ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በካኩማ የስደተኞች ጣቢያ | ወጣቶች | DW | 12.05.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ወጣቶች

ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በካኩማ የስደተኞች ጣቢያ

በኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገር ኬንያ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ይገኛሉ። ስደተኞቹ በምን አይነት ሁኔታ ይኖራሉ? ለምንስ ሀገራቸውን ጥለው ተሰደዱ?  የተወሰኑ በካኩማ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ጠይቀናል። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:48

ካኩማ የስደተኞች ጣቢያ

የካኩማ የስደተኞች ጣቢያ የተመሠረተው እኢአ በ1991 ዓም ሲሆን የሚገኘውም ሰሜን ምዕራብ ኬንያ ውስጥ ነው። በዚሁ መጠለያ ጣቢያ 185 000 የሚጠጉ ሰዎች ይኖራሉ። አብዛኞቹም ከሀገራቸው የዕርስ በዕርስ ጦርነት የሸሹ ደቡብ ሱዳናውያን ሲሆኑ ሶማላዊያን፣ ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራውያን እና ሌሎች የአፍሪቃ ሀገራት ዜጎችም በዚሁ መጠለያ ይኖራሉ።

በኬንያ በትልቅነቱ ከዳዳብ የስደተኞች መጠለያ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ በሚገኘው የካኩማ ስደተኞች ጣቢያ ከ12 ሀገራት በላይ የመጡ ስደተኞች ይኖራሉ። ከነዚህ አንዱ ቢንያም ብላችሁ ጥሩኝ ያሉን ኢትዮጵያዊ ናቸው። በዚሁ መጠለያ መኖር ከጀመሩ ሶስት ዓመት አለፋቸው። ኬንያ የገቡት ባለቤታቸው እና አንድ ልጃቸውን ኢትዮጵያ ጥለው ነው።በፖለቲካ ምክንያት ከሀገር ሸሽተው በኬንያ ጥገንነት ሲጠይቁ ቢንያም በቅድሚያ የተላኩት ወደ ኬንያ መዲና ናይሮቢ ነበር። ከዛም ወደ ካኩማ ነው።

ቢንያም በዚሁ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የተቀንቀሳቃሽ ስልክ ባትሪ በመሙላት የተወሰነች መተዳደሪያ ገንዘብ ለማግኘት ይሞክራሉ። የተወሰኑ ኢትዮጵያውያን ደንበኞችም አሏቸው።

እድል የገጠማቸው በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን በእንግሊዘኛው ምህፃር UNHCR አማካኝነት ወደሌሎች ሶስተኛ ሀገራት ተሻግረው ጣቢያውን ይለቃሉ። ሌሎች ደግሞ ከጣቢያው ጠፍተው ወደ ደቡብ ሱዳን እና ዮጋንዳ የመሳሰሉት ሀገራት ይሸሻሉ። ይህ ያልተሳካላቸው ደግሞ ልክ እንደ ወጣት ናና አሁንም ካኩማ ውስጥ ይኖራሉ። ናና ከኢትዮጵያ ስትወጣ ዘጠኝ ዓመቷ ነበር። ዘንድሮ ኬንያ በሚገኘው የካኩማ የስደተኞች ጣቢያ 18 ዓመቷን አከበረች። ናና አያቷ ሲሞቱ የተሻለ ህይወት ፍለጋ ነው ከአክስቷ ጋር ወደ ኬንያ የተሰደዱት።  ከልጅነቷ አንስቶ የምታውቀውም የስደት ኑሮን ቢሆንም ወጣቷ  በዚያው በጣቢያው ትምህርቷን መከታተል ችላለች። ትምህርቱም በኪሲዋሂሊኛ እና እንግሊዘኛ ነው።

የካኩማ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የሚገኘው በኬንያ ሁለተኛ ደሀ የሚባለው አካባቢ  ሲሆን አብዛኛው ጊዜም በስደተኞቹ እና በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ግጭት ተስተውሏል። ስደተኞችም የተመጣጠነ ምግብ ባለማግኘት፤ በተላላፊ በሽታዎች እና ወባ ብዙውን ጊዜ ይጎዳሉ።

ካኩማ መኖር ከጀመሩ 10 አመት ያስቆጠሩት ኢትዮጵያዊት ወይዘሮ ወርቅነሽም ቢሆኑ ያለውን ችግር ዘርዝረው አይጨርሱትም።ወይዘሮዋ እንጀራ እየጋገሩ እና እየሸጡ የዕለት ኑሯቸውን ይገፋሉ። ምኞታቸው ወደሌላ የተሻለ ቦታ መሄድ ወይም እዛው ባሉበት ያለው ሁኔታ እንዲስተካከል ነው።

ሌላው የካኩማ የስደተኞች ጣቢያ ነዋሪ ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ ኢትዮጵያዊ ናቸው። እኝህም ሰው ከተሰደዱ 7 አመት ሆናቸው። አሁን በሚኖሩበት ኬንያ ነጠላ ጫማ በመሸጥ ይተዳደራሉ።

ሙሉውን ዘገባ በድምፅ ያገኙታል።

ልደት አበበ

አዜብ ታደሰ

 

 

Audios and videos on the topic