ማኅበረሰቡ ውስጥ ገባ። አንዴ ማኅበረሰቡ ውስጥ ከገባ አይደለም አነስተኛ ሐብት ያላቸው ከሰሐራ በረሐ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት ቀርቶ ጣልያን በዛን ያህል የተደራጀ ኃይል  መመለስ አልቻለችም" የሚሉት አቶ ትዝአለኝ ኢትዮጵያውያን በባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮችን በቅጡ ገቢራዊ እንዲያደርጉ ይመክራሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ "የኮሮና ቫይረስ ወደ አፍሪካ እና በማደግ ላይ ያሉ አገሮች እየገሰገሰ ነው። የጤና ግልጋሎቶቻቸው በጣም ደካማ ናቸው። ካደገው ዓለም ጠንካራ ድጋፍ ይሻሉ። ያን ድጋፍ ከተከለከሉ አደገኛ ጣጣ ይገጥመናል። አገሮች አቅም ሳይኖራቸው ቀርቶ ቫይረሱ በቁጥጥር ሥር ሳይውል ከቀረ እንደ ሰደድ እሳት ሊዛመት ይችላል። በዚህም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ሊሞቱ ይችላሉ" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

እሸቴ በቀለ

ተዛማጅ ዘገባዎች