ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች ከየመን ተመለሱ | አፍሪቃ | DW | 02.05.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች ከየመን ተመለሱ

በህገ ወጥ መንገድ ወደ የመን የገቡ  ኢትዮጵያዉያን  ስደተኞችን ወደ ሀገራቸዉ መመለሱን አለም ዓቀፉ የስደተኞች መርጃ ድርጅት IOM አስታወቀ። ስደተኞቹ ወደ ሀገራቸዉ እንዲመለሱ የተደረገዉ በፈቃዳቸዉ መሆኑን ድርጅቱ ገልጿል።  

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:40

«በሚያዚያ ወር ብቻ 113 ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች ከየመን ተመልሰዋል።»

 
በኢትዮጵያ የሚገኘዉ  ድርጅቱ  ቅርንጫፍ ፤ ስደተኞቹን መቀበሉን ገልፆ መልሰዉ የሚቋቋሙበትን መንገድ እየፈለገ መሆኑን አመልክቷል። 
በየመን የድርጅቱ  ሚዲያና የኮሚንኬሽን መኮንን ሚስተር ሳባ ማላሚ  ከሰንዓ ለዶቼ ቬለ እንደገለፁት ስደተኞቹ የተጓጓዙት ደቡብ የመን በምትገኜዉ  ኤደን  ከተማ   በኩል ነዉ።ስደተኞቹ ወደ ኢትዮጵያ  ከመግባታቸዉ በፊትም  ጅቡቲ የሚገኜዉ የድርጅቱ ቡድን ለተመላሽ ስደተኞቹ ትብብር ማድረጉን ሀላፊዉ አመልክተዋል።ቀደም ሲል ስደተኞች በምዕራብ የሀገሪቱ ክፍል በሚገኜዉ «ሆዲዳህ» በተባለዉ ወደብ በኩል ይጓጓዙ የነበረ ሲሆን  በኤደን በኩል  ሲጓጓዙ እነዚህ  የመጀመሪያወቹ መሆናቸዉ ተገልጿል። ጉዞዉ የተከናወነዉ ስደተኞቹ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት  መሆኑንም ሀላፊዉ አመልክተዋል።
« ለመመለስ ጥያቄዉን አቀረቡ ። ታዉቃላችሁ ሰዎች በፈቃደኝነት የሚመለሱበት የ IOM መርሃ ግብር አለን።ስለዚህ ስደተኞቹ ወደ IOM ከመጡና ወደ ሀገራቸዉ ለመመለስ ከጠየቁ እንረዳቸዋለን። ስደተኞችን በግዳጅ መመለስ የመንግስት ጉዳይ ነው። እኛ ደግሞ የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅት ነን ፣ ስለዚህ ስደተኞችን የመመለሱ ነገር በፈቃደኝነት ነዉ መሆን ያለበት። ጉዞዉን የተሳካ ለማድረግ ግን ለመመለስ  ፈቃደኛ መሆናቸዉን እና IOM እንዲረዳቸው መፈለጋቸውን የሚገልጽ ሰነድ ላይ መፈረም አለባቸዉ።»

አብዛኛወቹ የኢኮኖሚ ስደተኞች መሆናቸዉን የተናገሩት ሚስተር ሳባ አንዳንዶቹ የመን የኖሩ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ የተሻለ ስራና ኑሮ ፍለጋ  ወደ ሳዉዲ አረቢያ ፣የተባበሩት አረብ ኢሜሬትስና ኦማን መሳሰሉ የባህረ ሰላጤ ሀገራት ለመሻገር በመጠባባቅ ላይ የነበሩ ናቸዉም ብለዋል።  ተመላሾቹ  በችግር ላይ ይገኙ የነበሩ በመሆናቸዉም ለጉዞ የሚያስፈልጋቸዉን  ነገሮች ከድርጅቱ ማግኜታቸዉንም ኃላፊው አብራርተዋል። 
«ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት እና በኋላ እንዲሁም ሲደርሱ፤ ምግብ እና የመድህኒት እርዳታ ብቻ ሳይሆን የምናቀርብላቸው፤ የህክምና አገልግሎትና የጤንነት ምርመራ እናደርግላቸዋለን። ይህ የተባባሩት መንግስታት የሰብዓዊ እርዳታ እንቅስቃሴ ነዉ ።ደረጃዉን ባሟላ ሁኔታ ደህንነታቸዉ ተጠብቆ መጓዝ አለባቸዉ።ምግብ መቅረብ አለበት።ዉሃ መቅረብ አለበት።በተሟላ ሁኔታ መጓዝ አለባቸዉ።»


በትናንትናዉ ዕለትም ስደተኞቹ ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸዉን የዓለም ዓቀፉ የስደተኞች ድርጅት የኢትዮጵያ ቃል አቀባይ  አቶ አለማየሁ ሰይፈስላሴ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።እነዚህን ጨምሮ በጎርጎሮሳዉያኑ የሚያዚያ ወር ብቻ ከመቶ በላይ ኢትዮጵያዉያን ከየመን መመለሳቸዉን አረጋግጠዋል።
«ባለፈዉ ሳምንትም የገቡ አሉ።ከዚያም በፊት የገቡ አሉ።እና በአጠቃላይ 113 ናቸዉ።እንግዲህ ኢትዮጵያዉያን   «ፓርቲኩላርሊ« ከየመን ተመልሰዉ የገቡት።»ይህ ቁጥር የሚያዚያ ወር ብቻ  ነዉ ካሉ በኋላ ከነዚህ ዉስጥ 28ቱ ሴቶች መሆናቸዉን ነዉ የተናገሩት።
እንደ አቶ ዓለማየሁ ካለፈዉ ጥር  እስከ ሚያዚያ፣ 2010 ዓም  ድረስ  837 ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች ከተለያዩ የአፍሪቃ ሀገሮችና ከየመን  የተመለሱ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ሳዉዲ አረቢያ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞችን መመለስ ከጀመረች ካላፈዉ ጥቅምት ወዲህ  ከተለያዩ ሀገራት ከ150 ሺህ የሚበልጡ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች ወደ ሀገራቸዉ ገብተዋል። እነዚህን ወገኖች መልሶ ለማቋቋምም ከፍተኛ በጀት ስለሚያስፈልግ፣ ይህ አስቸጋሪ መሆኑን ገልፀዋል፤ ያም ሆኖ ግን በድርጅቱ በኩል ወደሀገር ከተመለሱት መካከል የተወሰኑትን ለመርዳት ድርጅቱ  ጥረት እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
«እንግዲህ ምንድነዉ መልሶ ማቋቋም ከባዱ ስራ እሱ ነዉ።ምክንያቱም ብዙ ሰዎች ናቸዉ ።ከፍተኛ በጀትም ነዉ የሚጠይቀዉ።እሱን ለማድረግ አሁን በተወሰነ መልኩ ስራ ጀምረናል።በስልጠና ፣«በማቴሪያል»፣በገንዘብና  እንዲሁም በመንግስት በኩል ደግሞ የሚደረገዉ የመስሪያ ቦታወች እንዲኖሯቸዉ ለማድረግ ያዉ ቦታወችን ለማመቻቸት ጥረት ይደረጋል።» በማለት ነዉ የገለፁት።
እንደ ዓለም ዓቀፉ የስደተኞች ድርጅት IOM በጎርጎሮሳዉያኑ 2017 ብቻ ወደ 87 ሺህ የሚጠጉ የአፍሪቃ ቀንድ ስደተኞች ባህር አቋርጠዉ ከጎርጎሮሳዉያኑ 2014 ጀምሮ በጦርነት ውስጥ ወደምትገኘው የመን ተሰደዋል። በ2018ም  ቢሆን አዳዲስ ከሚመጡ ስደተኞች አንፃር ቁጥሩ ቢጨምር እንጅ ሊቀንስ እንደማይችል ነዉ ድርጅቱ ያመለከተዉ። በየመን አፍሪቃዉያኑ ስደተኞች  በጦርነቱ ሳቢያ ከሚያጋጥማቸዉ ችግር በተጨማሪ በርካታ  የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈፀመባቸዉ መሆኑንም ዓለም ዓቀፉ የሰብዓዊ ድርጅት ሂዉማን ራይትስ ዎች ከጥቂት ጊዜ በፊት መግለጹ የሚታወስ ነው። 


ፀሐይ ጫኔ 
አርያም ተክሌ

 

 

Audios and videos on the topic