ኢትዮጵያውያን ወጣቶችና የፌስቡክ ውይይት | ባህል | DW | 10.06.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

ኢትዮጵያውያን ወጣቶችና የፌስቡክ ውይይት

ከአዲስ አበባ እና ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የተውጣጡ ተመራማሪዎች የኢትዮጵያውያን የማህበራዊ ድረ-ገጽ እና የጥላቻ ንግግርን አስመልክተው ለሁለት አመታት የሰሩት ጥናት በአብዛኛው ወጣቶች በሚበረክቱበት የፌስቡክ ማህበራዊ ድረ-ገጽ ከተጻፉ የናሙና አስተያየቶች መካከል 0.4%ብቻ የጥላቻ ንግግር ተብለው እንደሚፈረጁ ጠቁሟል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:42

ኢትዮጵያውያን ወጣቶች እና የፌስቡክ ውይይት

የአዲስ አበባ እና ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያውያንን የማህበራዊ ድረ-ገጾች አጠቃቀም የፈተሹበትን 'መቻቻል' የተሰኘ ጥናት ይፋ አድርገዋል። ተመራማሪዎቹ በዚህ ጥናት በማህበራዊ ድረ-ገጾች በምርጫ ላይ የተደረጉ ውይይቶችና የጥላቻ ንግግር አጠቃቀምን ፈትሸዋል። ሁለት አመት የፈጀው የትብብር ጥናት ከማህበራዊ ድረ-ገጾች በፌስቡክ ላይ ያተኮረ ነው። ኢጊኒዮ ጋግሊያርዶኔ ከተመራማሪዎቹ መካከል አንዱ ናቸው።

«ፌስቡክን የመረጥንበት ምክንያት በኢትዮጵያ ተመራጭ ማህበራዊ ድረ-ገጽ በመሆኑ ነው። ታዋቂ ጦማሪዎችን የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች እና ፖለቲከኞችን ስናነጋግርም ሁሉም ተመራጭ መሆኑን ነግረውናል። ይህ የተለመደ አይደለም። ለምሳሌ ያህል በኬንያ በተለይም ለፖለቲካዊ ውይይት ትዊተር ተመራጭ ነው። ነገር ግን በአፍሪቃ እና ሌሎች ውስን የኢንተርኔት አገልግሎት ባለባቸው አገሮችም ተመሳሳይ ነው። እንደ ማይናማር በመሰሉ አገሮች ፌስቡክ ተመራጭ ነው። ለአንዳንድ ሰዎች ፌስቡክ ኢንተርኔት ነው።»

ይፋ የተደረገው የመቻቻል ጥናት ከሰበሰባቸው የናሙና አስተያየቶች መካከል 0.4%ብቻ የጥላቻ ንግግር ተብለው ተፈርጀዋል። እነዚህ ሌሎችን ጎሳቸውን፤ሐይማኖታቸውን እና ጾታቸውን መሰረት በማድረግ ግለሰቦች እንዲገለሉ የሚቀሰቅሱ መሆናቸውን ጥናቱ አትቷል። ከጥናቱ ናሙናዎች 0.3%ደግሞ በአንድ ቡድን ላይ ሰፊ ኹከት ለመቀስቀስ ጥሪ የሚያቀርቡ አደገኛ ንግግሮች ተብለዋል።

የጥላቻ ንግግር ሁሉንም የሚያስማማ ቁርጥ ያለ ትርጓሜ የለውም። የጥላቻ ንግግር ተብሎ የሚፈረጀው የትኛው ነው የሚለው ክርክር አሁንም መቋጫ አላበጀም። እነ ኢጊኒዮ ጋግሊያርዶኔ ጥናታቸውን የጀመሩት ነቃፊ እና ደጋፊ አስተያየቶችን በመለየት ነው።

«በግኝታችን መሰረት በኢትዮጵያ የሚገኙ ወጣቶች ከልዩነት ባሻገር ለመነጋገር ዝግጁ ይመስላሉ። በሌላ አነጋገር በወጣቶቹ ያለው የጥላቻ ንግር በትልልቅ ግለሰቦች ዘንድ ካለው ያነሰ ነው ማለት ነው። በኢትዮጵያ ያለው መገናኛ ብዙኃን ተጻራሪ ነው። መገናኛ ብዙኃኑ ለአሮጌው ትውልድ የወገኑ የሚያነሷቸው የቆዩ ቅራኔዎችን የተመለከቱ ርዕሰ ጉዳዮች በማህበራዊ ድረ-ገጾች አወዛጋቢ እና ኀይለኛ ክርክሮችን ይቀሰቅሳሉ። ወጣቶቹ ዓለም አቀፉ ርዕሰ ጉዳዮች ለመቀበል ፈቃደኛ መሆናቸውም ይታያል። በቡድናቸው ውስጥ ከመቆየት ይልቅ ከልዩነቶቻቸው ባሻገር በመነጋገር ማለት ነው። ከአሮጌው ትውልድ ይልቅ እድሜያቸው በ20ዎቹ ውስጥ የሚገኙ የአዲሱ ትውልድ ወጣቶች ያለፈ ቅራኔያቸውን ወደ ኋላ በመተው ወደ ፊት ለመመልከት ፈቃደኛ ናቸው።»

ምርጫና የጥላቻ ንግግር

ከአንድ አመት በፊት የተካሄደው እና ገዢው ፓርቲ መቶ በመቶ ያሸነፈበት ምርጫ በፌስቡክ ተጠቃሚዎች ዘንድ በስፋት ውይይት የተደረገበት እንደነበር የመቻቻል ጥናት ግኝት ይጠቁማል። የፌስቡክ ተጠቃሚ ኢትዮጵያውያኑ የጻፉት አስተያየትየምርጫው ውጤት ቀድሞ የታወቀ፤አጓጊ ያልነበረ እና አዲስ ነገር የማይጠበቅበት እንደነበር ይጠቁማሉ። በምርጫው ወቅት አዲስ ማህበራዊ አሊያም ፖለቲካዊ ውጥረት መፈጠሩን የሚጠቁም በቂ መረጃም አልተገኘም። አንድ ነጠላ ቡድን ተለይቶ የተቃርኖ ኢላማም አልሆነም። በመቻቻል ጥናት መሰረት የኢትዮጵያውያኑ የፌስቡክ ውይይት የምርጫውን ከንቱነት አሊያም ፍሬቢስነት በመጠቆም ላይ አተኩሯል። በሌሎች የአፍሪቃ አገሮች ምርጫ ሲቃረብ የጥላቻ ንግግር እድገት የማሳየት ልምድ አለ የሚሉት ኢጊኒዮ ጋግሊያርዶኔ በኢትዮጵያ ከዚህ የተለየ በእርሳቸው አባባል «አስገራሚ» ነገር እንደገጠማቸው ይናገራሉ።

« በተቀረው አፍሪቃ ምርጫ ሲመጣ የጥላቻ ንግግር የማደግ ምልክት እንደሚያሳይ የሚጠቁሙ መረጃዎች አሉ። በኢትዮጵያ ግን ይህ አልተከሰተም። ይህ ያልተፈጠረበት ምክንያት አብዛኞቹ ወጣቶች የምርጫው ውጤት ቀድሞ የታወቀ ነው ብለው በማመናቸው መሆኑን እና በፖለቲካ ምህዳሩ ምንም አይነት ለውጥ ባለመጠበቃቸው ለመረዳት ችለናል። በቅርብ ከተከታተልናቸው ጉዳዮች መካከል የተወሰኑ ኢትዮጵያውያን ከአይሲስ ጋር ግንኙነት ባላቸው አካላት በሊቢያ የተገደሉበትን ወቅት ነው። እንዲህ አይነት ክስተት የጥላቻ ንግግርን ሊቀሰቅስ በማህበራዊ ድረ-ገጾችም ከፍተኛ ውጥረት ይቀሰቅሳል ብለህ ልትጠብቅ ትችላለህ። የተፈጠረው ግን ተቃራኒው ነው። ውይይቶቹ ወደ ከፋ ጥላቻ አልተቀየሩም። በአንዳንድ ክስተቶች አሊያም ውስን ግለሰቦች ዙሪያ የሚደረገው ውይይት በውጥረት የተሞላ ነው። ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ወደ ኤርትራ ባቀኑበት ወቅት ይህ ተፈጥሯል። ሰዎች መንግስት እና ግንቦት ሰባትን በተለያዩ ጉዳዮች ሲወቅሱ ነበር። እነዚህ በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የጎሳ ዘለፋ እና የመሳሰሉትን የጨመረ ነበር። »

በመቻቻል የጥናት ግኝት መሰረት ለጥላቻ ንግግር ተንኳሽ የሆኑ የፌስቡክ ተጠቃሚ ኢትዮጵያውያን መካከል 92%ማንነታቸውን የደበቁ ግለሰቦች ናቸው። ተጽዕኖ ፈጣሪ ናቸው የተባሉት ለውይይት የሚጋብዙ አስታራቂ ሐሳብ አቅራቢ ናቸው።

«ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑት ግለሰቦች በሌላው ጠርዝ ካሉት አኳያ ለውይይት የሚጋብዙ እና አስታራቂ ሐሳብ አቅራቢ ሆነው አግኝተናቸዋል። ያገኘናቸው የጥላቻ አሊያም አደገኛ ንግግሮች በአብዛኛው ማንነታቸውን በደበቁ ግለሰቦች የተሰነዘሩ ናቸው። ብዙ የጥላቻ ንግግሮች የሚስተዋሉባቸው ቡድኖች ሊኖሩ ይችላሉ። ይሁንና እነዚህ ቡድኖች ተጽዕኖ ፈጣሪ አይደሉም። በተወሰኑ ተከታዮቻቸው ዘንድ ብቻ የተወሰኑ ናቸው። የመንግስት ደጋፊ እና ነቃፊ የሆኑ ግለሰቦች አሳታፊ/ተሳታፊ የሚያደርጓቸውን መንገዶች ለመከተል ይሞክራሉ። ለምሳሌ ከተከታተልናቸው ጦማሪዎች መካከል አንዱ እና የመንግስት ደጋፊ ነው ተብሎ የሚታሰበው ዳንኤል ብርሃነ ለተቺዎቹ እና ለተከታዮቹ ምላሽ በመስጠት አሳታፊ መንገድ ለመከተል ይሞክራል። ሌላው እንደ አለመታደል ሆኖ አሁን በእስር ላይ የሚገኘው የሰማያዊ ፓርቲ ቃል-አቀባይ የነበረው ዮናታን ረጋሳ ከዳንኤል በተቃራኒ ባለው ጎራ የሚገኝ ቢሆንም ውጤታማ በሆነ መንገድ የሚሳተፍ እና የጥላቻ ንግግር የማይጠቀም ነበር። በተለመደው ፖለቲካዊ ክርክር ውስጥ የሚሳተፍ ነበር።»

መንግስት እና ፌስቡክ

ለኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት እና ተቋማት የፌስቡክ ማህበራዊ ድረ-ገጽን ለመጠቀም ዳዴ ሲሉ ይስተዋላል። የተሳካላቸው በውይይቱ እና ክርክሩ ተቀባይነት ያገኙ ግን እጅጉን ጥቂት ናቸው። ለመሆኑ ወጣቶች የሚበዙበት የፌስቡክ መንደር ለሚያነሳቸው የጦፉ ክርክሮች የመንግስት ቦታ የቱ ጋ ነው። ለጥያቄዎችስ ምን ያክል ምላሽ ይሰጣሉ?

«እንደ አለመታደል ሆኖ ምንም ምላሽ አይሰጡም። ከመንግስት ባለስልጣናት መካከል በማህበራዊ ድረ-ገጾች ተጽዕኖ ፈጣሪ ናቸው ተብለው የሚታሰቡትን ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖምን አጠቃቀም ፈትሸናል። አብዛኛዎቹ የሚጽፏቸው ነገሮች አዎንታዊ ናቸው። በመንግስት ፖሊሲዎች ውጤታማነት ላይ ያተኩራሉ። ሰዎች ፕሮፖጋንዳ ነው ቢሉም መረጃ ሰጪ ናቸው። ነገር ግን እንዲህ አይነት ሰዎች ከሌሎች ጋር በውይይት እና ክርክር አይሳተፉም። ለጥያቄዎች ምላሽ አይሰጡም። ወደ ታችኛው የመንግስት አወቃቀር ስንወርድም የመወያየትና የመከራከር ባህል ያለ አይመስልም። ማህበራዊ ድረ-ገጽን ሰዎች ምን እንደሚያስቡ ለማወቅ እና ምላሽ ለመስጠት የመጠቀም ባህል የለም።»

እሸቴ በቀለ

ሒሩት መለሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች