ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች በሊቢያ | ኢትዮጵያ | DW | 27.04.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች በሊቢያ

የኢትዮጵያ መንግስት በሊቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገር ለመመለስ አስፈላጊውን ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል። በሊቢያ የሚገኙ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማህበራዊ ድረ-ገጽ ያሰራጫቸውን የስልክ ቁጥሮች ቢያገኙም ወደ አገር መመለስ ግን አስቸጋሪ መሆኑን ለዶይቼ ቨሌ ተናግረዋል።

ሰለሞን ሊቢያ ከገባ ከራረመ። ዋና አላማው የሜድትራኒያን ባህርን በማቋረጥ አውሮጳ መግባት ነበር። እንዳሰበዉ ግን እንዲህ በቀላል አልተሳካም። ከ120 በላይ ከሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ጋር ትሪፖሊ በሚገኝ የስደተኞች ማከማቻ መጋዘን ውስጥ የሚገኘው ሰለሞን «ከሱዳን ወደ ሊቢያ የሚልኩ ደላላዎች አሉ። በጣም ብዙ ልጆች ቤንጋዚ ከተማ የሚገኝ መጋዘን ውስጥ አሉ።ወደ ትሪፖሊ እንዳይመጡ በጣም ነገሮች ከረዋል። ከቤንጋዚ እስከ ትሪፖሊ ያለው ሁኔታ በጣም ሰው የሚገደልበት፤የሚታሰርበትና የሚዘረፍበት ነው።» ሲል የጉዞውን አስከፊነት ያስረዳል።ይሁንና አሁንም በርካቶች የጸጥታ ሁኔታዋ አሳሳቢ ወደ ሆነችው ሊቢያ በመጓዝ ላይ እንደሆኑ ይናገራል።

ሊቢያ ዉስጥ የ28 ኢትዮጵያውያን መገደል ከተሰማ በኋላ መንግስት በውጪ የሚኖሩ ስደተኞችን ለመመለስ ጥረት መጀመሩን አቶ ታምራት ደጀኔ የኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት የሚዲያ ልማትና ብዝሃነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በዶይቼ ቨሌ የእንወያይ መሰናዶ ላይ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መንግስት በሕጋዊም ይሁን ህገ-ወጥ መንገድ በውጭ አገራት የሚኖሩ ስደተኞችን ለመመለስ ዝግጁ ነኝ ሲልም ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ቀደም ሲል በሳዑዲ አረቢያ፣ የመንና ደቡብ አፍሪቃ በስደት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለጥቃት ሲጋለጡ ርዳታ ለማግኘት የሚጠቀሙባቸዉ የስልክ ቁጥሮችን ከመስጠት ጀምሮ ወደ አገር የሚመለሱበትን መንገድ እንዳመቻቸ አስታውቆ ነበር። ካለፈዉ ሳምንት ግድያ ወዲህ ሊቢያ ዉስጥ በጭንቀት ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ለመርዳት የሚደረገው ጥረት ግን ውስብስብ መሆኑን አቶ ታምራት ደጀኔ ጠቁመዋል።

«ሊቢያ ማዕከላዊ መንግስቱ የፈራረሰ ነው። ሰፊ አገር ነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሃላፊነት ወስዶ ይህን ጉዳይ የሚያስፈጽም መንግስት በሌለበት ሁኔታ ስራውን እጅግ ውስብስብና አደገኛ ነው የሚያደርገው።»

አሁንም የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሊቢያ ወደ አገር መመለስ ለሚፈልጉ ስደተኞች የሚያገለግሉ የስልክ ቁጥሮች በማህበራዊ ድረ-ገጾች አሰራጭቷል። ተግባራዊ ርምጃዉ ግን በአንድ ወገን የተሰዳጆቹን ፍላጎት በሌላ ወገን ደግሞ የመንግሥትንም አቅምና ስልት መጠየቁ አልቀረም። የሜድትራኒያን ባህርን ለማቋረጥ በመጋዘን ውስጥ ከሚጠባበቁ መካከል አማኑኤል «ወደ አገራችን ለመመለስ በጣም ከባድ ነው። ከቤት ልንወጣ አንችልም።» ሲል ያሉበትን ሁኔታ ያስረዳል። ከአማኑኤል ጋር በአንድ መጋዘን ውስጥ የሚገኘው አደፍርስ «ወደ ኢትዮጵያ መመለሱ በጣም ይከብዳል።አንደኛ ጸጥታ የለም ሁለተኛ ትንሽዬ ቤት ውስጥ ተዘግተን ነው ያለንው። መውጫ ራሱ የለም።» በማለት ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ቢፈልጉ እንኳእንደ ማይቻል ይናገራል።

አብዛኞቹ በሊቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሱዳን በኩል የሰሐራ በርሃን በማቋረጥ ሊቢያ የደረሱ ናቸው። ኢትዮጵያውያኑ አሁን ያሉበት ሁኔታ ይለያያል። ሰለሞን እንደሚለዉ እንደ አደፍርስ እና አማኑኤል ትሪፖሊ የወደብ ከተማ ደርሶ በመጋዘን መቀመጥ እንደ እድለኛ ያስቆጥራል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic