ኢትዮጵያውያን በባሕር እልቂት | ኢትዮጵያ | DW | 22.04.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያውያን በባሕር እልቂት

ባለፈው ረቡዕ ሜዲትራንያን ባሕር ውስጥ 500 ያኽል ስደተኞች ሠጥመው ሳያልቁ እንዳልቀሩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገልጧል። ምን ያኽሉ ስደተኞች የየት ሀገር ዜጋ እንደሆኑ ግልፅ መረጃ ባይኖርም በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙበት እየተነገረ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:34

እልቂት በሜዲትራንያን ባሕር

ከአደጋው በሕይወት ከተረፉት 41 የባሕር ላይ ስደተኞች መካከል፤ 23 ሶማሊያውያን፣ 11 ኢትዮጵያውያን፣ ስድስት ግብፃውያን እና አንድ ሱዳናዊ ይገኙበታል ተብሏል። በውል ምን ያኽል ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በአደጋው እንዳለቁ ግን በውል አልተነገረም።

ባለፈው ሣምንት ቅዳሜ በሊቢያ እና ጣሊያን የባሕር ክልል ትቀዝፍ በነበረች የንግድ መርከብ ታይተው በሕይወት ከተረፉት ስደተኞች መካከል የተገኘው ሙአዝ መሐመድ ከኦሮሚያ ኢትዮጵያ እንደመጣ ለሮይተርስ የዜና ምንጭ ተናግሯል። በማኅበራዊ የመገናኛ ዘርፎች እና በኢንተርኔት የመረጃ መረቦች እንደሚነገረው ከሆነ በመርከቢቱ ውስጥ አደጋ የደረሰባቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን የኦሮሚያ አካባቢዎች ተወላጆች ናቸው።

እዚህ ጀርመን ሀገር በስደት መኖር ከጀመረ ስምንት ወራትን ያስቆጠረው ሐሠን ዓሊ አደም የታላቅ ወንድሙን መርዶ የተረዳው ግብጽ በስደት ከሚገኙ ጓደኞቹ እና ቤተሰቦቹ እንዲሁም ከፌስቡክ ነው።

ስደተኞቹ ከ100 እስከ 200 የሚደርሱ ስደተኞችን በያዙ ቡድናት ተከፋፍለው በተለያዩ ጀልባዎች ጉዞ የጀመሩት ከሊቢያዋ ቶብሩክ ከተማ መሆኑን በሕይወት የተረፉት በተመድ የስደተኞች መርጃ ከፍተኛ ኮሚሽነር (UNHCR) ተናግረዋል።
እንደ የተመድ ዘገባ ከሆነ ስደተኞቹ በሕገ-ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች ለሰአታት ከተጓዙ በኋላ ባሕሩ መሐል ቆማ የምትጠብቃቸው ጀልባ ላይ ታጭቀው እንዲጫኑ ተገደዋል።

በሜዲትራኒያን ባሕር ወደ አውሮጳ ለሚሻገሩ ስደተኞች መብት የሚሟገተው «ኤጀንሲያ ሐበሺያ» ኃላፊ አባ ሙሴ ዘርአይ ከተረፉ ስደተኞች ባሰባሰቡት መረጃ መሠረት ስደተኞቹ በአራት የተለያዩ ጀልባዎች ነው የተጓጓዙት፤ የየት ሀገር ስደተኞች እንደሆኑ ግን በውል ማወቅ አልተቻለም ብለዋል።

ላለፉት ዐሥር ዓመታት ግድም በበጎ ተግባር የተሰማሩት አባ ሙሴ ከነበረው መጠነኛ የባሕር ንፋስ ባሻገር ጀልባዋ ከአቅሟ በላይ ስደተኞቹን በመጫኗ መገልበጧን ተናግረዋል። ስደተኞቹ ለሦስት ቀናት ያለምግብ እና ውኃ ባሕር ላይ መጓዛቸውን አክለዋል።

በስዊድን ነዋሪ የሆኑት ኤርትራዊትዋ የስደተኞች መብት ተሟጋች ወ/ት ሜሮን እስጢፋኖስ በበኩላቸው ባሰባሰቡት መረጃ መሠረት አደጋ ከደረሰባቸው ስደተኞች መካከል እስካሁን ኤርትራውያን አሉበት የሚል መረጃ እንዳልደረሳቸው ተናግረዋል። «እስካሁን ባለን መረጃ መሠረት ስደተኞቹ ኢትዮጵያውያን፣ ሶማሌያውያን እና ግብፃውያን ናቸው» ብለዋል። ስደተኞቹ የመጡባቸው ሃገራት እና አውሮጳውያን መንግሥታትን ግን ወቅሰዋል።

«368 ኤርትራውያን እና ስምንት ኢትዮጵያውያን በሰጠሙበት የላምፔዱዛው እልቂት በሚያሳዝን መልኩ ከሁለቱም ሃገራት መንግሥታት ምንም አስተያየት አልሰማሁም። አውሮጳውያንን በተመለከተ፤ ይኼ ድንበርህን ስትዘጋ የሚከሰት ነው። ያን ማድረግህ እንደውም ስደተኞችን ለበለጠ እልቂት እና ተጨማሪ እንግልት ያጋልጣቸዋል። ፍልሰትን ሊያስቆም አይችልም።»

እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2015 ብቻ 3,700 ስደተኞች ሜዲትራንያን ባሕር ውስጥ ሠጥመው አልቀዋል። ባለፉት አራት ወራት ደግሞ እዛው ባሕር ላይ 761 ሞተዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic