ኢትዮጵያዊ ሕይወት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በፊትና በኋላ | ኢትዮጵያ | DW | 11.07.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያዊ ሕይወት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በፊትና በኋላ

አገሪቱ በድንገት ከእስር ቤትነት ወደ ነጻ ምድርነት ተሸጋግራለች ማለት ይቻላል። ይህም ብቻ አይደለም። እስር በፍቺ ተተክቷል፤ ስደት በመመለስ ተክሷል። በትርምስ ጫፍ ላይ የነበረች አገር በድንገት ትልቅ ተስፋ አብቦባት ጭራሽ ለቀጠናው ሠላምና መረጋጋት ዓይነተኛ ተጫዋች ሆናለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ቃለ መሐላ ከፈፀሙ እነሆ ዛሬ መቶ ቀን ሞላቸው። አሜርካኖች በክፉ ቀናቸው ከደረሰላቸው ፕሬዚዳንት ፍሬድሪክ ሩዝቬልት ጀምሮ የአዲስ መሪያቸውን መቶ የሥራ ቀናት የሚገመግሙበት ባሕል አላቸው። በአገራችንም ባልተለመደ ሁኔታ ብዙኃን መገናኛዎች ሁሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድን መቶ የሥራ ቀናት አሜሪካኖች የሩዝቨልትን ቀናት በመዘኑበት ስሜት ለመገምገም እየሞከሩ ነው። እኔም በበኩሌ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሐላ ከፈፀሙበት መቶ ቀናት በፊት ወዲህ ያለውን ግዜ፣ ከመቶ የሥራ ቀናቸው ጋር ለማወዳደር ጦማሬን መዘዝኩ። እነሆ ውጤቱ።

ታኅሣስ 18፣ 2010 - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ከመሾማቸው 96 ቀን በፊት በማኅበራዊ ሚድያ ላይ እኔን ጨምሮ ሌሎችም የመብት አራማጆች "ሁሉም የፖለቲካ እና የኅሊና እስረኞች ይፈቱ" የሚል የሞቀ የበይነመረብ ዘመቻ እያደረግን  ነበር። ይሁን እንጂ ዘመቻው እንዲህ ባጭር ግዜ ግቡን ይመታል ብሎ የጠበቀ አልነበረም። ውጤቱ ግን ከተጠበቀው ያለፈበት ረገድ አለ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንበረ ሥልጣኑን በጨበጡ 93ኛው ቀን ላይ ከ70% በላይ የሽብርተኝነት ክሶች መንስዔ የሆኑትን ግንቦት 7፣ ኦነግ እና ኦብነግ “የሽብርተኛ ድርጅትነት" ፍረጃቸው ተሰርዟል፣ አዲስ የፀደቀውን የምኅረት አዋጅ ተንተርሶ። ብዙዎቹ የፖለቲካ እስረኞች የግንቦት ሰባት እና የኦብነግ የጦር መሪዎችን ጨምሮ ተፈትተዋል። የፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶች እና ጋዜጠኞች "እታሰር ይሆን" ስጋት ጠፍቷል።

በርግጥ፣ በታኅሣሥ ወር የተካሔደው የ17ቱ ቀን ጉባዔ ሲያበቃ የገዢው ፓርቲ አባል ድርጅቶች ሊቀ መናብርት "በራሳቸው ጥፋት" የታሰሩ ፖለቲከኞች እንደሚፈቱ እየተግደረደሩ ነግረውን ነበር። ይሁን እንጂ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገና የሹመት ንግግራቸውን ሲያደርጉ ነበር "ለውጥ ፈላጊዎች እና የዴሞክራሲ ኃይሎች ለከፈሉት መስዋዕትነት ይቅርታ እንጠይቃለን" በማለት የመግደርደር ዘመን ማለፉን ያበሰሩት። ይባስ ብሎ፥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰኔ 10  ፓርላማ ቀርበው "በሕዝቡ ይቅርታ አድራጊነት ነው እንጂ አሸባሪዎችስ እኛ ነበርን" ብለዋል። ይህ ንግግር በፊት በምክር ቤቱ አሸባሪዎች ተብለው የተፈረጁትን በደስታ ያስለቀሰ ነበር።

ከወር በፊት ኢሳት እና ኦኤምኤን ቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ማየት በሕግ ያስቀጣ ነበር፤ አገሪቷ በአስቸኳይ ግዜ ዐዋጅ ውስጥ ነበረች። አሁን የኦኤምኤን ቴሌቪዥን ባልደረቦች አዲስ አበባ ቢሮ ከፍተዋል። የኢሳት ቴሌቪዥንም መከተሉ አይቀርም።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመምጣታቸው በፊት እኔና ሌሎች ዐሥር ወዳጆቼ የኮከብ አርማው የሌለው ባንዲራ የተሰቀለበት ድግስ ላይ ተገኝታችኋል ተብለን፥ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለ11 ቀናት ታስረን ነበር። ከሰኔ 16 በኋላ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩን "አበጁ" ለማለት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተደረጉ ሰልፎች ላይ ለአገራችን ሪከርድ የሚሆኑ አርማ የሌለባቸውና በሕግ ታግደው የነበሩ ባንዲራዎች በአደባባይ ተውለበለቡ። ይህ ሲሆን በመንግሥት በጀት በሚተዳደሩ ሚድያዎች ተሰራጩ።

ከሳምንታት በፊት ወደ ኤርትራ ስልክ መደወል አይቻልም ነበር። ሐምሌ 1 ቀን ግን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአስመራን ሰማይ ደፍሮ ሰነጠቀው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኤርትራ ፕሬዚደንት ጋር እጅ ለእጅ ተጨባበጡ። ከሁለት ዐሥርት ዓመታት በኋላ ሁለቱ መንግሥታት በመልካም ስሜት ተነጋገሩ። ሕዝቦቻቸውም ከ17 ዓመታት በኋላ በቀጭኑ ሽቦ ለመደዋወል በቁ።

ልዩነቱ ጉልህ ነው…

ከኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ትዕይንት ለስድስት ወራት ተሰውሮ የቆየ ሰው ድንገት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ሆነ ቢሉት ለማመን ይቸገራል። አገሪቱ በድንገት ከእስር ቤትነት ወደ ነጻ ምድርነት ተሸጋግራለች ማለት ይቻላል። ይህም ብቻ አይደለም። እስር በፍቺ ተተክቷል፤ ስደት በመመለስ ተክሷል። በትርምስ ጫፍ ላይ የነበረች አገር በድንገት ትልቅ ተስፋ አብቦባት ጭራሽ ለቀጠናው ሠላምና መረጋጋት ዓይነተኛ ተጫዋች ሆናለች። ከወራት በፊት አመፅ ብቻ የሚያስተናግዱ አደባባዮች፥ ዛሬ የድጋፍ ሰልፍ እያስተናገዱ ነው። ድንገት "ፖለቲካን በሩቁ" ይሉ የነበሩ በሙሉ፥ "ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬስ ምን አሉ?" ወደሚል ተሸጋግረዋል። ቀድሞ እንደ ፕሮፓጋንዳ ማሽን ይቆጠሩ የነበሩ የመንግሥት ብዙኃን መገናኛዎች፥ እንደ ‘ሶጵ ኦፔራ’ በጉጉት የሚከታተላቸው በዝቷል። ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ሹመት በፊት የነበረው ስጋት እና ፍርሐት፥ በተስፋ እና ደስታ የብዙኃኑን ቤት አንኳኩቷል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ መቶ ቀናት በጣም ፈጣን፣ በአስገራሚ እመርታዎች የታጀበ ቢሆንም ትችቶች አልቀረቡበትም ማለት አይደለም።  በተለይ እዚህም እዚያም የታዩት ማንነትን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች እና የዜጎች ከቀዬ መፈናቀል ተባብሶ መቀጠል እመርታቸው ላይ ጥላሸት አኑሮባቸዋል። ይሁን እንጂ እርሳቸው ከመምጣታቸው በፊት ኢትዮጵያ የነበረችበትን ለሚያስታውሱ፥ መቶ የሥራ ቀናቶቻቸው በደማቅ የስኬት ቀለም የተጻፉ ናቸው።

በፍቃዱ ዘኃይሉ