ኢትዮጵያውያን ከጂዛን እስር ቤት ተማጽኗቸውን ያቀርባሉ | ዓለም | DW | 22.02.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ኢትዮጵያውያን ከጂዛን እስር ቤት ተማጽኗቸውን ያቀርባሉ

በመካከለኛው ምስራቋ ሳውዲ አረቢያ በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በእስር ላይ እንደሚገኙ የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የሳውዲ አረቢያ መንግስት ለኢትዮጵያውያን እስረኞች ምህረት እንደሚያደርግ ባለፈው ጥር ወር ቢያሳውቅም በርካታ ኢትዮጵያውያን አሁንም “የድረሱልን ጥሪ” ማሰማታቸውን ቀጥለዋል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:38

በሳውዲ አረቢያ ሺህዎች ኢትዮጵያውያን ታስረዋል

ሳውዲ አረቢያ በሺህዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ጎሮሮ መድፈኛ እና ጥሪት መቋጠሪያ እንደሆነችው ሁሉ ለሌሎች ሺህዎች ደግሞ በእስር መማቀቂያ ነች፡፡ እስር ቤቶቿ ከዓመት ዓመት ኢትዮጵያውያን አጥተው አያውቁም፡፡ አየር መንገዷ ከዓመት ዓመት ከሀገሪቱ የተባረሩ ኢትዮጵያውያን አሳፍረዉ አዲስ አበባ ላይ ከማፍሰስ አልቦዘኑም፡፡ ኢትዮጵያውያኑም ድንበር እያሳበሩ ወደ ሀገሪቱ መጎረፋቸውን አልተውም፡፡

ለሁሉም ግን ያሰቡት አይሞላም፡፡ ድንበር ላይ ተይዞ ወደ ወህኒ መወሰድ ለስደተኛ ኢትዮጵያውያን እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ የመን ድንበር አቅራቢያ የሚገኘው የጂዛን እስር ቤት ሺህዎች ኢትዮጵያውያንን ከሚያስተናግዱ ቤቶች አንዱ ነው፡፡ ከእስረኞቹ መካከል  በድብቅ በሚጠቀሙበት ተንቀሳቃሽ ስልክ ለጣቢያችን የደረሰ መልዕክት እንደሚጠቁመው በትንሹ ሁለት ሺህ ኢትዮጵያውያን በእስር ላይ አሉ፡፡ ስሙ እንዳይገለጽ የጠየቀ  የ25 ዓመት እስረኛ ወጣት ግን ቁጥሩን ከፍ ያደርገዋል፡፡

“በክፍል በክፍል ስለሆነ ይህን ያህል ነው ማለት አይቻልም፡፡ በግምት ግን ወደ 3500 አካባቢ ይሆናል፡፡ ቢያንስ በአንድ መኝታ ላይ ያለማካባድ ማለት ነው ሶስት፣ አራት ሰው ነው ተደራርቦ የሚተኙት እና አስቸጋሪ ነው፡፡ ቢያንስ አንድ ክፍል ውስጥ ከ60 እስከ 70 ኢትዮጵያውያን ነው አንድ ላይ የምንተኛው”ይላል።

ከታሰረ ሁለት ዓመት እንዳለፈው የሚናገረው ይህ ወጣት በእስር ቤቱ የሚገኙት አብዛኞቹ በእርሱ የዕድሜ ክልል የሚገኙ እንደሆኑ ይገልጻል፡፡ ገና ዕድሜያቸው ለአቅመ አዳም ያልደረሰ ወጣቶችም በርካታ እንደሆኑ ያስረዳል፡፡ አብዛኞቹ እስረኞች ጥይት፣ አደንዛዥ ዕጽ እና ጫት ተገኝቶባቸዋል በሚል መታሰራቸዉን  ይናገራል፡፡ “ዕድለኛ ሆኜ ከተያዝኩ ከአንድ ዓመት ከስምንት ወር በኋላ ፍርድ ቤት ቀርቤ ነበር” የሚለው ወጣቱ 95 በመቶ የሚሆኑት እስረኞች ግን ይህን ዕድል እንዳላገኙ ይገልጻል፡፡

“ወደ ሳውዲ አረቢያ ስትገባ አደንዛዥ ዕጽ ይዘህ ተገኝተሃል” በሚል 12 ዓመት የተፈረደበት እስረኛው የእስር ጊዜውን ካጋመሰ ሊፈታ እንደሚችል መስማቱን ይናገራል፡፡ እርሱም ሆነ ሌሎች በጂዛን ያሉ እስረኞች የሳውዲ አረቢያ መንግስት ባለፈው ጥር ወር ለኢትዮጵያውያን እስረኞች ምህረት እንደሚያደርግ ሲሰሙ ተስፋቸው ለምልሞ ነበር፡፡ ሆኖም ጥቂት ኢትዮጵያውያን የመለቀቃቸውን ዜና ከመስማታቸው በቀር ሁሉም ነገር የውሃ ሽታ ሆኖባቸዋል፡፡ 

ከጂዛን እስር ቤት መልዕክታቸውን የላኩ ኢትዮጵያውያን አብረዋቸው ታስረው የነበሩ እና በተመሳሳይ ወንጀል የተፈረደባቸው እስረኞች ሲለቀቁ እነርሱ ግን አሁንም በወህኑ ቤት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ “ፊርማ ፈርመን፤ ትወጣላችሁ ተብለን፤ ዝም ብለን አለን” ይላሉ፡፡ ከመካከላቸው ፍርዳቸውን አጠናቅቀው ያልተፈቱ እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡ በድብቅ ስልክ ያነጋገረን ወጣትም ሀሳባቸውን ይጋራል፡፡

“በእርግጥ ተፈርሟል፡፡ የሚገርምህ ነገር ቢያንስ ወደ አንድ ሺህ የሚሆን ሰው ፈርሟል፡፡ ፊርማው የምን እንደሆነ አይታወቀም፡፡ ከዚህ በፊት የወጡ እና አገር ቤት የሄዱ አራት አምስት የሆኑ ልጆች ነበሩ፡፡ አሁን እንደዚያ አይነት ፊርማ ሲፈረም በቃ ሁሉም ‘ሀገራችን እንሄዳለን’ ብሎ ነበር የፈረመው፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ምንም ነገር የለም፡፡ ቢያንስ አራት ወይም አምስት ወር አስቆጥሯል ይሄ ፊርማ ከተፈረመ” ይላል ተስፋ በቆረጠ ስሜት፡፡ 

በሳውዲ አረቢያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዲፕሎማቶች ከሶስት ሳምንት በፊት መጥተው እንደጎበኟቸው ከዚያ በኋላ ግን ምንም የተለየ ነገር እንደሌለ ወጣቱ እስረኛ ተናግሯል፡፡ በሳውዲ የኢትዮጵያ አምባሳደር አሚን አብዱልቃድር እና በኤምባሲው የዲያስፖራ ተሳትፎና የቆንስላ ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፈይሰል አልይን በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው ላይ በተደጋጋሚ ብንደውልም ልናገኛቸው አልቻልንም፡፡

በዶይቸ ቨለ የማህበራዊ መገናኛ አድራሻዎች  አስተያየታቸውን የሰጡ ተከታታዮቻችን በሁለት ጎራ ተከፍለዋል፡፡ ገሚሶቹ “ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ማንኛውም ሰው የሀገሪቱን ህግ አክብሮ የሚንቀሳቀስ ከሆነ ለችግር አይጋለጥም፡፡ በህገ ወጥ እንቅስቃሴዎች ላይ ከተገኙ ግን መታሰራቸው አይቀሬ ነው” የሚል አቋም አላቸው፡፡ ሌሎች  “የኢትዮጵያ መንግስት እና ኤምባሲው ለዜጎቻቸው ተቆርቋሪ ቢሆኑ ኑሮ ኢትዮጵያውያን ችግር አይደርስባቸውም ነበር” የሚል አስተያየታቸውን አካፍለዋል፡፡

ቀደም ሲል በሳውዲ አረቢያ እስር ቤቶች ታስረው እንደነበር የጠቀሱ ተከታታዮቻችን ደግሞ በዋትስአፕ አድራሻችን በድምጽ አስተያየታቸውን አጋርተውናል፡፡

“ሁሴን እባላለሁ፡፡ ሳውዲ አረቢያ ውስጥ 12 ዓመት ተቀምጫለሁ፡፡ ዞሬያለሁ፤ ኖሬያለሁ፤ ታስሬያለሁ፡፡ ስታስርም ወንጀል ሰርቼ ሳይሆን በቃ ህጋዊ ስላልነበርኩ ነው፡፡ ህጋዊ ፍቃድ ሳይኖረኝ እየኖርኩ ነበር፡፡ ስያዝ ከ15፣ ከ20 ቀን በኋላ ወደ ሀገሬ ይመልሱኛል፡፡ ግን ወንጀል ሲሰሩ፣ ተው የተባሉትን ነገር ሲሰሩ የተገኙ ሰዎች ሊታሰሩ ይችላሉ፡፡ እኔም የምለው ጥፋታችንን ለምን አንታረምም፡፡ ለምን እንጠፋለን ነው” ሲሉ አሁን በኢትዮጵያ ኖሯቸውን ያደረጉ አድማጭ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡  

ሌላኛው የቀድሞ እስረኛ በበኩላቸው ይህን ይላሉ፡፡ 

“ቢያንስ አራት አምስት ጊዜ የተያዝኩበት ጉዳይ ነው፡፡ ሳውዲ አረቢያ በኢትዮጵያ ላይ የምታደርሰው ጫና በጣም ከፍተኛ እና እንግልት የሚያደርስ መሆኑን እገልጻለሁ፡፡ ጂዛን እስር ቤት ላይ የሚሰቃዩ ኢትዮጵያዊ ዜጎች ከመጠን በላይ ንጹሃን ዜጎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት አስከፊ ነው፡፡ ጩኸት የሚሰማበት አካባቢ አይደለም፡፡ እዚያ ቦታ ላይ ምንም ተጠያቂ የሚሆን አካል የለም፡፡ በግድ ነው በህይወት አምልጠን የመጣነው” ይላሉ መሐመድ ሑመድ የተባሉ በጂዛን ታስረው የነበሩ ኢትዮጵያዊ፡፡  

አሁን በጂዛን በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ግን መፍትሄ የሚሏቸውን ሶስት ነገሮች በመልዕክታቸው ጠቁመዋል፡፡ የመጀመሪያው “ምህረት የሚቻል ከሆነ በምህረት ማውጣት” ነው ይላሉ፡፡ “ይህ የማይቻል ከሆነ ደግሞ ፍርዳችንን በአገራችን ታስረን እንድንጨርስ እንጠይቃለን” ባይ ናቸው፡፡ ሁሉም ጥረት ከከሸፈ ግን “በሳውዲ አረቢያ ህጋዊ ወደ ሆነ ማረሚያ እንድንታሰር ይደረግልን” ሲሉ ተማጽኗቸውን ያቀርባሉ፡፡ 

 

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic