ኢትዮጵያዊቷ ስነ-ፈለክ ተመራማሪ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 08.02.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ኢትዮጵያዊቷ ስነ-ፈለክ ተመራማሪ

ኢትዮጵያዊቷ ሣይንቲስት ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በሚገኝው የቪትስ ዩኒቨርሲቲ ብቸኛዋ ሴት የስነፈለክ ተመራማሪ ናቸው። ናሚቢያ በሚገኝ የምርምር ተቋም ውስጥም ጥናታቸውን ያኪያሂዳሉ። ድኅረ ዶክትሬት ጥናታቸውን አጠናቀውም ሌላ ምርምር በማከናወን ላይ ይገኛሉ፦ ዶክተር ነቢሃ በድሩ ሻፊ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:33

ኢትዮጵያዊቷ አስትሮ ፊዚክስ ሣይንቲስት

በአስትሮፊዚክስ ዘርፍ የዶክትሬት ጥናታቸውን ሲያጠናቅቁ በተማሩበት ተቋም ብቸኛዋ ሴት ተመራማሪ ነበሩ። ኢትዮጵያዊቷ ምሁር ዶክተር ነቢሃ በድሩ ሻፊ። ለሁለት ዓመት የተከታተሉትን ድኅረ ዶክትሬት ጥናታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ እዛው ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ምርምራቸውን ቀጥለዋል።

በቪትቫተርስራንድ ዩኒቨርሲቲ እና ከጆሐንስበርግ ከተማ ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ሐርትቢስቶክ ራዲዮ አስትሮኖሚ መቃኛ ተቋም ላይም ምርምር የሚያከናውኑ ብቸኛዋ ሴት የስነ-ፈለክ ሊቅ ናቸው። ከዓመታት በፊት በአንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የፊዚክስ ትምህርት ክፍል ለመግባት ባመለከቱበት ወቅት የተከሰተውን ዛሬም አይረሱትም። የትምህርት ክፍሉ ዲን እንዲህ ነበር ያሏቸው፦ «ምነው ልጄ፤ ግማሽ ዓመት ለማትዘልቂው እንዲህ መጣደፍ»። ዛሬ ኢትዮጵያዊቷ አስትሮ ፊዚክስ ተመራማሪ ሩቅ፤ ሲበዛ ሩቅ ተጉዘዋል። ኢትዮጵያዊቷ ሥነ-ፈለክ ተመራማሪ ዶክተር ነቢሃ በድሩ ሻፊ ናሚቢያ ውስጥ ከ250 በላይ ዓለም አቀፍ ሳይንቲስቶች ምርምር በሚያኪያሄዱበት ተቋም ዛሬም ተጨማሪ ጥናታቸውን ያከናውናሉ። ዋነኛ ጥናታቸው የከዋክብት ክምችቶች፦ ማለትም ጋላክሲዎች ላይ ነው።
 
ተወልደው ያደጉት፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውንም የተከታተሉት ደቡብ ኢትዮጵያ አላባ (ሐላባ) ነው። ዛሬ የሚገኙበት ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ላይ ለመድረስ የኖሩበት ማኅበረሰብ የኑሮ ዘዬ፣ የሀገሪቱ የትምህርት አሰጣጥ ብሎም ሌሎች ውጣ ውረዶችን ማሳለፍ ነበረባቸው። ሁሉንም ታዲያ በአንድ ወቅት በመጽሐፍ መልክ ማሳተም ይፈልጋሉ። በ1990 ዓ.ም. የከፍተኛ ትምህርት ጥናታቸውን ከጀመሩበት ከመምኅራን ኮሌጅ አንስቶ የነበረውን ውጣ ውረድ እንዲህ መለስ ብለው ይቃኛሉ።

ዶክተር ነቢሃ በደቡብ አፍሪቃው ግዙፉ ሚርካት (MeerKAT) አጉልቶ መመልከቺያ መነጽር (ቴሌስኮፕ) ፕሮጀክት ውስጥ በአሁኑ ወቅት አሉ ከሚባሉ ተመራማሪዎች መካከል አንዷ ናቸው። ሚርካት ቴሌስኮፕ  ከ10 ወራት በኋላ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ 64 የሬዲዮ አንቴናዎች የተገጠመላቸው ትልልቅ ሳህኖችን የሚያካትት ግዙፍ ፕሮጀክት ነው።

በዚህ ማዕከል ኅዋው ላይ በሩቅ ተዘርግተው የሚገኙ 13 የተለያዩ የከዋክብት ክምችቶችን (ጋላክሲዎችን) በቀላሉ መመልከት ይችላል።  ዶክተር  ነቢሃ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አራት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ በፊዚክስ ትምህርት ክፍል ሲከታተሉ ነበር ከአድማሱ ወዲያ የተዘረጋው ሰማይ ከነከዋክብቱ የማረካቸው። 

ዶክተር ነቢሃ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳሉ ከሚያውቋቸው ዶክተር ያብባል ጋር በመሆን የፊዚክስ ማኅበር ሲያቋቁሙ፤ በወቅቱ የነበሩትን የከዋክብት መመልከቺያ መነጽሮችም አሳድሰው ሲጠቀሙ ጉዞዋቸው ወዴት እንደሆነ ግን አያውቁም ነበር። የሳቸው ለተጨማሪ ጥናት ወደ ደቡብ አፍሪቃ ማቅናት ግን ለዶክተር ያብባል ሌላ መነቃቃት ነበር።

በኢትዮጵያ እንደ ዶክተር ነቢሃ ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ ሴት ተመራማሪዎች ቁጥር እጅግ ዝቅተኛ ነው። የትምህርት ሚንስትር ድረ-ገጽ መረጃ በኢትዮጵያ ለዶክትሬት ዲግሪ ጥናታቸው በ2007 ዓ.ም. ከተመዘገቡ 3,135 ተማሪዎች መካከል የሴቶች ቁጥር 380  ብቻ እንደነበር  ይጠቅሳል።  

መጋቢት 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ጊዮን ሆቴል ውስጥ የቀረበው የፕሮፌሰር ጽጌ ገብረማርያም ጥናታዊ ጽሑፍ ደግሞ የትምኅርት እርከኑ ከፍ እያለ በሄደ ቁጥር የሴቶች ቁጥር እያነሰ እንደሚያንስ ይገልጣል። ይኽን ኹኔታ ፕሮፌሰር ጽጌ «የተሸነቆረ ቧንቧ» ይሉታል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በሞያ ተዋረድ ሴቶች ዝቅተኛ መደቦች ላይ እንዲከማቹ መደረጋቸው እንደሆነ ይጠቁማሉ።

ሴቶች በብዛት ጠጠር ካሉት እንደ ፊዚክስ እና ምሕንድስና የትምህርት ዘርፎች ይልቅ ላላ ወዳሉት ባዮሎጂን ወደመሳሰሉ የትምህርት ዘርፎች በከፍተኛ ደረጃ መሰብሰባቸው ሌላው ምክንያት ነው ይላሉ ፕሮፌሰር ጽጌ።   

«የኅዋ ሳይንስ» የተሰኘ የሬዲዮ ፕሮግራም ለአምስት ዓመታት ግድም ያዘጋጁ የነበሩት ዝነኛው ኢትዮጵያዊ የአስትሮ ፊዚክስ ምሁር ዶክተር ለገሰ ወትሮ ጠጣር በሆነው የሳይንስ ዘርፍ ሴቶች በብዛት አለመኖራቸውን ይጠቅሳሉ።

የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳሉ በ9ኛ ክፍል የፊዚክስ መምኅራቸው አቶ ዘውዱ ታፈሰ እገዛ የፊዚክስ ፍቅር ያደረባቸው ዶክተር ነቢሃ ዛሬ ለደረሱበት የቤተሰብ አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበር ይጠቅሳሉ። 

«የትምህርት መጨረሻ የለውም እንደውም ብዙ እያወቅህ በሄድ ቁጥር ይበልጥ አለማወቅህ ይገለጥልሃል» ያሉት ዶክተር ነቢሃ በድሩ ሻፊ ከድኅረዶክትሬት ባሻገር ተመራማሪ ሆነውም «ገና መች ተጀመረና» ይላሉ።

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምፅ ማጫወቻውን ይጫኑ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic