ኢትዮጵያዉያን፤ ስደት፤ ስደተኞችና መከራቸዉ | አፍሪቃ | DW | 17.07.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

   ኢትዮጵያዉያን፤ ስደት፤ ስደተኞችና መከራቸዉ

ሰደተኞች፤ የሰደተኞቹ ልጆች የየተሰደዱበት ሐገርና ሕዝብም «የእልፍ ሲሉ እልፍ» ይገኛል ዉጤት መሆናቸዉ የሚነገር-የሚመሰከርበት የዚሕ ዘመን ፖለቲከኛ የዘመኑን ስደተኛን አይንሕ ላፈር ማለቱ እንጂ  ሰቀቀኑ።የሳዑዲ አረቢያ ነገስታት የተለዩ አይደሉም።እርምጃቸዉ ግን ጠንክሯል።የኢትዮጵያዉኑ ስደተኞች መከራም ከፍቷል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:38

ሌላዉ ቀርቶ የማስታወቂያ ሙያቶች  ሐገራችን «ምን ጠፍቶ» እያሉ ስደተኛዉ ሐገሩ እንዲገባ ጠርተዉታል።መጣ።ግን ማን ምን አደረገለት?

አዉሮጶች እንደሚወገዙ፤እንደሚወቀሱባቸዉ ብዙ ነገሮች ሁሉ የሚደነቁ፤የሚመሰገኑባቸዉ አያሌ መርሕ፤ እርማጃዎች አሏቸዉ።ለልጅ የሚያደርጉትን አለማወደስ ግን በርግጥ አይቻልም።አብዛኞቹ የአዉሮጳ መንግሥታት ለልጅ ገንዘብ ይከፍላሉ።የሳዑዲ አረቢያ ነገሥታት በቅርቡ የነደፉት ዕቅድ እስከ 2030 (እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ባለዉ ጊዜ ሐገር-ሕዝባቸዉን እንደ አዉሮጳ ለማዘምን ያለመ ነዉ ይላሉ።እኩልነትን፤ለደካሞች አዘኔታን፤ለድሆች እርዳትን የሚሰብከዉ ትልቅ ሐይማኖት የፈለቀባት ሐገር ነገስታት ሐገርን በማዘመን ስም እመጫት፤እርጉዝ፤በሽተኛ አዛዉንትን ሳይቀር ስደተኛን በገፍ ያባርራሉ።ለማባረር ምክንያት ያጡለትን በየልጁ ቁጥር ልክ ገንዘብ ያስከፍላሉ።የሪያዶች እርምጃ መነሻ፤ የኢትዮጵያዉን ስደተኞች አበሳ መድረሻችን ነዉ። 

                            

ሁለቱ፤ ዛሬ እንጂ ያኔ የአንድ ክፍለ-ግዛት፤ የአንድ ዘመን ዉልድ፤ ግን የማይተዋወቁ የቅርብ-ሩቅ ልጆች ነበሩ።አንደኛዉ የሙዚቃ ፍቅር፤ጥማቱን ሌላዉ በርትቶ የመስራት ፍላጎቱን ለማርካት፤ ሁለቱም እኩል ኑሮን የመለወጥ ዓላማን ለማሳካት የመጀመሪያዉ ቀድሞ፤ ሁለተኛዉ ተከትሎ፤ ቀዳሚዉ ከየጁ አዲስ አበባ፤ ተከታዩ ከወልዲያ ጂዳ ገቡ።

ከኢንተርኔት በቃረምነዉ መረጃ መሠረት በ1960ዎቹ ከየጁ አዲስ አበባ የገባዉ ከኢትዮጵያ እዉቅ ድምፃዉያን አንዱ ለመሆን

ጊዜ አልፈጀበትም።ሥም፤ አያሌዉ መስፍን።በዚያዉ ዘመን ከወልዲያ ጂዳ የገባዉ ወጣት ዛሬ አዱኛ ከሰገደችላቸዉ የዓለም ጥቂት ቱጃሮች አንዱ ናቸዉ።ሼኽ መሐመድ ሁሴይን አሊ አል አሙዲ።

እርግጥ ነዉ ድምፃዊዉ «ብቸኛ ነኝ» ባለዉ ዜማዉ «ካገራችሁ ሳታዉቁ እንዳትወጡ» ማለቱን ያስተወለ «ተሰድዶ ከመሳደድ የያዝኩትን ጠበቅ ብሎ-ያለዉን አድርጎት ይሆን-ይሆናል።ስም ዝናዉ የገነነዉ ድምፃዊ ካዜመዉ ይልቅ እሱ እና መሐመድ ሁሴይን ያደረጉትን፤ ከነበሩበት ይበልጥ የደረሱበትን ያየ-የሰማ ግን በ«እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል» ብሒል እየተፅናና ኑሮን ለማሻሻል ስደትን ሙጥኝ ቢል በርግጥ «አበጀሕ» እንጂ ሌላ ሊባል አይችልም።

ጂዳ-ሳዑዲ አረቢያ የሚኖሩ አንድ ኢትዮጵያዊ እንዳሉት ከ1980ዎቹ ጀምሮ በጣሙን ወደ አረብ ሐገራት በጥቂቱ ወደ አዉሮጳና አሜሪካ የሚሰደደዉ አብዛኛዉ ኢትዮጵያዊም ሰርቶ ከመኖር ዘመድ ወዳጆቹን ከማኖር ያለፈ ዓላማ ፍላጎትም የለዉም።

                                    

ከሔንሪ ወይም ሐይንስ አል ፍሬድ ኪሲንጀር እስከ ማድሊን ወይም ማሪ ጃን ኮርቤሎቭ አል ብራይት ያሉ እዉቅ የአሜሪካ ዲፕሎማቶች ስደተኞች ናቸዉ።ዴቪድ ቤን ጎሪዮን ወይም ግሩን እና የዓላማ ተጋሪዎቻቸዉ

ከአዉሮጳ ወደ ፍልስጤም ባይሰደዱ ኖሮ የዛሬዋን ጠንካራ እስራኤልን ማሰብ ዚበዛ ከባድ ነዉ።

 ባራክ ኦባማ እና  ዶናልድ ትራምፕ ለዩናይትድ ስቴትስ፤ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ለዓለም ካቶሊኮች፤ ሚካኤል ኢሊያስ ቴመር ለብራዚል የሠሩና የሚሰሩት ጥሩ ወይም መጥፎ ሊሆን ይችላል።ሁሉም የየሚወክሉትን ሕዝብ የመሩና የሚመሩ ናቸዉ።ሁሉም የስደተኞች ልጆች ናቸዉ።

ሰደተኞች፤ የሰደተኞቹ ልጆች የየተሰደዱበት ሐገርና ሕዝብም «የእልፍ ሲሉ እልፍ» ይገኛል ዉጤት መሆናቸዉ የሚነገር-የሚመሰከርበት የዚሕ ዘመን ፖለቲከኛ የዘመኑን ስደተኛን አይንሕ ላፈር ማለቱ እንጂ  ሰቀቀኑ።የሳዑዲ አረቢያ ነገስታት የተለዩ አይደሉም።እርምጃቸዉ ግን ጠንክሯል።የኢትዮጵያዉኑ ስደተኞች መከራም ከፍቷል።

                          

በ2013  ሪያድ ዉስጥ በሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንና በከተማይቱ ወጣቶች መካከል በተከሰተ ግጭት ቢያንስ ሁለት ኢትዮጵያዉያን ተገድለዉ ብዙ ቆስለዋል፤ ሌሎች ታስረዉ ነበር።

በዚያ ዓመት የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ሕገ-ወጥ ያላቸዉን ከ3 እስከ 5 ሚሊዮን የሚደርሱ የዉጪ ሐገር ዜጎችን በጅምላ ወደየሐገራቸዉ አባርሯል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚገምተዉ ያኔ 2 መቶ ሺሕ ያኽል ኢትዮጵያዉያን ወደ ሐገራቸዉ ተመልሰዉ ነበር።

ዘንድሮ በተከፈተዉ ዘመቻም ሰባ ሺሕ የሚገመት ኢትዮጵያዊ  ወደ ሐገሩ ተመልሷል።ዘመቻዉ እስካሁን ያልተመለሰዉንና ሕጋዊ መኖሪያ ፍቃድ ወይም ኢጋማ ያለዉን ኢትዮጵያዊ ኑሮም አዉኮታል።

                             

በሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ደንብ መሠረት ሕገ-ወጥ የሚባሉት 1 ሚሊዮን የሚደርሱ የዉጪ ዜጎች እስከ ያዝነዉ ወር ማብቂያ ድረስ መዉጣት አለባቸዉ።ሕጋዊ የሚባሉት ደግሞ ለባለቤታቸዉ እና ለልጆቻቸዉ በነብስ ወከፍ በየወሩ መቶ ሪያል መክፈል ግዱ ነዉ።ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ እንደሚለዉ ግብሩ እና አከፋፈሉ በየትኛዉም ደረጃ ለሚኖር ኢትዮጵያዊ ስድተኛ የሚቻል አይደለም።

                                        

ስማቸዉ እንዲጠቀስ ያልፈለጉት ኢትዮጵያዊ እንደሚሉት ደግሞ ግብሩ የመኖሪያ ፍቃድ በሚታደስበት ጊዜ ሁሉ እየጨመረ የሚሔድ ነዉ።እስካሁን ሕገ-ወጥ በሚባሉት የዉጪ ዜጎች ላይ ያረፈዉ የሳዑዲ አረቢያ ጠንካራ ሕግ ሕጋዊ የሚባሉትንም ተስፋ እያቀጨጨዉ ነዉ።ካነጋገርናቸዉ ኢትዮጵያዉያን አንዱ እንዳሉት የቻለ ይከፍላል

።ያልቻለ ከሚስትና ልጆቹ ይነጠላል።ሌለኛዉ ግን አማራጩ ጠቅልሎ ሐገር መግባት ነዉ ባይ ናቸዉ።ግን የኢትዮጵያ መንግሥትን ይማፀናሉ-ምናለበት እንደ ሱዳን እንኳን ቢሆን እያሉ።እሳቸዉ አከሉበት።እኚሕኛዉ ደግሞ ሳዑዲ አረቢያዎች ስደተኛዉን አልፈለጉትም ይላሉ።ጋዜጠኛ ነብዩም ተመሳሳይ አስተያየት መስማቱን ነግሮናል።

                             

እልፍ ሲሉ እልፍን ተመኝቶ ካገሩ የወጣዉ ኢትዮጵያዊ ከሰሐራ በረሐ እስከ ደቡባዊ አፍሪቃ ዱር ጉራንጉር፤ ከሜድትራንያን ባሕር እስከ አደን ባሕረ-ሠላጤ ሲረግፍ ኢትዮጵያዊዉ አልቀሳሏል።ያለቅሳልም።አሸባሪዎች ሲገድሉት ባደባባይ አርግዷል።ሥለ ስደት አስከፊነት ገጣሚዉ ተቀኝቶበታል።፤ደራሲዉ መፅሐፍ አሳትሞበታል።ድምፃዊዉ አንጎራግሯል።የመንግሥት ሹመኛዉ «ደላላ» እያለ የሚያወግዛቸዉን ቀጥቷል።ሌላዉ ቀርቶ የማስታወቂያ ሙያቶች  ሐገራችን «ምን ጠፍቶ» እያሉ ስደተኛዉ ሐገሩ እንዲገባ ጠርተዉታል።መጣ።ግን ማን ምን አደረገለት? «ምንም» ባዮች እንደገና ተሰደዱ። ቸር ያሰማን። 

                                 

ነጋሽ መሐመድ 

አዜብ ታደሰ

 

 

 

Audios and videos on the topic