ኢቦላ እንደገና በሴራሊዮን | አፍሪቃ | DW | 16.01.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ኢቦላ እንደገና በሴራሊዮን

የዓለም የጤና ድርጅት የምዕራብ አፍሪቃ አገራት ከኢቦላ ነፃ ናቸው ሲል ቢያውጅም ቃሉ አልሰመረም።ለሁለት አመታት የዘለቀው እና 11,300 ሰዎች ለሞት፤በርካታ ህጻናትንም ወላጅ አልባ ያደረገው የኢቦላ ወረርሽኝ የቀጣናውን አገራት እንዲህ በቀላሉ የሚለቅ አይመስልም። እንዲህ ጠፋ ሲባል ብቅ እያለ ለምዕራብ አፍሪቃውያን ስጋት ሆኗል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 07:52

ኢቦላ እንደገና-ሴራሊዮን

በሴራሊዮን ዋና ከተማ ህይወት ወደ ነበረችበት የለት ተለት እንስቅስቃሴ ተመልሳ ነበር። ከአመት በፊት ሰዎች እጅ ለእጅ መጨባበጥ እንኳ ስጋት ነበረባቸው። በእያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸው እጆቻቸውን መታጠብ ግዴታ ሆኖም ነበር። የበጎ ፈቃድ ሰራተኛው ሃሳ ኮሮማ በአገሩ ሰዎች ላይ የሞት ጥላ ያጠላውን የኢቦላ ወረርሽኝ ለማጥፋት ከዘመቱት የሴራሊዮን ዜጎች አንዱ ነው።
«ኢቦላ ያለፈ ታሪክ በመሆኑ ደስተኞች ነን። በሽታው በሁሉም የአገሪቱ የሥራ ዘርፎች ላይ ጫና አሳድሯል። ቢሆንም በሴራሊዮናውያን ዘንድ ከፍተኛ የጤና ግንዛቤ ፈጥሮ አልፏል። እኔ በግሌ የቅርብ ጓደኞቼንና የቤተሰብ አባላትን አጥቻለሁ። እግዚዓብሄር ይመስገን አሁን በሴራሊዮን የተሻለ ግንዛቤ አለን።»

ይህ የሴራሊዮናውያን ደስታ እና የነጻነት ስሜት እንደገና የኢቦላ ስጋት ተጭኖታል። በሰሜናዊ ሴራሊዮን በዚህ ወር መጀመሪያ ከዚህ ዓለም በሞት በተለየች የ22 አመት ወጣት አስከሬን ላይ የተደረገ የኤቦላ ምርመራ ውጤት ፖዘቲቭ መሆኑን ትናንት የአገሪቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል። ከደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል ህክምና ፍለጋ ወደ ሰሜናዊ ሴራሊዮን ተጉዛ ነበር የተባለችው ወጣት የሞት መንስኤ የሆነው ኢቦላ ለአለም የጤና ድርጅት እና የሴራሊዮን መንግስት አስደንጋጭ ዜና ነው።
በዓለም ትልቁ የተባለውና ላይቤሪያ፤ጊኒ እና ሴራሊዮን ያዳረሰው የኢቦላ ወረርሽኝ 28,500 በላይ ሰዎችን ለህመም ዳርጓል። የሶስቱን አገራት የጤና መሰረተ-ልማት ደካማነት ያጋለጠው እና ከቀጣናው ተሻግሮ ዓለም አቀፍ የጤና ቀውስ ሊፈጥር ይችላል የሚል ስጋት የጫረው ወረርሽኝ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠባሳው ዛሬም ደምቆ ይታያል።

የዓለም የጤና ድርጅት ምዕራብ አፍሪቃ ከኢቦላ ነጻ ሆኗል ብሎ ሲያውጅ የመጨረሻው የላይቤሪያ ህመምተኛ የምርመራ ውጤት ኔጌቲቭ ከሆነ 42 ቀናትን አስቆጥሮ ነበር።በኢቦላ ወረርሽኝ ከታመሱት የምዕራብ አፍሪቃ አገራት መካከል አንዷ የሆነችው ሴራሊዮን ነጻ የተባለችው ከሁለት ወራት በፊት ነበር። በሴራሊዮን ብቻ ወረርሽኙ 3,955 ሰዎችን ለሞት ዳርጓል። በኢቦላ ከተያዙ ህመምተኞች ግማሽ ያህሉ ድነዋል። በሽታውን መቋቋም የቻሉት ደም በመለገስ፤የሙታንን አስከሬን በመቅበር እና የታመሙትን በመንከባከብ ወረርሽኙን ለመቋቋም በተደረገው ርብርብ ውስጥ ግንባር ቀደም ሚና መጫወታቸውን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።
የዓለም የጤና ድርጅት የኢቦላ ወረርሽኝ ሲቀሰቀስ ምላሽ ለመስጠት ዘገምተኛ ነበር እየተባለ ይወቀሳል። አሁን ዓለም አቀፉ ተቋም ደካማውን የምዕራብ አፍሪቃ የጤና መሰረተ-ልማት ለመገንባት ፤ብቁ ባለሙያዎችን ለማሰልጠን እና ግንዛቤውን ለማሳደግ ተፍ ተፍ እያለ ነው። ፒተር ግራፍ የዓለም የጤና ድርጅት የሴራሊዮን ተወካይ ናቸው።
«ህመምተኞች ሲያጋጥሙ የህክምና ማዕከላት እና መንግስታት በሽታው ኢቦላ ወይም ሌላ ከባድ ህመም መሆኑን ለመለየት የሚያስችሏቸው በቂ እና በብቃት የሰለጠኑ የጤና ባለሙያዎች፤ ጠንካራ የክትትል እና ቁጥጥር ስልት፤የተሟሉ ላብራቶሪዎች መኖራቸው መረጋገጥ ይኖርበታል።»
በዘገምተኛቱ የሚወቀሰው ግን የዓለም ጤና ድርጅት ብቻ አይደለም። በሴራሊዮን፤ጊኒ እና ላይቤሪያ ያለው የጤና አገልግሎት መሰረተ-ልማት በብቃት የተደራጀ አልነበረም። በገንዘብ፤የሰለጠነ የሰው ኃይል እና የቁሳቁስ እጥረት የተዳከመ ነበር። ስለኢቦላ ተኅዋሲ ያለው አናሳ ግንዛቤም ሆነ የጤና ማዕከላቱ የተኅዋሲው ባህሪ በብቃት መለየት አለመቻል ሌላው ጉድለት ነበር። ናይጄሪያዊው ህክምና ተመራማሪ ኦያዋሌ ቶሞሪ የቀጣናው አገራት እንደ ኢቦላ አይነት ወረርሽኝ ለመቋቋም ዝግጁ እንልሆኑ ይተቻሉ።
«በፍጹም ዝግጁ አልነበርንም። አሁን ድረስ ከኢቦላ ወረርሽኝ ለመላቀቅ እየታገልን ነው። ነገር ግን ምንም ያዘጋጀንው ነገር የለም። ወደ ፊት ሊከሰት የሚችል የኢቦላ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር አሁንም አልተዘጋጀንም።»
የኢቦላ ወረርሽኝን መቀነስ ብሎም መግታት ለዓለም የጤና ድርጅትም ሆነ የምዕራብ አፍሪቃ አገራት ትልቅ ስኬት ተደርጎ ቢቆጠርም ለመጻዒው ጊዜ ማስተማመኛ አይደለም። የኢቦላ ተኅዋሲ ዛሬም ድረስ ከዳኑ ህሙማን ሰውነት ውስጥ መቆየት ይችላል። ምዕራብ አፍሪቃ ነጻ በተባለበት ዕለት «ተኅዋሲው በወንድ ልጅ የዘር ፈሳሽ ውስጥ እስከ 12 ወራት ሊቆይ ይችላል።» ሲሉ የተናገሩት የዓለም ጤና ድርጅት የአስቸኳይ ጊዜ አደጋ መከታተል እና የሰብዓዊ ምላሽ ኃላፊ ሪክ በርናን ወረርሽኙ በማንኛውም ጊዜ ተመልሶ ሊመጣ እንደሚችል አስጠንቅቀው ነበር። ወረርሽኙ ለአሁኑ ባይከሰትም ኢቦላ ግን ርቆ ላለመሄዱ ሴራሊዮን ማሳያ ሆናለች። ፒተር ግራፍ ከኢቦላ ወረርሽኝ በኋላ በሶስቱ የምዕራብ አፍሪቃ አገራት ላይ ትኩረት ያደረጉ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት በፍጹም ቸልተኛ ሊሆኑ እንደማይገባ አስጠንቅቀዋል።


«ከአጋሮቻችን፤መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና መንግስታት ጋር በጥምረት መስራታችንን እንቀጥላለን። በሶስቱም አገራት ያለ ውጪ እርዳታ ኢቦላ መሰል ፈተናዎችን መቋቋም የሚችል ብሔራዊ አቅም ለመኖሩ እርግጠኞች ልንሆን ይገባል። በነገራችን ላይ ኢቦላን በተመለከተ ከየትኛውም የዓለም ክፍል የበለጠ በአሁኑ ወቅት የተሻለ ግንዛቤ እና አቅም ያለው በጊኒ፤ሴራሊዮን እና ላይቤሪያ ነው።»
የዓለም የጤና ድርጅት የሴራሊዮንን አዲስ የኢቦላ መረጃ ከሰማ በኋላ ባወጣው መግለጫ በመጪዎቹ ጊዜያትም አነስተኛ ወረርሽኞች ሊከሰቱ እንደሚችሉ በመጠቆም ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስቧል። በዓለም የጤና ድርጅት የኢቦላ ግብረ-መልስ ተልዕኮ ኃላፊ ዶ/ር ብሩስ አይልዋርድ «አሁን ሰፊው የኢቦላ ወረርሽኝ ቢቆምም አሁንም ግለሰቦችን እያከምን እና አዳዲስ ህሙማን መኖራቸውን እየተከታተልን ነው።» ሲሉ ተናግረዋል ።
ዶ/ር ብሩስ አይልዋርድ አሁን በርካታ ህሙማን በማከም እና ሙታንን በመቁጠር ባይጠመዱም ከፍተኛ ጥንቃቄ ከሚፈልገው ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል። የኢቦላ ወረርሽኝ ነሴራሊዮን፤ጊኒ እና ላይቤሪያ የጤና መሰረተ-ልማት እና አገልግሎት ላይ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚያቸው ላይም ከፍተኛ ጫና አሳድሯል። የጤና አገልግሎት አቅራቢ ማዕከላት እና ባለሙያዎች ግን አሁንም ያገገሙ አይመስልም። የጤና ማዕከላቱ የነበረባቸው የገንዘብ ችግር ተቀርፎ የመንግስታት እና ዓለም አቀፍ ተቋማትን ትኩረት ቢስቡም በርካታ ከሟቾቹ መካከል ባለሙያዎቻቸውም ይገኙበታል። ናይጄሪያዊው ህክምና ተመራማሪ ኦያዋሌ ቶሞሪ የምዕራብ አፍሪቃ አገራት የዝግጅት ማነስ አሁንም ያሳስባቸዋል።


«ከተቆጣጠርንው የባለፈው ዓመት የኢቦላ ወረርሽኝ በኋላ በናይጄሪያ የትኩሳት ወረርሽኝ ተከስቷል። ወረርሽኙ በህዳር ወር ጀምሮ እየተስፋፋ ሲሆን ህመሙ ከያዛቸው ሰዎች እስከ 50 በመቶው ሞተዋል። እስካሁን መፍትሔ አላገኘም። ይህ ዝግጁ አለመሆናችንን ነው የሚጠቁመው። ለምንም አይነት ህመም ቢሆን ናይጄሪያም ሆነች ሌሎች የአካባቢው አገራት በፍጹም ዝግጁ አይደሉም።»
የሴራሊዮን ባለስልጣናት በኢቦላ ምክንያት ለሞት የተዳረገችው የ22 አመት ወጣት የተገናኙ ሰዎችን በማሰስ ላይ መሆናቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል። ምን አልባት ወጣቷ ካገኘቻቸው ሰዎች መካከል በኢቦላ የተያዙ ሰዎች መኖራቸውን ማጣራት እና መለየት ዋንኛ ተግባራቸው ነው። የዓለም የጤና ድርጅት የሴራሊዮን፤ጊኒ እና ላይቤሪያ ዜጎች የግል ንጽህናቸውን እንዲጠብቁ እና የአስቸኳይ ጊዜ መመሪያዎችን በትኩረት እንዲከታተሉ መመሪያ አስተላልፈዋል። ለሴራሊዮን ዜጎች አሁን የተደመጠው የሞት ዜና ቀድሞ ወደ ነበሩበት የጥርጣሬ እና ስጋት መመለስ ምልክት ነው። የዓለም ጤና ድርጅት በሶስቱ አገራት ከፈታቸው 70 የመስክ ቢሮዎች አሁንም አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው። እስከ ጎርጎሮሳዊው 2016 ዓ.ም ድረስ ክፍት ሆነው ይቀጥላሉ።
እሸቴ በቀለ
ሒሩት መለሰ

Audios and videos on the topic