ኢቦላ ቫይረስ የአፍሪቃ ስጋት | ጤና እና አካባቢ | DW | 08.04.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

ኢቦላ ቫይረስ የአፍሪቃ ስጋት

ኃይለኛ ትኩሳት፤ ራስ ምታትና የጡንቻ ህመም ከሚያስከትላቸዉ የህመም ስሜቶች ይጠቀሳሉ። በትንፋሽ ሳይሆን ከአካል በሚወጣ ፈሳሽና በመነካካት ይተላለፋል። እስካሁንም መድሃኒት አልተገኘለትም ኢቦላ ቫይረስ። ከሳምንታት በፊት ጊኒ ዉስጥ በሽታዉ ተከስቷል

ኢቦላ ቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተዉ በጎርጎሪዮሳዊዉ 1976ዓ,ም ነዉ፤ ናዛር ሱዳን ዉስጥና ያምቡኩ ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ። ቦታዎቹ የገጠር መንደሮችና እርጥበትና ሙቀት በማይለዉ ደን አካባቢ የሚገኙ ናቸዉ። በወቅቱም የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለዉ ሱዳን ዉስጥ 284 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዉ 151ዱ ህይወታቸዉን አጥተዋል። ዴሞክራቲክ ኮንጎ ደግሞ 318 ታመዉ 280 አልተረፉም። ሱዳን ዉስጥ በ19 79 እንዲሁም 2004ዓ,ም በጎርጎሪዮሳዊዉ ቀመር ማለት ነዉ ዳግም ተከስቷል። ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ ዉስጥ ግን እያሰለሰ ለ10 ጊዜያት መደጋገሙን የዓለም የጤና ድርጅት የመዘገበዉ መረጃ ያመለክታል። ቫይረሱ ስሙን ያገኘዉ ኮንጎ ዉስጥ በሽታዉ በተከሰተበት ሰሜናዊ የሀገሪቱ አካባቢ ከሚገኘዉ ኤቦላ ወንዝ ነዉ። ኤቦላ ወንዝ የታላቁ ኮንጎ ወንዝ ገባር የሆነዉ ሞንጋላ ወንዝ መገኛ ምንጭ መሆኑ ይነገርለታል። ቫይረሱ ስሙን ህይወት አንድ ከሆነዉ ወራጅ ዉሃ ያግኝ እንጂ ቫይረሱ ከመነሻዉ ከታወቀበት ጊዜ አንስቶ እስከአሁን ነፍስ በመቅጠፍ ነዉ የሚታወቀዉ። የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለዉም በኢቦላ ቫይረስ ከተያዙ ሰዎች 90 በመቶዉ አይተርፉም።

ከሳምንታትም በፊት ደን በበዛበት በደቡባዊ ጊኒ የኢቦላ ቫይረስ ወረርሽኝ በድንገት ተከስቶ ለበርካቶች ህይወት ማለፍ ምክንያት ሆኗል። በተጨማሪም ከአንድ መቶ ሃያ የሚልቁም እንዲሁ በቫይረሱ ሳይያዙ እንዳልቀሩ የምርመራ ዉጤት እያመለከተ ነዉ።

በአካባቢዉ ለእርዳታ የተሰማሩ የህክምና ባለሙያዎች ተገቢዉን ጥንቃቄ ካላደረጉም እነሱንም ሊያሰጋ እንደሚችል ነዉ ማስጠንቀቂያ የተሰጠዉ። በስፍራዉ ከተሰማሩት አንዱ የሆኑት የድንበር የለሽ ሃኪሞች ባልደረባ ሚሼል ፋን ኸርፕ በአካባቢዉ የተከሰተዉ ቫይረስ ከያዛቸዉ መካከል የብዙሃኑን ህይወት ሊያጠፋ የሚችል አደገኛ ነዉ ይላሉ፤

«በጣም አደገኛ የሆነዉ የኢቦላ ቫይረስ ዓይነት ነዉ እዚህ የገጠመን ። ዛየር ኢቦላ ቫይረስ የሚባለዉ ማለት ነዉ። ይህኛዉ ዓይነት ከያዛቸዉ አስር ሰዎች ዘጠኙን ይገድላል።።»

ድንገተኛና ኃይለኛ ትኩሳት፣ ድካም እንዲሁም የጡንቻ ህመም፤ ራስ ምታት እና የጉሮሮ ህመም የበሽታዉ ዓይነተኛ ምልክቶች ሲሆኑ ማስመለስና ማስቀመጥም ያስከትላል። በመቀጠልም የኩላሊትና ጉብተን ተግባር በማሰናከል አንዳንዴ አካል ዉስጥም ሆነ ከዉጭ የደም ፍሰት ያመጣል። ቫይረሱ ከአንዱ ወደሌላ ሰዉ በፍጥነት የሚጋባ በመሆኑም ይታወቃል።

የኢቦላ ቫይረስ ከሰዉ ወደሰዉ የሚተላለፈዉ በትንፋሽ ሳይሆን ደምን ጨምሮ ከሰዉነት በሚወጣ ፈሳሽ እና ንክኪ አማካኝነት መሆኑ ነዉ የሚገለፀዉ። በበሽታዉ ህይወቱ ያለፈዉን ሰዉ አስከሬን መንካት ቢሆን ተመሳሳይ መዘዝ ይኖረዋል። በዚህ ምክንያትም ሃኪም ቤቶች ሳይቀሩ ቫይረሱ የመተላለፍ አጋጣሚዉን የሚጠቀምባቸዉ መንገዶቹ እንደሚሆኑ ነዉ የህክምና ባለሙያዎች የሚያሳስቡት።

እንደጤና ባለሙያዎች እምነትም ሰዉ ብቻ ሳይሆን እንስሳትም ቫይረሱ ለማሸጋገር ዓይነተኛ ሚና ይጫወታሉ። በተለይ የሌሊት ወፍ ከበሽታዉ አሸጋጋሪዎች ግንባር ቀደም ሳትሆን እንደማትቀር ትጠረጠራለች።

ኢቦላ ቫይረስ መነሻዉ ማዕከላዊ አፍሪቃ እና ደቡብ ምስራቅ እስያ ናቸዉ ቢባልም በአብዛኛዉ ግን በማዕከላዊና ምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት ገጠራማ አካባቢዎች ይከሰታል። በተለይም በዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ፣ ሱዳን፣ ጋቦን፣ አይቮሪኮስት እንዲሁም ዩጋንዳ ባለፉት 36 ዓመታት በሽታዉ በተደጋጋሚ የታየባቸዉ ሃገራት ናቸዉ። ከሳምንታት በፊት ቫይረሱ ጊኒ ዉስጥ መታየቱ በተነገረ ሰሞንም በዚያ ሳይወሰን ወደላይቤሪያም መዛመቱ ታይቷል። ማሊና ሴራሊዮንም እንዲሁ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ሳይኖሩ እንዳልቀሩ የህክምና ባለሙያዎች ጥርጣሬያቸዉን እየገለጹ ነዉ።

የዓለም የጤና ድርጅት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ኢቦላ ቫይረስ መሰል ሌሎችም ቫይረሶችም አሉ። ለህይወት አደገኛ እንደሆኑ የሚነገርለትን የኢቦላ ቫይረስና ተመሳሳይ አደገኛ ቫይረሶችን ዋና መንስኤያቸዉ እስካሁን በእርግጠኝነት አልተነገረም። ከእንስሳት መገኘቱ ቢነገርለትም እነሱን በምን ምክንያት ለቫይረሱ እንደሚጋለጡ ገና አልታወቀም። ከዚህ በመነሳትም ይመስላል ስዉም ሆነ እንስሳትን ከኢቦላ ቫይረስ ማዳን የሚችል መድሃኒትም ሆነ መከላከያ ክትባት እስካሁን የለም።

በአንድ ወገን ለበሽታዉ መፍትሄ የሚሆን አብነት ላለመኖሩ የሚሰጠዉ ምክንያትም ካለፍ አገደም የሚከሰት የጤና እክል በመሆኑ ለእሱ የሚሆን መድሃኒት ለመሥራት ትላልቆቹ የመድሃኒት ኩባንያዎች ገንዘባቸዉን ለዚህ ያዉላሉ ተብሎ እንደማይገመት ነዉ። መድሃኒቱ በቀጣይነት ተፈላጊ ላይሆን ስለሚችል ማለት ነዉ። ትርፍና ኪሳራን በማስላት። የመድሃኒት ተስፋ እንደሌለ በማስተዋልም በጊኒ ዋና ከተማ ኮናክሪ ባለስልጣናት ኅብረተሰቡ የራሱንና የአካባቢዉን ንፅህና እንዲጠብቅ ቅስቀሳና ዘመቻ እያካሄዱ ነዉ። በጊኒ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የበሽታ መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ሳኮባ ኬይታ ስለሁኔታዉ እንዲህ ያስረዳሉ፤

«ጉዳዩ ከሚመለከታቸዉ ከተለያዩ ወረዳዎች ከመጡ ልዩ ልዩ የመንግስት አመራር አካላት፣ ከኅብረተሰቡና ከግል ዘርፎች ከተዉጣጡ ወገኖች ጋ ስብሰባ አካሂደናል። እናም ባስቸኳይ እነዚህን ርምጃዎች ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጠይቀናቸዋል።»

ጥቂት የማይባሉ ሰዎችን ህይወት ቫይረሱ ቢያጠፋም ድንበር የለሽ ሃኪሞች እንደሚችለዉ እስካሁን ጊኒ ዉስጥ በኢቦላ ተይዘዋል ተብለዉ ከተጠረጠሩ በርከት ያሉ በሽተኞች ገሚሱ ነፃ መሆናቸዉ እየተረጋገጠ ከሃኪም ቤት ወጥተዋል። ሃኪሞቹ እንደሚሉትም እነዚህን ሰዎች መጨበጡም ሆነ መሳሙ አሁን ለቫይረሱ ያጋልጣል የሚል ስጋት አይኖርም። ኢቮላ ቫይረስ የሚያሳየዉ የህመም ምልክት ከመነሻዉ ቢታይባቸዉም በሽታ የመቋቋም አቅባቸዉ ጠንካራ በመሆኑ በቀላሉ በተደረጋለቸዉ የህክምና ክትትል ጤናቸዉ ተመልሷል። በዚህ ሁኔታ ላይ ከነበሩት ህመምተኞች መካከል የመጀመሪያዉ ድነዉ ከሃኪም ቤት ሲወጡ ታማሚዉና ቤተሰቦቻቸዉ ብቻ ሳይሆኑ ሃኪሞቹም እጅግ መደሰታቸዉን ነዉ የተናገሩት።

በአሁኑ ወቅት የኢቦላ ቫይረስ ጊኒ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ሃገራትም እየታየ ነዉ። በጥቅሉ በምዕራብ አፍሪቃም እስካሁን ከአንድ መቶ በላይ ሰዎችን ገድሏል። ሳኮባ ኬይታ ዛሬ እንዳመለከቱት ጊኒ ዉስጥ ብቻ አሁንም ከ151 የሚልቁ ሰዎች በቫይረሱ ሳይያዙ እንዳልቀሩ ምልክቶች እየታዩ ነዉ። የዓለም የጤና ድርጅት በበኩሉ ላይቤሪያ ዉስጥ በኢቦላ ቫይረስ 10 ህይወታቸዉን እንዳጡ ሌሎች 21 ሰዎችም እንደተያዙ ገልጿል። በተቃራኒዉ ጋና ዉስጥ በነበራት ኃይለኛ ትኩሳት ምክንያት በኢቦላ ሳትያዝ እንዳልቀረች የተሰጋ አንዲት የ12ዓመት ልጅ በተደረገላት የደም ምርመራ በቫይረሱ እንዳልተያዘች መረጋጡን የሀገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሼሪ አይቴይ ትናንት ገልጸዋል። ከልጅቱ ለምርመራ ወደአክራ የተወሰደዉ ናሙና ወደሀገሪቱ የህክምና ዩኒቨርሲቲ ማዕከል ተወስዶ ከተመረመረ በኋላ ነፃ መሆኗ ቢነገርም MSF የህክምና አገልግሎት ይዞታዉ በተዳከመዉ አካባቢዉ ኢቦላ ቫይረስ ዉሎ አድሮ ችግር ሊያደር እንደሚችል አስጠንቅቋል። ሴራሊዮን በበኩሏ ሁለት ሰዎች በኢቦላ ቫይረስ መያዛቸዉን ስታረጋግጥ፤ ማሊ ዉስጥ ደግሞ በኢቦላ ሳይያዙ እንዳልቀሩ ከተጠረጠሩ ስድስት ህመምተኞች ሁለቱ ነጻ መሆናቸዉ ተገልጿል። የህክምና ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት አንድ ሰዉ በኢቦላ በተያዘ ከሁለት እስከ 21ቀናት ቫይረሱ በዚያ ሰዉ ዉስጥ አቅሙን አጠናክሮ ማጥቃቱን ይጀምራል። ያኔ ነዉ ትኩሳቱም ሆነ የጡንቻ ህመም ብሎም ራስ ምታት የሚመጣዉ፤ ከዚያም ዓይነተኛ የተባሉት ምልክቶች ይቀጥላሉ። የምግብ ፍላጎት ይጠፋል። በሂደቱም አንጀትን እንዲሁም የመተንፈሻ አካላትን ማወክና መጉዳቱን ቀጥሎ ለህልፈት ይዳርጋል።

ቫይረሱ አንዴ በሰዉነት ገብቶ ሥር ከሰደደ መፍትሄ ስለሌለዉም ሊደረግ የሚችለዉ ራስን የመከላከል ርምጃ ብቻ ነዉ። ለዚህም የአካባቢና የግል ንፅህናን ከመጠበቅ አንስቶ ሃኪም ቤት ከሄዱ እጆችን በጥንቃቄ ማፅዳት ማለትም በሳሙናና ዉሃ መታጠብ፤ የሚቻል ከሆነም በባዶ እጅ ሳይሆን በፕላስቲክ እጅ መሸፈኛ ወይም ጓንት መጠቀም ራስን ከኢቦላ ቫይረስም ሆነ ከሌሎች አደገኛ ተህዋሲያን ለመከላከል ይመከራል።

ኢቦላ ቫይረስ የዛሬ 38ዓመታት ገደማ ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ ዉስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከታየ አንስቶ እስካሁን 15 የአፍሪቃ ሃገራት ቫይረሱ ሊገኝባቸዉ እንደሚችል የዓለም የጤና ድርጅት ያመለክታል። እስካሁንም አፍሪቃ ዉስጥ ከአንድ ሺህ ሶስት መቶ ሰዎች በላይ ገድሏል። ከዱር እንስሳት ወደሰዎች እንደተላለፈ የሚነገርለት ኢቦላ ቫይረስ በተለይ የአፍሪቃ ስጋት ብቻ መሆኑ ነዉ እስካሁን የሚታወቀዉ።

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic