ኢትዮጵያውያንን ለሞት እየዳረገ ያለው የፌስቡክ ላይ የጥላቻ ፅሁፍ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 21.12.2022
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ኢትዮጵያውያንን ለሞት እየዳረገ ያለው የፌስቡክ ላይ የጥላቻ ፅሁፍ

ግዙፉ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ፌስቡክ ናይሮቢ በሚገኘው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያለፈው ሳምንት ክስ ተመስርቶበታል።ድርጅቱ ክስ የተመሠረተበት በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው የርስ በርስ ጦርነት ጥላቻን የሚሰብኩ እና ግጭት የሚያነሳሱ መልዕክቶችን አሰራጭቷል ተብሎ ነው።ከእመልካቾቹ መካከል በፌስ ቡክ የጥላቻ መልዕክት አባቱ የተገደሉበት ተጎጅ ይገኝበታል።

ኢትዮጵያውያን በፌስቡክ ላይ ከስ መሰረቱ


ፌስቡክ ጊዜ እና ቦታ ሳይገድበው መረጃን በቀላሉ በማሰራጨት የሚመሰገነውን ያህል በዚያው ልክ ደግሞ ጥላቻ እና ግጭት አባባሽ መልዕክቶችን በማስፋፋት  ተደጋግሞ ይወቀሳል።
ከሰሞኑም የፌስቡክ እናት ኩባንያ ሜታ በኢትዮጵያ ጥላቻ አዘል እና ግጭት አባባሽ መልዕክቶችን በአግባቡ አልተቆጣጠረም በሚል  ክስ ቀርቦበታል።
በኬንያ ናይሮቢ በድርጅቱ ላይ የቀረበው ክስ  ሁለት  ቢሊዮን የሚጠጋ ዶላር ካሳ የሚጠይቅ ነው።
ያለፈው ሳምንት ረቡዕ በጎርጎሪያኑ ህዳር 14 ቀን 2022 ዓ/ም  በኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሁለት ግለሰቦች እና በአንድ የመብት ተሟጋች ድርጅት የቀረበዉ ክስ፤ ሜታ በፌስቡክ ገፆች ላይ ለቀረቡ የጥላቻ ይዘቶች በተለይም የሰሜን ኢትዮጵያ  የትግራይ  ጦርነትን በተመለከተ በቂ ምላሽ አልሰጠም ተብሏል።
ከአመልካቶቹ መካከል አንዱ የሆነው የትግራይ ተወላጁ አብርሀም ማዕረግ እንደሚለው አባቱ  ፕሮፌሰር ማዕረግ አማረ አብርሃ በጎርጎሪያኑ ህዳር ወር  2021ዓ/ም  ከመገደላቸው በፊት በፌስቡክ የዘረኝነት መልዕክቶች ዒላማ ነበሩ።ያምሆኖ ፤ ድርጅቱ እነዚህን ጽሁፎች እንዲያጠፋ ለቀረበለት ጥያቄ ፈጥኖ ምላሽ አልሰጠም።በዚህ የተነሳ አባቱ መገደላቸውን ተናግሯል።
አብርሃም አያይዞም «ፌስቡክ የጥላቻ  ፅሁፎችን በአግባቡ ቢቆጣጠር እና ቢያስቆም ኖሮ አባቴ በህይወት ይኖር ነበር»ሲል ተናግሯል።


በመሆኑም  የጥላቻ ንግግር እንዲራገብ አድርጓል በሚል በፌስቡክ እናት ኩባንያ ሜታ ላይ ክስ መስርቷል። በኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተመሠረተውን ይህንን ክስ  ፎክስግሎቭ የተባለ የመብት አቀንቃኝ ቡድንም ይደግፈዋል።
የመብት ተሟጋች ድርጅቱ ዳይሬክተር የሆኑት ብሪታኒያዊቷ ጠበቃ ሮዛ ከርሊንግ ለDW እንደገለፁት በፌስቡክ እየተወሰደ ያለው የይዘት ማስተካከያ ውሳኔ  የሞት እና የህይወት ጉዳይ ሆኗል።
«ይህ ጉዳይ ፈታኝ ነው። በፌስ ቡክ  እየተሰራጨ ያለው ጥላቻ  ሰዎች እንዲሞቱ አድርጓል። በፌስቡክ እየተወሰዱ ያሉት የይዘት ማስተካከያ ውሳኔዎች የህይወት እና የሞት ጉዳዮች ናቸው። ከአብረሃም እንደሰማችሁት በፌስቡክ ላይ ሁለት ጥላቻ አዘል መልዕክቶች በገፁ ላይ ከተለጠፉ በኋላ የአባቱ በግፍ መገደል ለቤተሰቦቹ የሚያሳዝን ጉዳይ  ነበር። ምንም እንኳ  አብርሃም በተደጋጋሚ  ቢነግራቸውም ፅሁፉን ከገፁ አላነሱትም። ፌስቡክ የይዘት ቁጥጥር  በሚያደርግባቸው መንገዶች ላይ ለውጦች እንዲደረጉ እንጠይቃለን።»
የአብርሃም ጠበቃ ሜርሲ ሙተሚ  ፌስቡክ ይዘቱ እንዲወርድ አብርሀም ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት አንድ ወር ፈጅቶበታል ሲሉ ድርጅቱን ይተቻሉ። ሙተሚ እንዳሉት ፌስቡክ ይዘቱ የማህበረሰብ መስፈርቶችን እንደጣሰ ቢያውቅም ከአንድ አመት በኋላ እንኳ ገፁ ላይ የተለጠፈው አንደኛው የጥቃት ፅሁፍ አሁንም ድረስ አልተነሳም። ምክንያቱም አብርሃም እንደገለፀው መሰል ይዘቶች የተጠቃሚዎችን ተሳትፎ ስለሚጨምሩ እንዲነሱ አይደረግም።
በቤተሰቡ የደረሰው በሌሎች እንዳይደርስ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት መውሰዱን የገለፀው አብርሃምም፤ «በፌስቡክ ትርፍ ማጋበስ ለተጎዱ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ አፍሪካውያን ወገኖቼ ፍትህ እና ለአባቴ ግድያ ድርጅቱ ይቅርታ እንዲጠይቅ አፈልጋለሁ።»ብሏል።
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ተመራማሪ የሆኑት አቶ ፍስሃ ተክሌ ሌላው አመልካች ናቸው።እሳቸው እንደሚሉት  ድርጅቱ ስለጦርነቱ ባወጣቸው መረጃዎች ሳቢያ በፌስቡክ  ለሚሰራጭ ጥላቻ አዘል ፅሁፍ ተጋልጠዋል።ይህም የቤተባቸውን ሕይወት አደጋ ላይ ጥሏል።ከዚህ ባሻገር የፌስቡክ የይዘት ቁጥጥር ማነስ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በግጭቱ የደረሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ የሚያወጣቸውን ዘገባዎች ማደናቀፉንም ገልፀዋል። 

Logo amnesty international


ሌላው አመልካች የኬንያ የመብት ተሟጋች የሆነው የካቲባ ኢንስቲትዩት ሲሆን፤ ይህ ተቋም እና ሌሎቹ የክሱ አመልካቶች በፌስቡክ የመረጃ ትንተና ቀመር  /አልጎሪዝም/ ላይ ለውጦች እንዲደረጉ እንዲሁም ጥላቻን የሚሰብኩ አደገኛ ይዘቶችን ከማሰራጨት እንዲቆጠብ በክሱ ጠይቀል። 
 በሌላ በኩል 500 ሚሊዮን ህዝብ ለሚሸፍነው ምስራቃዊ እና ደቡባዊ ሰፊ  የአፍሪካ ክፍል የመቆጣጠር ኃላፊነት የተጣለው ናይሮቢ በሚገኙ ጥቂት የይዘት ክትትል ባለሙያዎች ላይ በመሆኑ  ሜታ በሀገር ውስጥ ቋንቋዎች የይዘት ቁጥጥር የሚያደርጉ ተጨማሪ ሠራተኞችን እንዲቀጥር ክሱ ይጠይቃል።
ከርሊንግ ከDW ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስም ፌስቡክ ስልተ ቀመሮቹን መቀየር ብቻ ሳይሆን አመፅ እና ጥላቻን የሚያሳዩ ጽሁፎችን የማስወገድ ኃላፊነት ለተሰጣቸው የይዘት ክትትል ሰራተኞችም  የበለጠ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ብለዋል።
«ናይሮቢ በአፍሪካ 500 ሚሊዮን ለሚሆኑ ተጠቃሚዎች የይዘት ማስተናገጃ ማዕከል ነች። እናም ይህንን ስራ ለሚሰሩ የይዘት ክትትል ባለሙያ ግለሰቦች በአግባቡ ዋጋ መስጠት፣ በአግባቡ እንዲከፈላቸው ማድረግ  እና  የሰው ሀይል ጭማሪ ማድረግ ወሳኝ ነው።117 ሚሊዮን ሰዎች ላሉት የኢትዮጵያ ገበያ  ፌስቡክ  በአሁኑ ጊዜ 25 የይዘት ክትትል ባለሙያዎችን ብቻ ይጠቀማል። ያ በጣም በቂ አይደለም።»


አብረሃም በሰጠው ምስክርነት  ፌስቡክ በአፍሪካ ያለው የይዘት ቁጥጥር (Content moderation)አነስተኛ ሲሆን፤በኢትዮጵያም በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ እና በትግርኛ ይዘቶችን የሚፈትሹ ባለሙያዎች ጥቂት መሆናቸውን አመልክቷል። 
አቤቱታ አቅራቢዎቹ በጎርጎሪያኑ ጥር 6፣ 2021 ዓ/ም በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች በአሜሪካ ካፒቶል ላይ  ጥቃት በደረሰ ጊዜ ድርጅቱ ከወሰደው ፈጣን ምላሽ ጋር በማነፃጸር ፤ ፌስቡክ በአፍሪካ  ተጠቃሚዎቹ ላይ «ስልታዊ አድልኦ» ፈፅሟል ብለዋል። 
 በፌስቡክ  በሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮች እና በግጭት አነሳሽ ይዘቶች ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው ካሳ የሚሆን 1.6 ቢሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፈል አቤቱታ አቅራቢዎቹ  ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል
በዚህ ሁኔታ በይዘት ክትትል ማነስ፣ በጥላቻ እና በግጭት አባባሽ ንግግርን በማስፋፋት  እየተከሰሰ ያለው  ፌስቡክ በዓለም አቀፍ ደረጃ 10,000 ሰዎችን ከስራ ሊያሰናብት መሆኑን ሲገልጽ ቆይቷል።ውሳኔው የንግድ እና ገቢን የማሳደግ  ውሳኔ መሆኑን ድርጅቱ አመልክቷል።ከዚህ አንፃር ሜታ በርካታ ሰዎችን የመቅጠሩ ነገር አጠራጣሪ መሆኑን የሚገልፁም አሉ። ይህም ችግሩን በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ እንዳያደርገው ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ። ብሪታኒያዊቷ ጠበቃ ሮዛ ከርሊንግም  የፌስቡክ እርምጃ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎችን ለሞት እየዳረገ በመሆኑ በርከት ያሉ የይዘት ክትትል ሰራተኞችን መቅጠር አለበት ይላሉ።
«ኩባንያው በሚያስደንቅ ሁኔታ ሀብታም እና ብዙ ሰዎችን መቅጠር የሚችል  ነው። እኛ እያቀረብናቸው ያሉት ሁለት ፍላጎቶች። አንደኛው የሶፍትዌር ዲዛይናቸውን ስለማስተካከል ነው። ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት ፌስቡክ ምቹ የጥላቻ ንግግር  ማስፋፊያ  ቦታ ሆኗል። ያንን እንዲያስቆሙ እና እጅግ በጣም ብዙ ተጨማሪ የይዘት ተቆጣጣሪዎችን እንዲቀጥሩ እየጠየቅን ነው። ከኢትዮጵያ ጋር በተያያዘ ከጠቀስኳቸው 25 የይዘት አወያዮች ውስጥ 25ቱ አሁን በኢትዮጵያ ከሚነገሩት 85 ቋንቋዎች ውስጥ ሶስቱን ብቻ ይናገራሉ። ይህ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም።ይህ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎችን ለሞት እየዳረገ ነው እና መቆም አለበት።የኬንያ ፍርድ ቤቶትም ያንን ይደርጋል የሚል በጣም ትልቅ ተስፋ አለኝ።»
ሜታ በበኩሉ በገጹ የሚንሸራሸሩ መልዕክቶችን ለማጥራትና ጥላቻ አዘል የሆኑትን ለማስወገድ ከፍተኛ  ጥረት ማድረጉን ይገልፃል።

የድርጅቱ ቃል አቀባይ ቤን ዋልተርስ በጉዳዩ ላይ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ  እንደተናገሩት ኩባንያው በፌስቡክ እና ኢንስታግራም ላይ የተፈቀዱትን እና ያልተፈቀዱትን የሚገልጹ ጥብቅ ደንቦች  አሉት። የጥላቻ ንግግር እና ግጭት አነሳሽ መልዕክቶችም ከገጹ መርህ ጋር ይጣረሳሉ ይላሉ። በዚህም መሰረት  አካላዊ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ስጋት ሲኖር የተሳሳተ መረጃን አስወግደናል በማለት ገልፀዋል። በኢትዮጵያም  ተመሳሳይ ስራ መሰራቱን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል። እሳቸው ይህን ይበሉ እንጅ ተንታኞች እንደሚሉት፣ ሜታ እና ሌሎችም ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሐሰተኛ መረጃዎችን፣ የጥላቻ ንግግሮችን እና ግጭት የሚያነሳሱ ይዘቶችን በመቆጣጠር  እና ከገጻቸው በማስወገድ ረገድ  በቂ ጥረት ሲያደርጉ አይታይም።
በዚህ የተነሳ  ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሁለት አመቱ በኢትዮጵያ ጦርነት በሁለቱም ወገኖች የታዩ  ወደ ዘር ማጥፋት የሚወስዱ የጥላቻ  እና ሰብዓዊነት የጎደላቸው ንግግሮችን በተለያዩ መንገዶች ሲያወግዝ ቆይቷል። 
ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ፌስቡክ፤ከዚህ ቀደምም ከማይናማር ወደ ጎረቤት ባንግላዲሽ በፀጥታ ሃይሎች በተወሰደ እርምጃ በተባረሩ የሮሂንጊያ ስደተኞች  ላይ የሚሰነዘረውን የጥላቻ ንግግር ማስቆም አልቻለም በሚል በ2021 ዓ/ም መገባደጃ ላይ የ150 ቢሊዮን ዶላር ክስ ቀርቦበታል።
በመሆኑም በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች ሀገራት ችግሩ በአግባቡ እንዲፈታ በድርጅቱ ላይ ግፊት ማድረግ አስፈላጊ ነው ይላል።ከዚህ ቀደም DW ያነጋገረው  የመብቶች እና የዲሞክራሲ እድገት ማዕከል በእንግሊዥኛው ምህፃሩ CARD በመባል የሚጠራው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ዳይሬክተር የሆነው ፀሀፊ እና ጦማሪ በፈቃዱ ሀይሉ።
 

ፀሀይ ጫኔ
ማንተጋፍቶት ስለሺ

 

Audios and videos on the topic