ኢትዮጵያውያንና ሶማሊያውያን ስደተኞች በየመን | ዓለም | DW | 21.01.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ኢትዮጵያውያንና ሶማሊያውያን ስደተኞች በየመን

በጎርጎሮሳውያኑ 2015 ዓ,ም በርካታ ኢትዮጵያውያንና ሶማሊያውያን በጦርነት ወደ ተመሰቃቀለችው ወደ የመን መግባታቸውን የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን በምህፃሩ «UNHCR» አስታወቀ። ከመካከላቸውም አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን የድርጅቱ ቃል አቀባይ አንድሪያስ ኔድሃም ለዶቼ ቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:35

ኢትዮጵያውያንና ሶማሊያውያን ስደተኞች በየመን

በአደገኛ ጉዞ የመን ለደረሱት ለእነዚህ ስደተኞች «UNHCR» በፀጥታ ችግር ምክንያት አስፈላጊ ርዳታ ሊያደርግላቸው አለመቻሉን ገልፀዋል። የየመኑ ጦርነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ቢሄድም ኢትዮጵያውያንና ሶማሊያውያን ወደ የመን መሰደዳቸው አልቆመም። የተመ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን እንዳስታወቀው ጦርነቱ ተጠናክሮ በቀጠለበት በጎርጎሮሳውያኑ 2015 ዓ,ም፤ 92,446 ስደተኞች የመን ገብተዋል። ከመካከላቸው ሶስት አራተኛው የመን የገቡት ጦርነቱ ከተባባሰበት ካለፈው መጋቢት በኋላ ነው። ድርጅቱ እንደሚለው 82,268 ቱ ማለትም 90 በመቶው ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ የተቀሩት ደግሞ ሶማሌዎች ናቸው። እነዚህ ስደተኞች ጦርነት ወደ ሚካሄድባት የመን የመሰደዳቸው ምክንያት የ «UNHCR» ቃል አቀባይ አንድሪያስ ኒድሃም እንደሚሉት የተለያየ ነው ።
«አብዛኛዎቹ ጥገነት ለማግኘት ወይም በስደተኝነት ለመመዝገብ እና ከ «UNHCR» ርዳታ ለማግኘት አለያም ችግርም

ቢኖር በየመን ወይም በሌላ ሃገር የተሻለ ህይወት ፍለጋ ነው ።»
ያም ሆኖ ቃል አቀባዩ እንደሚሉት አብዛኛዎቹ ስደተኞቹ ወደ የመን የሚጓዙት ሃገሪቱ ስለምትገኝበት ሁኔታ ትክክለኛ መረጃ ሳይዙ ነው።
«አንዳንድ ጊዜ ወደ የመን የሚጓዙ ሰዎች የተሳሳተ መረጃ ነው ያላቸው። በጀልባዎች የሚያሻግሯቸው ሰዎች ከሶማሌላንድ ከፑንትላንድ ከሶማሊያ ወይም ከጅቡቲ ወደ የመን ለመጓዝ ለተነሱ ሰዎች የመን ያለው ሁኔታ ተሻሽሏል፤ ጥሩ ሆኗል ብለው ይነግሯቸዋል። እነርሱ ስለማያውቁ ተታለው ጉዞ ይጀምራሉ።»
«UNHCR» ወደ የመን የሚደረግ ጉዞ፤ ቀድሞም ሆነ አሁን አደገኛ መሆኑን እንደሚያስጠነቅቅ ቃል አቀባዩ ይናገራሉ። በርሳቸው አስተያየት ወደ የመን ለመጓዝ የሚነሱ ሰዎች ራሳቸውን ለሁለት አደጋዎች ነው የሚያጋልጡት።
«UNHCR» እነዚህን ሰዎች የሚያስጠነቅቀው አንደኛ ጉዞው አደገኛ መሆኑን ነው። ጀልባዎቹ ብዙ ጊዜ ይሰጥማሉ። በአሳዛኝ ሁኔታ ከቅርብ ሳምንታት በፊት እንኳን ስደተኞችን የጫኑ ጀልባዎች ሰጥመው የስደተኞች ህይወት ጠፍቷል። ከዚህ ሌላ የመን ከገቡ በኋላም ግጭቱ ተባብሶ እንደቀጠለ በመሆኑ ራሳቸውን ለተጨማሪ አደጋ ያጋልጣሉ።»
ከ13 ቀን በፊት በጀልባ የመን ለመግባት ከሞከሩ 106 ስደተኞች 36 ቱ ሰጥመዋል። በጎርጎሮሳውያኑ 2015 በጉዞ ላይ ጀልባቸው ሰጥሞ 95 ሰዎች ለሞት መዳረጋቸውን «UNHCR» አስታውቋል። ከሞት ተርፈው የመን የሚገቡትም ከባድ ችግር ውስጥ ናቸው።

«ሃራድ ውስጥ 20 ሺህ የሶማሊያ ስደተኞች መጠለያ ነበር ። በግጭቱ ምክንያት ስደተኞች ከመጠለያው ተፈናቅለው ወደ ተለያዩ ከተሞች ሄደዋል። አንዳንዶቹ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ተጠልለዋል «UNHCR» ባለፈው አመት ለ300 ሺህ ሰዎች የመጠለያ ድጋፍ ይሰጥ ነበር ።ሆኖም 2.5 ሚሊዮን ተፈናቃይ ባለበት በየመን ድርጅቱ ለስደተኞች በቂ ድጋፍ መስጠት አልቻለም ።»
በየመን የፀጥታ ችግር ምክንያት UNHCRን የመሳሰሉ ስደተኞችን የሚረዱ ድርጅቶች እንደ በፊቱ ለስደተኞች መድረስ አልቻሉም። ያም ሆኖ UNHCR በሌሎች አጋር ድርጅቶች በኩል ለስደተኞች የተቻለውን እርዳታ ለማቅረብ እንደሚጥር ቃል አቀባዩ አስረድተዋል ።

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic