ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች በ«አክስት አገር ዩጋንዳ»
ሐሙስ፣ መስከረም 16 2017ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች በ«አክስት አገር ዩጋንዳ»
«በዩጋንዳ ዉስጥ እቁብ አላቸዉ ። ከኢትዮጵያ ጋር የሚያመሳስላቸዉ። ሳኮ የሚባል ነገር አለ፤ ሴቶች አንድ ላይ ተሰብስበዉ እቁብ ያደርጋሉ። በዩጋንዳ ካየሁት እና ካስደነቀኝ ነገር፤ ሴቶች በየሳምንቱ በጋራ በመሆን እቁብ ይሰበስባሉ። የሚሰበስቡት የገዘብ መጠን እራሳቸዉ እንደተስማሙበት ነዉ። በየሳምንቱ አንድ ጊዜ ዉስጥ ወይም ዛፍ ጥላ ስር ይሰበሰቡና ፤ ለቸገረዉ አልያም ገንዘብ ለሚፈልግ በቅድምያ እየሰጡ እቁቡን ይጨርሳሉ። ይህ ዩጋንዳዉያን ከኢትዮጵያዉያን ባህል ጋር የሚያመሳስላቸዉ ነገር ነዉ። ብዙ የምንመሳሰልበት ነገሮችም አላቸዉ።» ስትል የገለፀችልን ጋዜጠኛ እንግዳወርቅ ተፈራ ትባላለች።
ጋዜጠኛ እንግዳወርቅ ተፈራ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በተለይ በቲክቶኩ ዓለም አክስት አገር ዩጋንዳ በሚል ነዉ የምትታወቀዉ። ዩጋንዳ ኢትዮጵያዉያን አሁን አሁን የሚሰደዱባት ሃገር ሆናለች፤ ኤርትራዉያንም ብዙ አሉ፤ ሰላማዊ ሃገር ናት ስትል ነዉ፤ ጋዜጠኛ እንግዳወርቅ ተፈራ ዩጋንዳን የምትገልጻት። መሸሸግያ ማኩረፍያም ስለሆነችን አክስት አገር ብያታለሁ ስትል አጫዉታናለች።
በቲክቶኩ ዓለም አክስት አገር ዩጋንዳ በሚል መረጃን የምታጋራዉ ጋዜጠኛ እንግዳወርቅ ተፈራን እስቲ ስለ ዩጋንዳ ባህል፤ እዝያ ስለሚኖሩ ኢትጵያዉያን አጫዉችን ስንል ጥያቄ ባቀረብንላት ወቅት በደስታ ስትል ነበር ቀጠሮ በቅስበት የሰጠችን። በቀጠሮዉ መሰረት ከቀናቶች በኋላ በስልክ ደዉለን አገኘናት። በመጀመርያም ለጋዜጠኛ እንግዳወርቅ ያቀረብንላት ጥያቄ አክስት አገር ዩጋንዳ ልምን አልሻት ስንል ነበር ቃለ ምልልሳችንን የጀመርነዉ።
« ብዙ ሰዎች ናቸዉ ፤ ለምን አክስት አገር ዩጋንዳ ሲሉ ጥያቄ የሚያቀርቡት። በባህላችን በቤታችን ዉስጥ የማዉቀዉ አክስት ማክረፍያ መሆንዋን ነዉ። እናትሽ አባትሽ ቤት በሆነ ነገር ቅሪታ ሲፈጠር የምታኮርፊበት የመጀመርያዉ ቦታ አክስት አጎት ቤት ነዉ የሚኬደዉ። አክስት ማኩረፍያ ናት። ጥሩ አክስት ከሆነች ደግሞ ፤ ከቤተሰቦችሽ ቤት የበለጠ ተመችቶሽ እንድትኖሪ፤ ያንን የኩርፍያሽን ጊዜ የከፋሽን ጊዜ እንድታሳልፊ እንድትረሽ ጉልበት እንድታገኚ ታደርጋለች። እና እኔም ለጊዜዉ በአገሪ በኢትዮጵያ የሚመች ሁኔታ ስላልነበረ ነዉ ፤ ተሰድጄ ወደ ዩጋንዳ የመጣሁት። እና ዩጋንዳን የአክስት ቤት ሆና ነዉ ያገኘኋት። ከዝያ ተነስቼ ነዉ አክስት አገር ዩጋንዳ ያልኳት። ዩጋንዳ ስኖር አንዳንድ ጊዜ አገር የቀየርኩ ሁሉ አይመስለኝም ። የሆነ ክፍለሃገር ያለሁ ሆኖ ነዉ የሚሰማኝ። ይህን ስሜቴን ከገለፀልኝ ብዩ ነዉ አክስት አገር ዩጋንዳ ያልኳት።»
ኢትዮጵያዉያን በዩጋንዳ ብዙ አሉ ማለት ነዉ?
« አዎ፤ ዩጋንዳ ስደተኞችን ከሚቀበሉ አፍሪቃ ሃገራት አንዷ ናት። ዩጋንዳ በጣም ሰላማዊ ሃገር ናት። ከዝያ ባለፈ ለስደተኞች ምቹ ናት። በቅርቡ UNHCR ያወጣዉን መረጃ እደተከታተልኩት፤ በአጠቃላይ በዩጋንዳ የሚገኙ አፍሪቃዉያን ስደተኞች ቁጥር ፤ አንድ ሚሊዮን ሰባት መቶ አርባ አንድ አካባቢ ነዉ። በዩጋንዳ የሚገኙ የኢትዮጵያዉያን UNHCR የመዘገባቸዉ ስደተኞች ቁጥር 13,933 ናቸዉ። በዩጋንዳ የሚኖሩ ኤርትራዉያን ስደተኞች ቁጥር ደግሞ ወደ 55,000 መሆኑን UNHCR ከአንድ ወር በፊት ያወጣዉ መረጃ ያመለክታል። ዋናዉ ነገር ዩጋንዳ ለስደተኞች ምቹ ሃገር ናት። ዩጋንዳ ዉስጥ አንድ ስደተኛ ዜጋዉ ያለዉ መብት ሁሉ ነዉ ያለዉ። በተለይ ስደተኛ የሚል ወረቀት አሟልቶ ከተገኘ ልክ እንደዜጋዉ በሙሉ መብት መንቀሳቀስ መስራት፤ ቤት መግዛት መሸጥ፤ይችላል። በዚህም ይመስላል ፤ ብዙ ስደተኞች ይሄንን አገር እየመረጡት ነዉ። ወደ ሌላ አገር ለመሻገርም ዩጋንዳን እየመረጡ ነዉ።
ህዝቡስ ምን ያህል እንግዳ ተቀባይ ነዉ ስደተኞችንስ ምንም አይልም?
« ዩጋንዳዉያን በጣም ሰላማዊ ሰዎች ናቸዉ። ትልቁን ዩጋንዳን ተመራጭ የሚያደርጋት በደቡብ አፍሪቃ እንደሚታየዉ ጥላቻ ዝርፍያ ጥቃት ባለመኖሩ ነዉ። አንድ ስደተኛ ህጉን ጠብቆ ሥነ-ስርዓት ይዞ ከኖረ በሰላም ይኖራል። እዚህ ላይ እኔ እንደችግር ነዉ ብዬ የማየዉ፤ አበሻዉ አንድ አካባቢ ተሰብስቦ በመኖሩ ነዉ። ብዙ አይቀላቀልም። ዩጋንዳዉያኑን የማቅረብ ነገር ብዙ አይታይም። ከዝያ አልፈሽ ግን ስትቀርቢያቸዉ በጣም ደስ የሚሉ ህዝቦች ናቸዉ። »
ኢትዮጵያዉያንስ የአገሪዉን ባህል ምግብ ለምደዉታል?
«እዚህ በዩጋንዳ አበሾች ያላቸዉ የንግድ ተቋማት በጣም ብዙ ነዉ። አበሾች ከትናንሽ ቡናቤት ጀምሮ እስከ ትላልቅ ፋብሪካ ኩባንያ የሚያስተዳድሩ ጥቂት አይደሉም። በተለይ ደግሞ አበሾች የመረጥዋቸዉ እና ሰብሰብ ብለዉ በሚኖሩባቸዉ አካባቢዎች፤ ሱቁም ሆነ ምግቤቱ እናም ሌላም ተቋማትስማቸዉ በአማርኛ በትልቁ ተጽፎ የሚታይባቸዉ ናቸዉ። ማስታወቅያ ሁሉ በamareና ተጽፎ ይታያል። ለምሳሌ ላምፓላ ዉስጥ ሃያ ሁለት የሚባል ሰፈር አለ፤ እዚህ ሰፈርዉስጥ ሲገባ አንድሁለት ዩጋንዳዊ ማግኘት እንኳ ያዳግታል። ሙሉዉን ሰፈር አበሻ ነዉ። ስጋቤት አለ ቡናቤት አለ የጀበና ቡና ይሸጣል። አበሻዉ እዝያ አካባቢ በሚገኝ ቡናቤት ወይም ሻይ ቤት ተሰብስቦ ይጫወታል፤ መረጃ ይለዋወጣል። ለምሳሌ ካሳንችስ የሚባል ምግቤትም አለ። አይቤክስ የሚባል ምግቤት አለ። ዩጋንዳ ዉስጥ በየጎዳናዉ ማስታወቅያ ላይ የአማርኛ ጽሑፍን ማየት ብርቅ አይደለም። የዩጋንዳን ምግብም አበሻዉ እየለመደዉ ነዉ። በጣም ጤናማ የሆነ ምግብ ነዉ። የሚከብድ ምግብ አይደለም። እኔን ጨምሮ ብዙ አበሾች ደስ ብሎን ነዉ የምንበላዉ። እኔ እንደዉም በሳምንት ሁለት ጊዜ እቤቴ አበስላለሁ።»
በሕክምና ሞያ ላይ የሚገኙ አበሾች ካምፓላ ዉስጥ አሉ
«እንዳልኩት ዩጋንዳ ለመኖር የሚጠበቅብሽ ብዙ ነገር ስላልሆነ ወይም ሁኔታዉ ቀላል በመሆኑ፤ ካምፓላ ዉስጥ የህክምና አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ያላቸዉ አበሾች አሉ። አንዱ የህክምና ተቋም ብትሄጂ ሐኪሞቹ፤ ረዳቶቹ ሁሉ አበሾች ሆነዉ የሚያስገርም ነዉ። ለምሳሌ የጥርስ ሐኪሞች የማህፀን ሐኪሞች አሉ፤ እነዚህ ሐኪሞች ግልጋሎት የሚሰጡት አበሾች በከፈትዋቸዉ ክሊኒኮች ዉስጥ ነዉ።»
ስለዩጋንዳ በቲክቶክ በምታጋራዉ መረጃ ብዙ ተከታዮችን ያፈራችሁ ጋዜጠኛ እንግዳወርቅ ተፈራ ፤ የተባበሩት መንግሥት በቅርቡ ይፋ ባደረገዉ ግምታዊ መረጃ ሃምሳ ሚሊየን አስራአምስትሺ ዘጠና ሁለት ህዝብ እንዳላት፤ መዲና ካምፓላ ዉስጥ ብቻ አራት ሚሊየን ስምንት መቶ ሃያ ስድስትሺ ነዋሪ ይገኛል ሲል ግምታዊ አሃዝን ማስቀመጡን አጫዉታናለች። ሙሉ ቃለ ምልልሱን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።
አዜብ ታደሰ
ታምራት ዲንሳ