ኢትዮጵያን በተመለከተ ፈረንሳዊቷ እማኝ በአዉሮፓ ፓርላማ መድረክ | የጋዜጦች አምድ | DW | 19.05.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

ኢትዮጵያን በተመለከተ ፈረንሳዊቷ እማኝ በአዉሮፓ ፓርላማ መድረክ

በዕለቱ የእማኝነት መድረክ ምስክርነታቸዉን ለመስጠት በስፍራዉ ከተገኙት መካከል ፈረንሳዊቷ የኮምፕዩተር ድረ ገፅ ፀኃፊ አዲስ ፈረንጅ ትገኝበታለች።

አረንጓዴ፤ ብጫ ቀይ የሆነዉን የኢትዮጵያን ባንዲራ በአንገቷ ዙሪያ አድርጋለች አዲስ ፈረንጅ። ይህን ባንዲራችንን በመልበስ የሚታወቁትና በዓለም ዙሪያ በእሱዉ የሚለዩት የራስ ተፈሪያን ወገን ብትሆን ባልገረመኝ ሆኖም አንዲት ፈረሳዊት ባንዲራችንን አሳምራ ይዛዉ አየሁ በፈረንሳይ ግዛት ስትራስቡርግ።አዲስ ፈረንጅ የሚለዉ መጠሪያዋ በአዲስ አበባ የምትኖር የዉጪ ዜጋነቷን እንደሚያመላክት ነገረችኝ ስሟ ግን ናታሊ አምዮ ነዉ።

ለመሆኑ ምን የታዘብሽዉ ቢኖር ነዉ በዚህ በአዉሮፓ ፓርላማ ኢትዮጵያ ካለፈዉ ምርጫ አንድ ዓመት በኋላ በሚለዉ መድረክ ለመገኘት ያነሳሳሽ?

«እዚያ ከአራት ዓመታት በላይ ኖሬያለሁ። ያለፈዉ ምርጫ ከመካሄዱ በፊትም ሆነ በኋላ የነበረዉንና የተከሰተዉን ሁሉ በቅርበት ተከታትያለሁ። እናም የተደረገዉ ወከባና ተፅዕኖ የአይን ምስክር ነኝ። ሁኔታዉ በጣም ስላናደደኝ በኢንተርኔት በየቀኑ መጀመሪያ በፈረንሳይኛ ደረ ገፅ ከዚያም በእንግሊዝኛዉ ናዝሬዝ ኮም ላይ እየተከታተልኩ መዘገብ ጀመርኩ። መንግስት የግል ፕሬሱ ላይ ጫና አሳርፎ ባለበት ሁኔታ እንዲህ ያለዉ መንገድብቻ ነዉ መረጃ ሊያንሸራሽር የሚችለዉ። እናም ያን በተከታታይ ለማስኬድ በመቻሌ እዚህ ዛሬ እንዳየሽዉ ለእኔ በገረመኝ መልኩ በርካታ ተከታታዮችና አድናቂዎች ማትረፍ ቻልኩ።»

ለመሆኑ በቆይታሽ ምንድነዉ ልታይ የቻልሽዉ? ለምስክርነት ለመቆምስ ምን አስገደደሽ?

«ይህን የመረጃ ማሰራጨት ስራ ለመስራት ያስገደደኝ በርካታ አጋጣሚ አለ። ያንን ነዉ ዛሬ ለአዉሮፓ ፓርላማ ልናገር የመጣሁት። ለምሳሌ ችግር ያስከተሉት ሁኔታዎች ከተፈፀሩ በኋላ በጎጃም በረንዳ አካባቢ ነበርኩ። ሰዎች የሞቱት ሊሰርቁ ሲሉ ነዉ የሚል ነገር ተሰምቷል፤ ሆኖም ላረጋግጥልሽ የምፈልገዉ እንዲያ ባለ የድሆች መንደር ባንክም ሆነ የጌጣ ጌጥ መጋዘን የለም አልነበረም። ይህ አይነቱ ሁኔታ አሳበደኝ። የድርጊቱን ሰለባዎችና እየተዋከቡ ያሉትን ወገኖች ባገኘሁ ቁጥር የእኤም ተሳትፎ ከፍ እያለ ሄደ። ልክ አሁን አንቺ እንደምታደርጊዉ ከብዙዎች ጋር ቃለመጠይቅ አካሂጄያለሁ። ይነግሩኝ የነበረዉ ሁሉ እጅግ ያሳዝናል። በሰኔዉም ሆነ በህዳር የተፀመዉ ሁሉ የሆነዉ ወጣት ልጆች መፈክር እያሰሙ ሰላማዊ ሰልፍ ሲያደርጉ ነዉ።»

ግን ናታሊ ሰላማዊ ሰልፈኞቹ ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን ፖሊስ ላይ ወርዉረዋል ተብሏል፣ ባዶ እጃቸዉን አልነበሩም አሉ።

«ተቀጣጣይ ፈንጂ የሚባል አልነበረም። ከየት ያገኙታል? ድንጋይ ነበር የያዙት። ያም እዉነት ነዉ። እኔ የአይን ምስክር ነኝ። ሆኖም ድንጋይ ብቻ በታጠቁ ሲቪሎች ላይ ነዉ ጥይት የተተኮሰዉ። እምልሽ ድንጋይ ስለወረወርሽ ብቻ ልትገደይ አይገባም። በዚያ ላይ በከተማዋ የነበረዉ የወታደር ኃይል ከሚገባዉ በላይ ነበር። ለቅኝት ሲዟዟሩ ታያለሽ። ስድስት ሰባት ሆነዉ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱ መግቢያ ላይ ተቀምጠዉ ታያለሽ።»

እንዴት ወጣሽ ከአዲስ አበባ ተባረሽ ነዉ ወይስ ፈርተሽ?

«እንዲህ ባለዉ ከተማ ህፃን ልጄን ይዤ መቀመጥ አልፈለኩም። ለደህንነትሽ እርግጠኛ መሆን የማትችይበት ሁኔታ ነዉ ያለዉ።»

ከአራት ዓመታት በላይ አዲስ አበባ ነበርኩ ነዉ ያልሽኝ? ለመሆኑ ከምርጫዉ በፊት የነበሩትን ጊዜያትና ከዚያ በኋላ ያለዉን ሁኔታ እንዴት ነዉ የምትገልጪዉ?

«በሰኔ ወር ከተፈጠረዉ ችግርና ግድያ በኋላ ይህን መንግስት አምባገነን እንደነበር ለማረጋገጥ ችያለሁ። ያንን ከዚያ በፊት በፍፁም አላወቅኩም።»

መልካም ታዲያ ምስክርነትሽ ምን ያመጣል ብለሽ ነዉ እዚህ የተገኘሽዉ?

ያየሁትን ሁሉ እናገራለሁ። የአዉሮፓ ሀገራት ምን ማድረግ እንዳለባቸዉም እጠቁማለሁ። እነሱ በሚሰጡት እርዳታ መንግስት የራሱን ህዝብ ሲያሸብር እያዩ ዝም ሊሉ አይገባም።»

የሚሰሙሽ ይመስልሻል?

«እንደሚመስለኝ ብዙ በጮህን ቁጥር ሰሚ እናገኛለን። እሱን ነዉ ዛሬ እያደረግን ያለነዉ። ይሄ ትግል ነዉ። ምን ያህል ጊዜ እንደሚፈጅ ባላዉቅም የምችለዉን ሁሉ አደርጋለሁ።»